
አሜሪካ ከሰላም ንግግር ያገለሏቸው የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ግብዣ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊያቀኑ ነው።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የዜሌንስኪን ይፋዊ ጉብኝት በኤክስ ገጻቸው ቢያረጋግጡም ቀኑን አልጠቀሱም።
ግብዣው የመጣው አሜሪካ እና ሩሲያ ጦርነቱን በሰላም መቋጨት በሚቻልበት ዙሪያ በመከሩበት በሳዑዲ አረቢያው ጉባኤ ዩክሬን መገለሏን ተከትሎ ነው።ፕሬዚዳንት ራማፎሳ እና አቻቸው ዜሌንስኪ ባደረጉት ውይይት “አስቸኳይ እና ሁሉን አቀፍ የሰላም ሂደት አስፈላጊት” ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ዜሌንስኪ በበኩላቸው “ስለ ዩክሬን ያለ ዩክሬን ምንም የሚሆን ነገር የለም” ማለታቸው ተገልጿል።
አጋርነቷ ከሩሲያ ጋር የጠበቀ ነው የምትባለው ደቡብ አፍሪካ ከዚህ ቀደምም ለጦርነቱ ሰላማዊ እልባት ለመስጠት የበኩሏን ጥረት አድርጋለች።
በአውሮፓውያኑ 2023 ፕሬዚዳንት ራማፎሳ የመሩት ግብፅ፣ ሴኔጋል፣ ዛምቢያ እና ኡጋንዳን ጨምሮ ሰባት አገራትን ያቀፈ የልዑካን ቡድን ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ጋር ተገናኝቷል።ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያ ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ አገራቱ ብራዚል፣ ሕንድ እና ቻይናን ጨምሮ ታላላቅ ምጣኔ ሀብት ያላቸው አገራትን በአባልነት የያዘው ተጽዕኖ ፈጣሪው የብሪክስ ቡድን አባል ናቸው። ፕሬዚዳንት ራማፎሳ “ከፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ጋር ገንቢ የሆነ ንግግሮችን አድርገናል፤ በቅርቡም በደቡብ አፍሪካ የሚኖረውን ይፋዊ ጉብኝት እጠብቃለሁ” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አጋርተዋል።
ዜሌንስኪ በበኩላቸው “ደቡብ አፍሪካ ለዩክሬን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት” እያደረገች ስላለው ድጋፍ ፕሬዚዳንት ራማፎሳን አመስግነዋል። “በዚህ ዓመት ዘላቂ ሰላም እንደምናገኝ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም አክለዋል።ራማፎሳ እና ዜሌንስኪ የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በአካል ጭምር ተገናኝተው ተደጋጋሚ ውይይቶችን አድርገዋል። ሆኖም ዜሌንስኪ በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ፍላጎት ቢኖራቸው እስካሁን ሊሳካ አልቻለም ነበር።
የዩክሬኑ መሪ ከጥቂት ወራት በፊት ደቡብ አፍሪካን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው በዓለም አቀፍ የምግብ ጉባኤ ላይ ከአፍሪካ ጋዜጠኞች ጋር በተገናኙበት ወቅት መናገራቸውን የደቡብ አፍሪካው የዜና ድረገጽ ኒውስ 24 ዘግቧል።
“በፕሪቶሪያ መገኘት ደስታዬ ነው። ነገር ግን ራማፎሳን መጠየቅ አለባችሁ። ሥራ የበዛበት ይመስለኛል” ሲሉ ዜሌንስኪ መናገራቸውን ኒውስ 24 አክሎ አስነብቧል።
ዜሌንስኪ ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር እያደረጉት ያለው ውይይት እንደ ቁልፍ አጋር ከሚቆጥሯት አሜሪካ ጋር ውጥረት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬኑን መሪ “መጥፎ ሥራ የሠራ አምባገነን” ሲሉ መወረፋቸውን ተከትሎ ውዝግቡ መክረሩን ያሳየ ሆኗል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያላቸው ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ ሻክሯል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ያጸደቀችው የመሬት ፖሊሲ በተወሰኑ “ማኅበሰረሰቦች” ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ለአገሪቱ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ መዛታቸው ይታወሳል።
ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታድ ሥርዓት ማብቃት ከ30 ዓመታት በኋላ አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬቶች በጥቂት ነጮች እንደተያዘ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው በሚል በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የከሰሰቻት ሲሆን፣ ክሱ በጦር መሳሪያ ጭምር እየደገፈቻት ያለችውን አሜሪካን አስቀይሟል።