
ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ለሁለት የተከፈለው አመራር ‹‹በችግሮቻችን ላይ ለመደራደር›› ያስችለናል ያለውን የሥነ ምግባር ሰነድ ከተፈራረመና የነበረውን ልዩነት በንግግርና በውይይት ለመፍታት ስምምነት ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ ስምምነቱ አንድ ሳምንት ሳይሞላው አፍርሶ፣ የድርጅቱን 50ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓል በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ባልተገኙበት ማክበር ተገለጸ። በዋናነት ከፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ክልላዊ፣ እንዲሁም ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ስለሚኖረው የሥራ ግንኙነት የተመለከቱ፣ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለወራት ለሁለት ተከፍሎ ሲወዛገብ የከረመው፣ በሊቀመንበሩ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ቡድኖች፣ የውዝግብ መነሻ ችግሮችን በውይይትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የተደረገው ስምምነት መፍረሱ በክብረ በዓሉ ዋዜማ፣ በአስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ይፋ በተደረገ መግለጫ ነበር የታወቀው። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ሰኞ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት ይፋ ባደረገው መግለጫ፣ ባለፉት ሳምንታት በክልሉ የሃይማኖት አባቶች አሸማጋይነት በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ሕወሓትና በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ልዩነቶቻቸውን በከፊል ወደ ጎን በማድረግ፣ የየካቲት 11 50ኛ ዓመት የተመሠረተበትን በዓልና የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን በጋራ በመታደም አብሮ ለመሥራት ከስምምነት ተደርሶ እንደነበር ገልጿል፡፡
በተጨማሪም አስተዳደሩ በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የፕሪቶሪያ ስምምነት ግምገማ ወቅት በጋራ ተገኝተው አቋማቸውን ማንፀባረቃቸውን በማስታወስም፣ በዓሉን ለማክበር የተዋቀሩት የሁለቱም ቡድኖች ኮሚቴዎች በጋራ እንዲሠሩ ከስምምነት ተደርሶ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
ይሁን እንጂ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ‹‹ከራሱ ሥልጣን ውጪ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ግድ የማይሰጠው ቡድን፣ የተጀመረውን የሰላም መንገድ በማናጋት ሆን ብሎ ሕዝብን ወደ ሁከትና ግጭት ለማስገባት እየሠራ እንደሆነ ደርሼበታለሁ፤›› ብሏል፡፡
በዚህም ምክንያት የሕወሓት 50ኛ ዓመት በዓል በጋራ ለማክበር የነበረው ዕቅድ በቡድኑ በመጨናገፉ፣ የካቲት 10 እና የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የተያዙትን በዓሉን የተመለከቱ መርሐ ግብሮች መሰረዙንና በራሱ መንገድ በዓሉን ለማክበር መወሰኑን አስታውቋል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ ‹‹በዓሉን አስመልክቶ በሚተኮስ ርችት አሊያም ተቀጣጣይ ነገር ሳቢያ የሚፈጠር አደጋ ካለ ቡድኑ ተጠያቂ ይሆናል፤›› ሲል፣ በመግለጫው በማስታወቅ፣ ሕዝቡ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሁለቱ የሕወሓት ቡድኖች ከአንድ ወር በፊት ተፈራርመው የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ ባደረጉት የሥነ ምኅባር ደንብ ሰነድ መሠረት፣ ከስምምነት የተደረሰባቸው አምስት ዋና ዋና አንቀጾች መካከል፣ የፖለቲካ ግቦችን ለማሳካት የኃይል ዕርምጃን አለመውሰድ፣ ጥላቻና ጥቃትን ከሚቀሰቅሱ ንግግሮች መቆጠብ፣ ማስፈራራትንና ጥቃትን መከላከል የሚሉት እንደሚገኙበት ይታወሳል።
ይሁንና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የሃምሳ ዓመት ዕድሜ ባስቆጠረው ሕወሓት የምሥረታ በዓል ዋዜማ የተደረገው ስምምነት፣ በሊቀመንበሩ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በሚመራው ቡድን መጣሱን አሳውቋል፡፡
ትናንት ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የክልሉ ዋና ከተማን መቀሌ ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የፓርቲው ሃምሳኛ ዓመት ምሥረታ ሲዘከር፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በዝግጅቶቹ ላይ ሳይሳተፉ መቅረታቸው ታውቋል።
ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ምክትል ሊቀመንበሯ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ) እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ያሉበት የሕወሓት ቡድን፣ በመቀሌ ከተማ ሰማዕታት ሐውልት ቅጥር ግቢ በመገኘት፣ ለሰማዕታት የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓትን ጨምሮ፣ በተለያዩ መንገዶች የምሥረታ በዓሉን ሲዘክሩ፣ በአስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው የሚመራው የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ሳይገኙ ቀርተዋል።