በዓውደ ዓመት ገበያ በተለምዶ ‘የሐበሻ’ እና ‘የፈረንጅ’ የሚባሉ ዶሮዎች፣ እንቁላል እና ሌሎችም የምግብ ዓይነቶች እንዲሁም ግብዓቶች በተለያየ ዋጋ ይቀርባሉ።
ሽንኩርት፣ እህል እና ሌሎችም የምግብ ሸቀጦች ‘የሐበሻ’ እና ‘የፈረንጅ’ በሚል ተለይተው ለገበያ ይቀርባሉ።
ሸማቾች እንደየምርጫቸው ከሁለት አንዱን ሲሸምቱ፣ አንደኛው ዓይነት ከሌላኛው በጣዕም እና ለጤና በሚሰጠውም ጥቅምም እንደሚለያዩ ሲናገሩም ይደመጣል።
ለመሆኑ የሐበሻ ዶሮ እና የፈረንጅ ዶሮ እንዲሁም የሐበሻ እንቁላል እና የፈረንጅ እንቁላል ልዩነታቸው ምንድን ነው? ስንል የጠየቅናቸው በዲላ ዩኒቨርስቲ የምግብ ሳይንስና ኒውትሪሽን ተመራማሪ ዶ/ር ይሁኔ አየለ እንደሚሉት ከምርታማነት ጀምሮ ልዩነት እንዳላቸው ያስረዳሉ።
“ሰው በበለጠ የሐበሻ ወደሚባለው ዶሮ እና እንቁላል ነው እያጋደለ ያለው” ይላሉ ባለሙያው።
ኢትዮጵያ በዶሮ እና በእንቁላል አጠቃቀም ከአፍሪካ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ዶ/ር ይሁኔ ጠቅሰው ሕዝቡ “ከዶሮ ሥጋ እና ከእንቁላል ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እያገኘ” እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
በተለምዶ ‘የሐበሻ’ እና ‘የፈረንጅ’ የሚባሉ ዶሮዎች እንዲሁም እንቁላል መካከል ካሉ ልዩነቶች መካከል ምርታማነት፣ የሥነ ምግብ ይዘት እና ጣዕምን ይጠቀሳል።
“ዘራቸው በጥሩ ሁኔታ ያልተዳቀለ እና አመጋገባቸው ጥሩ ያልሆነ የሐበሻ ዶሮዎች ምርታማ አይደሉም። በዓመት ከ30 እስከ 60 ባለው መካከል ነው እንቁላል ሊሰጡን የሚችሉት” ይላሉ ዶ/ር ይሁኔ።
የፈረንጅ ዶሮ ግን ከ300 በላይ እንቁላል ሊሰጡ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።
በአጠቃላይ እንደ አገር ከዶሮ ሥጋ እና እንቁላል “እንደ ማኅበረሰብ ማግኘት ያለብንን ጥቅም እያገኘን አይደለም” ይላሉ።
“የሐበሻ ዶሮ እና እንቁላል የሚመረጠው በምግብ ይዘቱ ወይም በሥነ ምግብ (ኒውትሪሽን) ዋጋው ሳይሆን በባህል ለብዙ ጊዜ ከመጠቀም የተነሳ ነው” ሲሉም ያክላሉ።
በሁለቱ ዓይነቶች መካከል ልዩነት ቢኖርም “ያን ያህል ጉልህ” እንዳልሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ከጤና አንጻር ሲታይ ትክክለኛ የፕሮቲን እና የስብ መጠን ያላቸው የሐበሻ ዶሮዎች እንደሆኑ ጥናቶች ማሳየታቸውን ይጠቅሳሉ።
ከሐበሻ እና ከፈረንጅ እንቁላል እንዲሁም ዶሮ ናሙና በመውሰድ ሰዎች እንዲመገቡ ተደርጎ በተሠራው ጥናት፣ ጣፍጦ የተገኘው የሐበሻ መሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ።
“የሐበሻ የበለጠ ይጣፍጠኛል፣ ይመቸኛል የሚለው ሳይንሳዊ መሠረት ያለው ሆኖ ተገኝቷል” ይላሉ።
ለጤና ከሚሰጡት ጥቅም አንጻር ልዩነት አላቸው?
የዶሮ ሥጋ እና የሌሎችም እንሰሳትን ሥጋ ከሥነ ምግብ ይዘት አንጻር ስንመለከታቸው “የተሰጣቸውን ነው መልሰው የሚሰጡት” ይላሉ ተመራማሪው ዶ/ር ይሁኔ።
በደለበ እና በግጦሽ ሳር ያደገ የቀንድ ከብት መካከል ያለውን የሥጋ ልዩነት እንደማሳያ መውሰድ ይቻላል።
አንድ ሥጋ ጤናማ የሚባለው ብዙ ስብ ሳይኖረው እና የስብ ዓይነቱ እንዲሁም የሥጋው ቅንብር የተሟላና ከፍተኛ ፕሮቲን ያለው መሆን አለበት።
“በሆርሞን ወይም ታስረው የሚያድጉ እንሰሳት ሥጋቸው ጤናማ አይደለም። ወደ ዶሮ ስንመጣ ‘ፍሪ ሬንጅ’ የሚባሉት በነጻ ተለቀው ጭረው የሚለቅሙ፣ የሚንቀሳቀሱ እና አየር የሚያገኙ አሉ። ‘ኬጅድ’ የሚባሉት እንደ ሳጥን አንድ ላይ የተቀመጡት ናቸው” ይላሉ ባለሙያው።
ሳይንቀሳቀሱ የሚያድጉት ዶሮዎች ሥጋቸው በቀላሉ የሚፈረካከስ እና ወደ ሥጋ ደረጃ ያላደገ ወይም ያልፈረጠመ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ከፍተኛ ፕሮቲን እና የተመጣጠነ የቅባት መጠን ያለው እንዲሁም ሲበላ ጣዕም ያለውን መምረጥ ቢያስፈልግ የሐበሻ ተመራጭነት እንዳለው ጠቅሰው “የፈረንጁ ዶሮ አይጠቅምም ማለት ግን አይደለም” ይላሉ።
በሐበሻ እንዲሁም በፈረንጅ ዶሮዎች መካከል አንዳቸው ከሌላቸው ልዩነት እንዳላቸውም ይናገራሉ።

ጭረው የሚለቅሙ፣ የሚንቀሳቀሱ እና አየር የሚያገኙ ዶሮዎች ቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ቢ እና ቫይታሚን ኢ የተሻለ መጠን እንዳላቸው ባለሙያው ያስረዳሉ።
እነዚህ ዶሮዎች እየተንቀሳቀሱ የተለያየ ምግብ ስለሚመገቡ ሥጋቸው ተመራጭ መሆኑንም ያክላሉ።
“ዶሮውን ተልባ ከመገብነው ኦሜጋ 3 ይሰጠናል። አትክልት ካበላነው ካልሽየም ይሰጠናል። ስለዚህ ልዩነቱን የሚያመጣው አመጋገባቸው እና መንቀሳቀሳቸው ነው” ይላሉ ዶ/ር ይሁኔ።
ካለው የሕዝብ ቁጥር አንጻር የሐበሻ ዶሮ እና እንቁላል ማዳረስ እንደማይቻል በመጥቀስም፣ የሐበሻ እና የፈረንጅ የሚለው መከፋፈል ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ይናገራሉ።
“የፈረንጅ ዶሮ እና እንቁላል የበላ ከሐበሻ ዶሮ እና እንቁላል የሚገኘውን ያጣል ማለት አይደለም። የጣዕምና የፍላጎት ጉዳይ አድርገን ብንወስደው ይሻላል” በማለትም ያስረዳሉ።