
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዲስ ዘረጋሁት ባለው የኢ-ፓስፖርት ሲስተም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሚስጥራዊ ህትመትና ቴክኖሎጂ ልምድ አለው ከተባለው የጃፓኑ ቶፓን ሴኩሪቲ ኢትዮጵያ አ.ማ አማካይነት ዘመኑ በደረሰበት የሚስጥራዊ ህትመት የታተመ አዲስ ፖስፖርት ዛሬ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም ይፋ እያደረገ ነው፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በፓስፖርት ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ይፋ መደረጉ ይታወሳል። ቀደም ሲል 2 ሺህ ብር ይጠየቅበት የነበረው የአዲስ ፓስፖርት ክፍያ በአዲሱ የዋጋ ማሻሻያ 5 ሺህ ብር (50 የአሜሪካ ዶላር) መሆኑን አስታውቋል። በአስቸኳይ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ይጠየቅ የነበረው 5 ሺህ ብር ደግሞ ወደ 20 ሺህ ብር (200 ዶላር ገደማ) ከፍ ማለቱን አገልግሎቱ አስታውቋል።እንደ አገልግሎቱ መረጃ ከሆነ ፓስፖርቱ ዕድሜ ኖሮት እርማት ለማግኘት ለፈጣን አገልግሎት 40 ሺህ 500 ብር ያስከፍላል።በተመሳሳይ ለጠፋ ፓስፖርት በሁለት ቀን እርማት ለማድረግ የአገልግሎት እስከ 40 ሺህ 500 ብር (450 ዶላር) እንደሚያስከፍል አስታውቋል።በውጭ አገር ሆነው መደበኛ ፓስፖርት በኤምባሲ በመደበኛ ጊዜ የሚጠይቁ ኢትዮጵያዊያን 200 ዶላር ይከፍላሉ። በአስቸኳይ (በ15 ቀናት) ለማግኘት ደግሞ 350 ዶላር ይጠየቃል።ዛሬ ይፋ ይደረጋል የተባለው ፓስፖርት በሀገር ውስጥ የሚታተም በመሆኑ በውጪ ምንዛሬ ሲደረግ የነበረውን የህትመት ወጪ ይቀንሰዋል ተብሏል።