
ባለፉት ሁለት ወራት ከ75 በመቶ በላይ ሠራተኞች ከሥራ የተሰናበቱበት በአማራና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ ሥፍራ ላይ የሚገኘው የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካን፣ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መልሶ ሥራ እንዲጀምር ለማድረግ አዲስ ቦርድ ተቋቋመ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲስ የተቋቋመው ቦርድ እስከ ግንቦት ወር 2017 ዓ.ም. ድረስ ሁለት ሺሕ ሔክታር መሬት ለማልማት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ 450 ሔክታር መሬት ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።
‹‹ለፋብሪካው የራሱ ቦርድ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ለመመለስ እየተሠራ ነው። በተቻለ መጠን የፋብሪካው ዕቅድ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ መመለስ ነው። እስካሁን በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቷል፡፡ አሁን ግን ዕቅድ ይዘን እየሠራንበት ነው፤›› ሲሉ ብሩክ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር በ225 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የስኳር ፋብሪካው ከጥር ወር 2017 ዓ.ም. በኋላ ለአራት ወራት የተጠራቀመ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ሲጠባበቁ ከቆዩ ሠራተኞቹ መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከሥራ መሰናበታቸውን፣ በዚህም ምክንያት የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ በዋናነት በአስተዳደርና በእርሻ የተሰማሩ 421 ሠራተኞች በሥራ ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።
ሠራተኞቹ በሰላማዊ ሠልፍ የደመወዝ ጥያቄያቸውን ለፋብሪካው አስተዳደር ሲያቀርቡ አመራሮች፣ ‹‹ትርምስ ለመፍጠር በመሞከር›› በሚል ምክንያት ለመንግሥት የፀጥታ፣ ኃይሎች ወደ ቅጥር ግቢው መጥተው ዕርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ማድረጋቸውን፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሠራተኞቹ ‹‹አስፈሪ›› ሲሉ በገለጹት በታንክ ጭምር ከበባ ተደርጎባቸው እንደነበር መናገራቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።
ጉዳዩን በተመለከተ በወቅቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ብሩክ (ዶ/ር) ሥራቸውን ያቆሙት ሠራተኞች ወደ ተለያዩ ፋብሪካዎች ተመድበው እየሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ ያልተከፈላቸው የተጠራቀመ ደመወዝም እንዲሰጣቸው ቃል መገባቱን ጠቅሰው ምላሽ ሰጥተው ነበር።
ብሩክ (ዶ/ር)፣ ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ጉዳዩ ስለደረሰበት ደረጃ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር ከሚገኙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ፣ ከገባበት ችግር እንዲወጣ ለማስቻል፣ በአሁኑ ጊዜ በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር ከሚገኙትና መንግሥት ወደ ግሉ ዘርፍ በተለያዩ መንገዶች ለማዘዋወር ጥረት እያደረገባቸው ካሉት ፋብሪካዎች መካከል ተነጥሎ ለብቻው ቦርድ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
ብሩክ (ዶ/ር) አያይዘውም መንግሥት አሁንም የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ባለሀብቶች ለማዘዋወር በተለያዩ መንገዶች እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል በአፍሪካ ግንባር ቀደም ከሆነው የዳንጎቴ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሊኮ ዳንጎቴ ጋር በቅርቡ በተደረገ ውይይት፣ ድርጅቱ በስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሰማራ ለማድረግ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት በኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ቁጥር ሦስት ዳንጎቴ ግሩፕ የማስፋፊያ ሥራዎችን አከናውኖ በዘርፉ እንዲሰማራ ለማድረግ በቅድሚያ በፋብሪካው ላይ ጉብኝትና ግምገማ ለማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክረ ሐሳብ (Proposal) እንዲያቀርብ ከተደረገ በኋላ ስለኢንቨስትመንት ሁኔታው ለመወያየት ከስምምነት መደረሱንም አስታውቀዋል።