Quantcast
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

ግብፅ እና ጂቡቲ የቀይ ባሕር አስተዳደር የተጎራባች ሀገራት “ብቸኛ ኃላፊነት”እንደሆነ መስማማታቸው ተገለጸ

ግብፅ እና ጂቡቲ፤የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ “የአስተዳደር እና የፀጥታ” ጉዳይ የውሃ አካላቱን የሚጎራበቱ ሀገራት “ብቸኛ ኃላፊነት” እንደሆነ መስማማታቸውን የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ ተናገሩ።

ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም. ለይፋዊ የአንድ ቀን ጉብኝት ወደ ጂቡቲ ተጉዘው የነበሩት የግብፅ ፕሬዝዳንት አልሲሲ፤ ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡማር ጊሌ ጋር ተገናኝተው ንግግር አድርገዋል።

ሁለቱ መሪዎች ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የገለጹት የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል፤ በዚህ ንግግር የሶማሊያ እና ሱዳን ጉዳይ መነሳቱንም ጠቅሰዋል።

እንደ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ገለጻ ሁለቱ መሪዎች የተነጋገሩበት ሌላኛው ቀጣናዊ ጉዳይ የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤን የሚመለከት ነው። ሀገራቱ፤ ቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤን የሚያገናኘውን የባብ ኤል ማንደብ የባሕር ወሽመጥን በተመለከተ መነጋራቸውን የጂቡቲው ፕሬዝዳንት አስታውቀዋል።

ይህ የባሕር ወሽመጥ በጅቡቲ፣ በኤርትራ እና በየመን የሚገኝ ስትራቴጂክ አካባቢ ነው። ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች በዚህ የባሕር ወሽመጥ “የደኅንነት ሁኔታ” ላይ እንደተወያዩ ተገልጿል።

ወሳኝ የዓለም አቀፍ ንግድ መተላለፊ በሆነው ቀይ ባሕር “ነጻ የባሕር ንግድ እንቅስቃሴ” እንዲኖር ለማስቻል እና የባሕሩን “መረጋጋት ለማረጋገጥ” የሚያደርጉትን ትብብር ለማጠናከከር እንደስተማሙም የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል አስታውቀዋል።

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብድልፈታህ አል ሲሲሰ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር “አፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ቀጣና ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ” ከጂቡቲው ፕሬዝዳንት ጋር “ሰፊ” ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ሁለቱ ሀገራት በቀይ ባሕር ላይ “የሚያጋጥሟቸውን የጋራ ተግዳሮቶች” በተመለከተም ንግግር መደረጉ ተጠቅሷል።

ፕሬዝዳንት አል ሲሲ በንግግራቸው፤ “በወሳኝ የዓለም አቀፍ ንግድ መስመሮች ላይ የሚቃጣን ማንኛውም የደኅንነት እና በነጻነት የመጓዝ አደጋዎችን በማያሻማ ሁኔታ እንደምንቃወም አረጋግጠናል” ሲሉ ከጅቡቲው ፕሬዝዳንት ጋር የተስማሙበትን ነጥብ አንስተዋል።

በተጨማሪም፤ “ለቀጣናዊ ደኅንነት መርሆዎች እና መሠረቶች ለመገዛትን አስፈላጊነትን” በተመለከተም መግባባት ላይ እንደደረሱ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። አል ሲሲ፤ ከጂቡቲው ፕሬዝዳንት ጋር ከስምምነት ላይ እንደደረሱ የገለጹት ሌላኛው ጉዳይ የቀይ ባህር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ የአስተዳደር ጉዳዮችን የሚመለከት ነው።

ሁለቱ መሪዎች “ወሳኝ ዓለም አቀፍ የባሕር ንግድ መተላለፊያ” የሆኑት “የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ የአስተዳደር እና የደኅንነት ጉዳይ የተጎራባች ሀገራቱ ብቸኛ ኃላፊነት” እንደሆነ “ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን” አስታውቀዋል።

ግብፅ የቀይ ባሕር የአስተዳደር ጉዳይ የውሃ አካሉን የሚጎራበቱ ሀገራት “ብቸኛ ኃላፊነት” መሆኑን ስታነሳ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት “የህልውና ጉዳይ” መሆኑን እንዲሁም ሀገሪቱ ቀይ ባሕር ለደኅንነቷ አስፈላጊ መሆኑን በተደጋጋሚ ማንሳት መጀመራቸውን ተከትሎ በግብፅ በኩል ይህ አቋም ሲንጸባረቅ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ ግንታውን ልታጠናቅቅ በተቃረበችው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለዓመታት ተቃውሞዋን ስታሰማ የቆየችው ግብፅ ኢትዮጵያ እያሳየችው ካለው በቀይ ባሕር በኩል መተላለፊያ በር ከማግኘት በተቃራኒ የአካባቢውን አገራት እያስተባበረች ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያን በቀይ ባሕር በኩል ወደብ የማግኘት ፍላጎትን ይፋ ባደረጉበት ጊዜ “ቀይ ባሕር እና የዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያን የሚበይኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ናቸው” ማለታቸው አይዘነጋም።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ ታኅሣሥ ወር ላይ ወደ ግብፅ በተጓዙበት ወቅትም ይህ የግብፅ አቋም ተነስቶ ነበር።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ባደረጉት ንግግር ቀይ ባሕርን ሊጠቀሙ የሚገባው “ተጎራባች ሀገራት ብቻ” እንደሆነ እና “ሌላ አካል” ወደ ቀይ ባሕር “እንዲቀባ ሊፈቅድለት እንደማይገባ” ተናግረው ነበር።

ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳለህ ወደ ግብፅ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት አል ሲሲሰ ጋር በተነጋገሩበት ወቅትም በተመሳሳይ፤”የቀይ ባሕር የአስተዳደር እና ደኅንነት ጉዳይ” የተጎራባቾቹ ሀገራት “ብቸኛ ሚና” እንደሆነ መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን ለማሳከት ሶማሊያ እንደ ራሷ ግዛት ከምትቆጥራት ሶማሊላንድ ጋር ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. ስምምነት ላይ ደርሳ የነበረ ቢሆንምለ ስምምነቱ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።

ከሶማሊላንድ ጋር የነበረው ስምምነት ኢትዮጵያ የባሕር ጦር ሰፈር እና ወደብ እንድታገኝ የሚያስችል እንደሆነ ገልጾ ነበር።

ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ በቱርክ አሸማጋይነት ከሶማሊያ ጋር የወደብ ተጠቃሚነት ለማግኘት የሚያስችል ስምምነት ላይ ቢደርሱም ሞቃዲሾ ለኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር እንደማትሰጥ ገልጻለች።

ዜና ምንጭ BBC NEWS https://www.bbc.com/amharic/articles/c807j857zdvo


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>