
ከሩሲያ ከፍተኛ ጄነራሎች አንዱ የሆኑት ያሮስላቭ ሞስካሊክ ሞስኮ ውስጥ መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ጥቃት መገደላቸው የሩሲያ መንግሥት አረጋገጠ።
ከፍተኛ የጦር መኮንኑ ሩሲያ ውስጥ በዩክሬናውያን ዒላማ ከተደረጉ ከፍተኛ የክሬምሊን አመራሮች አንዱ ናቸው።
በአራት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የሩሲያ ጄነራል መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ በዋና ከተማዋ ሞስኮ ውስጥ ሲገደል ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የአገሪቱ ብሔራዊ የስለላ ተቋም ቃል አቀባይ ስቬትላና ፔትረንኮ እንዳሉት፣ የቦምብ ፍንዳታው የተፈጸመው ቤት ውስጥ በተሠራ ቦምብ ነው።
ባለፈው ታኅሣሥ የሩሲያ የራድየሽን፣ ኬሚካል እና ባዮሎጂካል ክፍል መሪ የነበሩት ጄነራል ኢጎር ኪሪሎቭ እዚያው ሞስኮ ውስጥ መገደላቸው ይታወሳል።
ግልሰቡ የተገደሉት በኤሌክትሪክ በሚሠራው ሳይክላቸው ላይ በተጠመደ ቦምብ ነበር።
ከዚህ ግድያ ከጥቂት ቀናት በፊት ዋነኛው የሩሲያ የሚሳዔል ሳይንቲስት ሚኻይል ሻታስኪ ሞስኮ አቅራቢያ ደን ውስጥ ተተኩሶባቸው ተገድለዋል።
ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው የዩክሬን የሕዝብ እንደራሴ የነበሩት የሩሲያ ደጋፊ ሊልያ ካያ ከሞስኮ ውጭ ባለ ፓርክ ውስጥ በተመሳሳይ በጥይት ተገድለዋል።
የአሜሪካው ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ዛሬ አርብ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተዋል። ከፑቲን ጋር ሲገናኙ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እንዳሉት ከዩክሬን ጋር የተኩስ አቁም ለመስማማት ዝግጁ ናቸው። ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቢቀጥሉም ሩሲያ በዩክሬን የምትፈጽመው ጥቃት ቀጥሏል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ከሩሲያ ጋር የሰላም ስምምነት ለማድረግ ዩክሬን መወሰን አለባት ብለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ በሩሲያ ቁልፍ ሰዎች ላይ ግድያዎች ሲፈጸሙ ዩክሬን በቀጥታ ተሳትፎ እንዳላት ገልጻ አታውቅም።
የያሮስላቭ ሞስካሊክ ግድያን በተመለከተ የአገሪቱ ብሔራዊ ስለላ ተቋም ቃል አቀባይ ስቬትላና ፔትረንኮ እንዳሉት፣ ጄነራሉ በሚያሽከረክሯት ቮልስዋገን ጎልፍ መኪናቸው ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ መገደላቸውን ገልጸዋል።
አሜሪካ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ስምምነት እንዲደረስ ጥረት እያደረገች ባለበት ጊዜ የተፈጸመው ጥቃት፣ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ሞስኮ ውስጥ ሳሉ ነው።
የተኩስ አቁም በሚደረግበት ወቅት የኪቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊትችኮ “ዩክሬን ለሰላም ስምምነት ሲባል ግዛቷን ለማጣት ዝግጁ መሆን አለባት” ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አማካሪ ሸርሊ ሌሽሄንኮ በበኩላቸው መጀመሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደርሶ በቀጣይ ንግግሮች ይቀጥላሉ ብለዋል።
አሜሪካ ለተኩስ አቁም ስምምነት ለአውሮፓ ባለሥልጣናት ባቀረበችው እና ሮይተርስ በተመለከተው ዕቅድ እንደተጠቀሰው፣ የዩክሬንን ደኅንነት ማስጠበቅ አንደኛው ግብ ነው።
ለዩክሬን ደኅንነት ማስተማመኛ መስጠት እንዳለ ሆኖ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) እንዳትቀላቀል ይደረጋል ተብሏል።
የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ በሩሲያ ይዞታ ሥር ስላሉ የዩክሬን ግዛቶች ውይይት እንደሚጀመር ይህ የተኩስ አቁም ሰነድ ያመለክታል።