በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሚመራው የህወሓት ክንፍ መካከል ያለው መጠዛጠዝ በነባሮቹ የፓርቲው አመራሮች የበላይነት የተቋጨ ይመስላል።
ከሁለት ዓመት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት ቆይታ በኋላ ማክሰኞ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም. አቶ ጌታቸው ረዳ ሥልጣኑን ለምክትላቸው ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ አስረክበዋል።
ቀጣይ መዳረሻቸው በግልጽ ያልታወቀው የቀድሞው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው፤ ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 1/2017 ዓ.ም. ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ አቅራቢ ዋሂጋ ማውራ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።
በዚህ ቃለ መጠይቅ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሲመሩት ስለነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር ስላጋጠሙት ተግዳሮቶች ተናግረዋል። ስለ አዲሱ ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ያላቸውን ግምገማ አጋርተዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንቱ ለየትኛዎቹ ጉዳዮች ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ እና ሊያጋጥማቸው ስለሚችሉ ተግዳሮቶችም ገልጸዋል።
ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ እና ትግራይ ፖለቲካ ውስጥ የቆዩት አቶ ጌታቸው ስለ ወደፊት ተሳትፏቸውም ተናግረዋል። እነሆ ቃለ መጠይቁን
አቶ ጌታቸው ረዳ – በድጋሚ ልንገባበት እንችል የነበረው ጦርነት ተመልሶ እንዳያገረሽ ማድረጋችን እንዲሁም ለለውጥ ያለን ተነሳሽነት እና የሰላም ጉጉትን መጥቀስ እችላለሁ። ማለት የምችለው ይህንን ነው።አቶ ጌታቸው ረዳ – አዎ። ጸጸት ማለት፤ ቀደም ብለን ልናከናውን እንችል የነበራቸው እና ማድረግ የነበሩብን [ጉዳዮች ነበሩ]። ለምሳሌ፣ የተፈናቃዮችን መመለስ። እንደ አለመታደል ሆኖ በትግራይ ውስጥ ያለው ለማይጠቅም ሥልጣን የሚደረግ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ይህንን እንዳንፈጽም አዳጋች አድርጎታል። የሚጸጽተኝ ዋነኛው ተጠያቂ እኔ ስለሆንኩ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ያለንበት ሁኔታ ውስጥ እንድንገባ ያደረገው መጓተት አካል ነበርኩ።
ቢቢሲ- ሥልጣን እንዲለቅቁ ምክንያት የሆነው ዋነኛው ጉዳይ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? ውስጣዊ ፖለቲካ ነው? ወይስ የተፎካካሪ ቡድኖች ናቸው?
አቶ ጌታቸው ረዳ – እየውልህ፤ የፖለቲካ አመራሩ ሂደቱን እና የእኔን አመራር ለማበላሸት ሁሉንም ዓይነት ጥረት ሲያደርግ ነበር። ነገር ግን የፖለቲካ አመራሩ ብቻ አይደለም። ወታደራዊ አመራሩም በሆነ ደረጃ የዚህ አካል ነበር። ዋነኛ ተጠያቂ ባላደርገውም ውስጣዊው የፓርቲ ሽኩቻ መኖርም በአንድ ዓመት ውስጥ ልናሳካ ይገባ የነበሩ እና ማከናወን የነበሩበትን ነገሮችን እንዳንፈጽም አድርጎናል። በሕግ አንጻር ሲታይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን በተቋቀመ በሁለት ዓመት ውስጥ ያበቃል። ስልጣኑን ለማስቀጠል የሚሰጥ ውሳኔም በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል ማለፍ አለበት።
ስለዚህ በዚህ ሂደት ውስጥ የተፈጠረ ማንኛውም ጉዳይ የውስጣዊ የፓርቲ ሽኩቻ እና የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ አለመተግበር ውጤት ነው። በሁለተኛ ደረጃ፤ የፌደራል መንግሥት የአመራር ለውጥ መደረግ እንዳለበት ከተሰማው፤ ይህንን ማድረጋቸው ምክንያታዊ ይመስለኛል። የእኔ መልቀቅ የብዙ ምክንያቶች ውጤት ነው፤ ከሁሉም ዋነኛው ግን የትግራይ ሕዝብ ሕይወት እንዲከብድ ያደረገው የፓርቲ ውስጣዊ ሽኩቻ ነው።
ቢቢሲ -ከሥልጣን የለቀቁት በፈቃደነኝነት ነው ወይ ፓርቲው መጥቶ ለቀጣዩ ምዕራፍ ሲባል እንዲወርዱ ጠይቆዎት ነው?
አቶ ጌታቸው ረዳ – አይደለም፤ የምን ፓርቲ? በህወሓት ውስጥ ያለው አንጃ ይንን ሂደት ሲያበላሽ ነበር። ሁሉንም ዓይነት የጀርባ ድርድር ሲያከናውኑ ነበር። ለፌደራል መንግሥት ይህንንም፣ ያንንም ሲያቀርቡ ነበር። የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት የመሾም ሥልጣን ያላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አይሆንም እያሉ ነበር።
አሁን ግን፤ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌላ አማራጭ ማየታችን ተገቢ ይሆን እንደሆነ ጠይቀውኝ ነበር። እኔ፤ ሥልጣኑን ተጠቅሜ ለምሳሌ እንደ የተፈናቃዮች መመለስ ባሉ ስራዎች ላይ ያከናወንኩት ጥቂት ሆኖ ሳለ፤ ሥልጣን ይዞ የመቀጠል ፍላጎት ያለኝ ሰው አይደለሁም።
ስለዚህ ለእኔ ጉዳዩ፤ [የጊዜያዊ አስተዳደሩ] የሥልጣን ዘመን ሲጠናቀቅ አይቀሬ የነበረ ነው። እኔ በፕሬዝዳንትነት እንድቀጥል ለማድረግ ልዩ የሆነ አሰራር መኖር ነበረበት ማለት ነው። ነገር ግን ለዚያ ሥልጣን ሲታገሉ የነበሩ ማንኛውም አካላት አሁን ካለንበት ቅርቃር ለማስወጣት የሚችል ፈጣን መውጫ መንገድ ገና አላቀረቡም።