Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

መንግሥት የኮሪደር ልማትን ለጊዜው እንዲገታና ሰዎችን በግዳጅ እንዳያፈናቅል አምነስቲ አሳሰበ

$
0
0
ከፈረሰ ቤት ደጃፍ ላይ የተቀመጡ አዛውንት

የኢትዮጵያ መንግሥት ቢያንስ በ58 ከተሞች እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት በአፋጣኝ አቁሞ በሰብአዊ መብት ላይ የሚያደርሰው ጫና መገምገም እንዳለበት አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች በኮሪደር ልማት ሳቢያ በግዳጅ ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል ሲል ጠይቋል።

ማንኛውም ዓይነት ሰዎችን ከቤታቸው የማስወጣት ሒደት ከዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ጥበቃ መርኅ ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት ሲልም አክሏል።

አምነስቲ ባወጣው ሪፖርት እንደጠቆመው ቢያንስ 872 ሰዎች በአዲስ አበባ በቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች በ2016 ዓ.ም መስከረም ውስጥ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።

ይህ አሐዝ ከ47 ቤቶች የተፈናቀሉ ሰዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 114 ሕጻናት፣ 13 አረጋውያን እና በአጠቃላይ 618 ተከራዮች ይገኙበታል።

“ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተገቢው ውይይት አልተከናወነም፤ በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ አልተሰጣቸውም፤ ተጎጂዎች ካሳም አላገኙም” ይላል የመብት ተከራካሪው ሪፖርት።

“በኮሪደር ልማት ምክንያት ሰዎች ያለ ሕግ ከለላ እና ሌሎች ጥበቃዎች በግዳጅ ከቤታቸው እየተፈናቀሉ ነው” ሲልም ጠቅሷል።

ኮሪደር ልማት በሚካሄድባቸው ከተሞች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤታችን እንፈናቀላለን በሚል በፍርሃት እየኖሩ መሆኑን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ጠቁሟል።

አምነስቲ በዚህ ዓመት ከጥር ወር አጋማሽ እስከ የካቲት መጀመሪያ ድረስ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን እና በቦሌ እንዲሁም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች 47 የቤት ባለቤቶችን ሁኔታ መቃኘቱን በሪፖርቱ ጠቁሟል።

ከኅዳር 2016 እስከ የካቲት 2017 ዓ.ም. በሳተላይት ምሥል አማካኝነት ምልከታ ማድረጉን እንዲሁም በቦሌ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች 29 ሄክታር የሚሆን የተጨናነቀ አካባቢ መፍረሱን አምነስቲ ተመልክቷል።

በሁለቱ ክፍለ ከተሞች በአጠቃላይ የተጎጂዎች ቁጥር በትክክል አልታወቀም። ሆኖም ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

አምነስቲ የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ውጤቱን ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደላከ እና ምላሽ እንዳላገኘ በሪፖርቱ አካቷል።

በሁለቱ ክፍለ ከተሞች አምነስቲ ያነጋገራቸው የ47 ቤቶች ባለቤቶች እንዳሉት ከቤታቸው በግዳጅ ከመፈናቀላቸው ከሳምንት በፊት የአካባቢው የከተማ መስተዳድሮች ለውይይት ጠርተዋቸዋል። ወደ 5,000 ሰዎች በውይይቱ እንደተሳተፉ እና በግዳጅ ከቤታቸው መፈናቀላቸውም ተገልጿል።

በውይይቱ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ የከተማ መስተዳድር ባለሥልጣናት ቤት ለቤት እየዞሩ ቤታቸው ከሦስት ቀናት በኋላ እንደሚፈርስ እንደነገሯቸው ለአምነስቲ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ሁሉም ነዋሪዎች ቤታቸው “ሰነድ አልባ” እንደሆነ እና ካሳ እንዳልተሰጣቸውም ተናግረዋል።

ልጆቻቸው ትምህርት እንዳቋረጡ፣ በቤት ኪራይ እየኖሩ እንደሆነ እና በአጭር ጊዜ የኪራይ ገንዘብ እንደሚያጥራቸው መስጋታቸውን የተናገሩ ነዋሪዎችም አሉ።

ቤታቸውን ከማጣታቸው ባሻገር እንደ እድር ያሉ ማኅበራዊ መደጋገፊያዎችን ባሕላዊ ትስስራቸው ማጣታቸውን በተለይም በሴቶች እና አረጋውያን ላይ የሚያሳድረውን ጫናንም አምነስቲ አትቷል። አንድ አምነስቲ ያነጋገራቸው ነዋሪ “ልጄ የአእምሮ ጤና ችግር ገጥሞታል። በመንግሥት ተስፋ ቆርጠናል” ብለዋል።

ሌላ ነዋሪ “ማኅበራዊ ሕይወቴ ተቆርጧል። የአእምሮ ጤናዬ ታውኳል። ቤት ኪራይ መክፈል ተቸግሬያለሁ” ብለዋል።

ስለ ኮሪደር ልማት ያላቸውን ስጋት የገለጹ ሰዎች እስራት እንደገጠማቸው እና ጋዜጠኞችም ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው መናገራቸውን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አያይዞ አንስቷል።

ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል ያለውን የግዳጅ ማፈናቀል የተቃወሙ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በመንግሥት መያዛቸውንም ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ የፈረመችውን ሰዎች መኖሪያ ቤት የማግኘት መብታቸውን የሚደነግገው ዓለም አቀፍ ሕግ (Universal Declaration of Human Rights) እንዲሁም የካምፓላ ስምምነት (Kampala Convention) ጨምሮ ሌሎችም ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እየተጣሱ መሆናቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት በግዳጅ ከቤታቸው የተፈናቀሉት ሰዎችን ሰብአዊ መብት ጥሷል” ሲልም አክሏል።

አያይዞም የኢትዮጵያ መንግሥት በአፋጣኝ የግዳጅ ማፈናቀልን እንዲያቆም እና የኮሪደር ልማት ሰብአዊ መብት ላይ የሚያደርሰው ጫና እስከሚጠና እንዲሁም ለዜጎች ጥበቃ እስከሚመቻች በጊዜያዊነት እንዲገታ አምነስቲ አሳስቧል።

ዓለም አቀፍ ሕግጋት እንዲከበሩ እና ሰዎችን ከቤታቸው ከማፈናቀል በፊት ያሉ አማራጮች ከግምት ውስጥ እንዲገቡም ጠይቋል።

“ከቤታቸው የተፈናቀሉና ቤት መገንባት የማይችሉ ሰዎች መኖሪያ ቤት ማግኘት አለባቸው። የካሳ እና የመልሶ ግንባታ መብታቸው መጠበቅ አለበት” ሲልም በሪፖርቱ ገልጿል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ከመኖሪያ ቤት ጋር የተያያዘ ልዩ ልዑክ ጉብኝት እንዲያደርግ እንዲፈቀድለትም አምነስቲ ጠይቋል።

የኮሪደር ልማት በዋና ከተማዋ በአዲስ አበባ ተጀምሮ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክልል ከተሞች የተስፋፋ የመልሶ ማልማት ሥራ ሲሆን፣ በተለይ በአዲስ አበባ በርካታ ነባር የመኖሪያ አካባቢዎች ፈርሰው የተለያዩ ግንባታዎች እየተካሄዱባቸው ናቸው።

በዚህ ሂደትም የከተማዋ ነዋሪዎች ወደተለያዩ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ የተደረገ ሲሆን፣ ሂደቱን የሚደግፉ እና የሚያደንቁ እንዳሉት ሁሉ በኮሪደር ልማቱ ተፈናቅለው ለችግር የተዳረጉ ሰዎች በርካታ መሆናቸው እየተነገረ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኅዳር 2017 ዓ.ም. የአዲስ አበባላይ ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በገመገሙበት ወቅት፣ “የአገር ግንባታ” በሂደቱ ወቅት የሚኖሩ ሰዎች “በቀላሉ ተቀብለው፣ ተስማምተው የሚሄዱበት ጉዳይ” እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ አሁን የሚሠራውን ሥራ የሚያደንቁ ሰዎች የሚመጡት “ከተማው የተገነባለት ትውልድ ሲነሳ” ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በአምስት አቅጣጫዎች የሚዘረጋ ሲሆን፣ 40 .7 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ተገልጿል።

የመጀመሪያው ከፒያሳ አራት ኪሎ 8.1 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሲሆን፣ ከአራት ኪሎ፣ በእንግሊዝ ኤምባሲ እስከ መገናኛ ያለውና 9.6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሁለተኛው አካባቢ ነው። ሜክሲኮ፣ ሳር ቤት እና ወሎ ሰፈር ሦስተኛው አካባቢ ናቸው።ከቦሌ፣ መገናኛ እስከ ሲኤምሲ ደግሞ አራተኛው አቅጣጫ ሲሆን፣ 10.5 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። የመጨረሻው ቦሌ፣ እስጢፋኖስ እስከ አራት ኪሎ 3.7 ኪሎ ሜትር የሚያካትት ነው። ይህም የመኪና አስፋልቶች፣ ሰፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መስመሮች እና አረንዴ አካባቢዎችን ይዞ እንደሚገነባ ተገልጿል።

ዜና ምንጭ BBC NEWS https://www.bbc.com/amharic/articles/crm343wvwd8o


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>