Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ አረፉ

$
0
0
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ፓፕ ፍራንሲስ

ለረጅም ጊዜ በከባድ የጤና ችግር በሕክምና ላይ የቆዩት የ88 ዓመቱ አዛውንት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፓፕ ፍራንሲስ ማረፋቸውን ቫቲካን አስታወቀች።

ወደ ጵጵስናው መንበር ከመምጣታቸው በፊት ካርዲናል ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ በመባል ይታወቁ የነበሩት ጳጳሱ፤ ቀዳሚያቸው ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነበር በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2013 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ የተመረጡት።

ፖፕ ፍራንሲስ ለወራት በሕክምና ላይ በነበሩበት ጊዜ ከአደባባይ ርቀው ከቆዩ በኋላ እሁድ ዕለት በተከበረው የትንሳዔ በዓል በቅዱስ ጴጥሮስ ለተሰበሰበው ምዕመን በአካል ተገኝተው የትንሳዔ በዓል መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

ጳጳሱ ዛሬ ሰኞ ሚያዚያ 13/2017 ዓ.ም. በፋሲካ በዓል ማግስት ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ካዛ ሳንታ ማርታ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በ88 ዓመት ዕድሜያቸው ማረፋቸውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስታውቃለች።

ብጹዕነታቸው ካርዲናል ፋረል በጳጳሱ ሞት ሐዘን ውስጥ ሆነው “የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች፣ የቅዱስ አባታችን ፍራንሲስ ሞትን በጥልቅ ሐዘን አሳውቃለሁ” ሲሉ የጳጳሱን ሕልፈት ይፋ አድርገዋል።

ዛሬ ሰኞ ጠዋት 7:35 ላይ ቫቲካን ውስጥ ማረፋቸውን የጠቀሱት ካርዲናል ፋረል “ፍራንሲስ ወደ አባታቸው ቤት ተመልሰዋል። ሕይወታቸውን ለጌታ እና ለቤተክርስቲያናቸው ሰውተው ነበር” ብለዋል።

አቡነ ፍራንሲስ ከደቡብ አሜሪካ የተሾሙ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጰስ ናቸው።

ግሪጎሪ ሳልሳዊ በ741 ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ለሮማ ካቶሊክ ከአውሮፓ ውጪ ሊቀ ጳጳስ ሲሾም አቡነ ፍራንሲስ የመጀመሪያው ናቸው።በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካውያን መንፈሳዊ መሪ የሆኑት ፖፕ ፍራንሲስ ዜና ዕረፍትን ተከትሎ አዲስ ጳጳስ እስኪመረጡ ድረስ የቤተክርስቲያኗ መሪነት ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ካሪዲናሎች በጋራ የሚካሄድ ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 252 ካርዲናሎች ያሏት ሲሆን፣ የፖፕ ፍራንሲስ ምትክን ለመምረጥ ጉባኤ ሲሰየም ከካርዲናሎቹ መካከል 138ቱ ብቻ ናቸው አዲስ ጳጳስ በመምረጡ ሂደት ድምጽ መስጠት የሚችሉት።

ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ባለፉት ወራት ጤናቸው ታውኮ አምስት ሳምንታትን በሁለት ሳምባቸው ላይ ላጋጠማቸው የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) በሆስፒታል ተኝተው ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ፖፕ ፍራንሲስ በሕይወት ዘመናቸው በ21 ዓመታቸው አንዱ ሳምባቸው በቀዶ ሕክምና እንዲወጣ ያደረገውን ጨምሮ በርካታ የጤና እክል ገጥሟቸዋል።

የጳጳሱ ህልፈት ይፋ መደረጉን ተከትሎ በመላው ዓለም ያሉ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እንዲሁም ታላላቅ የአገራት መሪዎች ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።

የሆላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲክ ስኮፍ “ፖፕ ፍራንሲስ በሁሉም መስኮች የሕዝብ ሰው ነበሩ” ያሉ ሲሆን፣ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ ደግሞ “የሌሎችንም ገጽ የሚያፈካው ፈገግታቸው በመላው ዓለም ሚሊዮኖችን ለመማረክ ችሏል” ብለዋል።

የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይሳክ ሄርዞህ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን “ወሰን የሌለው ርህራሄ” ባለቤት ሲሉ አወድሰዋቸዋል።

የስዊትዘርላንድ ፕሬዝዳንት ካሪል ኬለር-ሱተር ደግሞ ፖፕ ፍራንሲስን “ታላቅ መንፈሳዊ መሪ፣ የማይደክማቸው የሰላም ተከራካሪ” በማለት በህልፈታቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚኒስተር ጆን ስዊኒም በተመሳሳይ ጳጳሱን “የሰላም፣ የመቻቻል እና የዕርቅ” ድምጽ ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ዜና ምንጭ BBC NEWS https://www.bbc.com/amharic/articles/cgkg8j36r14o


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>