Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

ከሦስት ዓመታት በላይ የቆሙ 157 አውቶቡሶች በ67 ሚሊዮን ብር ተጠግነው ሥራ መጀመራቸው ተገለጸ

$
0
0

በተለያዩ ምክንያቶች ከሦስት ዓመታት በላይ ከፍተኛ ብልሽት ገጥሟቸው የቆሙ 157 አውቶቡሶች በ67 ሚሊዮን ብር ወጪ ተጠግነው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የ2017 ዓ.ም. የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ገጥሟቸው የቆሙ አውቶብሶችን በመጠገን ከዚህ በፊት ከነበሩት 991 አውቶቡሶች ወደ 1,140 ማሳደግ ተችሏል፡፡

በዚህ መሠረት ከከተማ አውቶቡስ በቀን ይሰበሰብ የነበረው 3.5 ሚሊዮን ብር ወደ ስምንት ሚሊዮን ብር ማሳደግ እንደተቻለ ሪፖርተር ያገኘው ሰነድ ያስረዳል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አካሉ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተለያዩ ብልሽቶች ምክንያት ከሦስት እስከ አራት ዓመታት ቆመው ለነበሩ እነዚህ አውቶቡሶች 67 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ አውቶቡሶችን ጨምሮ 1,154 አውቶቡሶች ሥራ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ የከተማዋ የአውቶቡስ የትራንስፖርት ድርሻ ከነበረው 28 በመቶ ወደ 34 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ከዚህ በፊት ከነበረው የማመላለስ አቅሙ ወደ 12 በመቶ ማሳደጉን አክለው ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ የአደረጃጀት፣ የአሠራርና የሥነ ምግባር ችግሮችን በጥናት በመለየትና የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት፣ የሰው ኃይል ሪፎርም መደረጉን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

የሪፎርም ሥራው በመከናወኑ የትራንስፖርት ሥምሪቱን ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ የነበሩ ብልሹ አሠራሮችን መቀነስ እንደተቻለ ሰነዱ ያመላክታል፡፡

በመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ 35 የአውቶቡስና የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች፣ 10 ተርሚናሎችና 35 የተሽከርካሪ መቆሚያ መሠረተ ልማቶች በከተማዋ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ ደግሞ በሒደት ላይ እንደሚገኙ ሰነዱ ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የስድስት ወራት አፈጻጸም እንደሚስረዳው፣ መስመር በማቆራረጥ፣ መስመር ባለመሸፈን፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል፣ ከመጠን በላይ በመጫን፣ ታፔላ ባለመለጠፍ፣ ከመስመር ውጪና ከተፈቀደው አገልግሎት ውጪ መመርያ ተግባራዊ ሳያደርጉ የተገኙ አሽከርካሪዎችን በመቅጣት ከ7.5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles