Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

የሪፖርተር ጋዜጠኛ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ ፍርድ ቤት ወሰነ

$
0
0
ጋዜጠኛ አበበ ፍቅር

ረዕቡ ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለው የሪፖርተር ጋዜጠኛ አበበ ፍቅር፤ በአስር ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና እንዲለቀቀ ፍርድ ቤት ወሰነ። መርማሪ ፖሊስ፤ ጋዜጠኛው “ሁከት እና ረብሻ ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ” እንደተያዘ ለፍርድ ቤት መናገሩን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሳምንት ሦስት ጊዜ በአማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች የሚታተመው የአንጋፋው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢ የሆነው አበበ፤ ዛሬ አርብ ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም. ረፋድ በአዲስ አበባ ከተማ፤ ከተማ ነክ ጉዳዮች ፍርድ ቤት የቀረበው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ጋዜጠኛው ከትናንት በስቲያ ረቡዕ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋለው፤ እያዘጋጀ ለነበረው ዘገባ የልደታ ክፍለ ከተማ ኃላፊዎችን ለማነጋገር በክፍለ ከተማው ቢሮ በተገኘበት ወቅት እንደሆነ ተገልጿል።

እንደ ምንጮቹ ገለጻ ጋዜጠኛው እየሠራ የነበረው ዘጋበ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “በደል ደርሶብናል” የሚሉ ሰዎች በሪፖርተር ጋዜጣ ቢሮ በመገኘት ካቀረቡት ቅሬታ ጋር የተያያዘ ነው።

“[ጋዜጠኛው፤ ቅሬታ ላቀረቡት] ሰዎች ቃለ መጠይቅ ካደረገ በኋላ፤ የቀረበው ቅሬታ ከክፍለ ከተማው ጋር ስለሚገናኝ [እና] የክፍለ ከተማውን ኃላፊዎች የግድ ማነጋገር ስለነበረበት እርሱን ለመሥራት በሄደበት ነው የተያዘው” ሲሉ አንድ ምንጭ ሁኔታውን ገልጸዋል።

አበበ፤ በልደታ ክፍለ ከተማ ቢሮ ከተገኘ በኋላ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ላይ ኃላፊዎችን እንዳላገኘ አሳውቆ እንደነበር የሚገልጹት ምንጩ፤ ወደ ቢሮ እንዲመለስ እና በማግስቱ በአካል ወይም በስልክ ኃላፊዎቹን ለማግኘት እንዲሞክር እንደተነበረው አስረድተዋል።

ጋዜጠኛ አበባ መታሰሩ የታወቀው ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ እንደሆነ ምንጮቹ ተናግረዋል። አበበ መያዙ የታወቀው አካባቢው ላይ የነበሩ ሰዎች ጋዜጠኛው “ወደ ሪፖርት ቢሮ በመደወል በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ እንደሄደ ማየታቸውን” በመናገራቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ይሁንና ጋዜጠኛ አበበ ከተያዘ በኋላ ወደ የት እንደተወሰደ በሰዓቱ እንዳልታወቀ የሚናገሩት ምንጮቹ፤ አበበ በልደታ ክፍለ ከተማ ሥራ በሚገኘው “ጌጃ ሰፈር አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ” እንደታሰረ የታወቀው ትናንት ሐሙስ ጠዋት ገልጸዋል። በትናትናው ዕለት ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ማደሩንም አክለዋል።

ዛሬ ረፋድ በነበረው የችሎት ውሎ ላይ፤ ጋዜጠኛው የታሰረው “በልደታ ክፍለ ከተማ የሥራ አስፈጻሚ ግቢ ውስጥ ሳይፈቀድለት ወይም የሚዲያ ባለሙያ መሆኑን ማስረጃ ሳያቀርብ ሲቀርጽ እና ፎቶ ሲያነሳ” በመገኘቱ እንደሆነ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል ተብሏል።

“ጋዜጠኛ መሆኑን አናውቅም፣ መታወቂያም የለውም” ያለው መርማሪ ፖሊስ፤ ጋዜጠኛ አበበ “ሁከት ለማስነሳት እና ረብሻ ለመፍጠር ሲንቀሳስ” በቁጥጥር ስር እንደዋለ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል። “ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 14 የምርመራ ቀናት” እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረቡንም ምንጮች አስረድተዋል።

ጋዜጠኛ አበበን የወከለው ጠበቃ በበኩሉ፤ “ጋዜጠኛ መሆኑን ማጣራት ይቻላል፤ ደብዳቤ አቅርቡ ተብለንም አቅርበናል” በማለት እንደተከላከለ ተነግሯል።

ጋዜጠኛው “የሠራው ዘገባ ገና ያልተሠራጨ” መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ጠበቃው፤ አበበ በክፍለ ከተማው ግቢ የተገኘው “ሌሎች ሰዎች ላቀረቡት ቅሬታ ሚዛናዊነት የክፍለ ከተማውን ኃላፊዎች ለመጠየቅ” እንደሆነ ገልጿል ተብሏል።

ጠበቃው፤ “ዋስትና ሊያስከለክለው የሚያስችል ምንም ጉዳይ የለም፤ ጋዜጠኛ በመሆኑም ከሕግ እና አዋጁ አንጻር ሊታሰርም አይገባም። ይህም ቢታለፍ እንኳ የዋስትና መብቱ ሊከበር ይገባል” የሚል መከራከሪያ ለፍርድ ቤቱ እንዳቀረበም ምንጮች ገልጸዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ ነክ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ አበበ በአስር ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና እንዲለቀቅ ውሳኔ መስጠቱን ተናግረዋል።

የጋዜጠኛውን የዋስትና ክፍያ የመፈጸም ሂደት ተጠናቅቆ እስከሚለቀቅ እየተጠበቀ መሆኑን የገለጹ አንድ ምንጭ፤ “ይለቀቃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን እስካሁን ድረስ ግን ድረስ ግን አልወጣም” ብለዋል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>