
በሰዎች አፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ባክቴሪያዎች ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ከአእምሮ ሥራ ለውጥ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ተመራማሪዎች ተናግረዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ኤክሰተር ዩኒቨርሲቲ የተሠራው ጥናት እንደሚያመለክተው አንዳንድ የባክቴሪያ ዓይነቶች ከተሻለ የማስታወስ ችሎታ እና ትኩረትን ጋር የሚዛመዱ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ከአእምሮ ጤና መጓደል እና ከመርሳት (አልዛይመር) በሽታ ጋር የተገናኙ ናቸው።
የጥናቱ መሪ ዶ/ር ጆዋና ኤል ሄሬክስ “አንዳንድ ምልክቶች ከመታየታቸው በፊት ወይም አንድ ታካሚ ለምርመራ ወደ ሐኪም ከመሄዱ በፊት የአልዛይመር ‘ጂን’ መኖር እና አለመኖሩን መተንበይ እንችል ይሆናል” ይላሉ።
ጥናቱ ገና ጅማሮ ላይ ቢሆንም ሙያተኞች አንዳንድ በናይትሬት የበለጸጉ ጤናማ የሆኑ ቅጠላ ቅጠሎች መመገብ ባክቴሪያን በማሳደግ የአንጎል ጤና ላይ ሊያሳድረው ስለሚችለው ተጽእኖ እየተመራመሩ ይገኛሉ።
ጥናቱ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ፕሮፌሰር አን ኮርቤት “የእኛ ጥናት አንድምታ ጥልቅ ነው” ይላሉ። ፕ/ሮፌሰር አን “አንዳንድ ባክቴሪያዎች የአንጎልን ተግባር የሚያደግፉ ሌሎች ደግሞ እንዲያሽቆለቁል አስተዋጽኦ የሚያደርጉ” እንደሆኑ ያብራራሉ።
ጨምረውም “በአፍ ውስጥ ያለውን የባክቴሪያ ሚዛን የሚቀይሩ ህክምናዎች የመርሳት በሽታን ለመከላከል የመፍትሄ አካል ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ ያክላሉ።
“ይህ የሚሆነው የአመጋገብ ለውጥ በማድረግ፣ በፕሮባዮቲክስ፣ የአፍ ንፅህናን በመጠበቅ፣ ወይም ደግሞ በታቀዱ ህክምናዎች ሊሆን ይችላል።”
ከዚህ በፊት በተካሄደ አንድ ጥናት ዕድሜያቸው ከ50 ያለፈ 115 በጎ ፈቃደኞች የግንዛቤ (cognitive) ፈተናዎችን እንዲወስዱ ተደርገዋል።
ተመራማሪዎቹ የጥናቱን ተሳታፊዎች መለስተኛ የግንዛቤ ችግር ያለባቸው እና ምንም ዓይነት ችግር የሌለባቸው በሚል በሁለት ቡድኖች ከፈለዋቸዋል።
የሁለቱም ቡድኖች ተሳታፊዎች አፍን በመጉመጥ ሂደት ውስጥ እንዲያልፉ ከተደረገ በኋላ ናሙናው እንዲተነተን እና ተህዋሲያኑ እንዲጠኑ ተደርገዋል።
ኒሴሪያ እና ሄሞፊለስ የተባሉት የባክቴሪያ ቡድኖች ብዛት ያላቸው ሰዎች የተሻለ የማስታወስ እና ውስብስብ ተግባራትን የመሥራት ችሎታ እንዳላቸው ጥናቱ አሳይቷል።
ይሁን እንጂ ዶ/ር ጆዋና የማስታወስ ችግር ባለባቸው ግለሰቦች ላይ ፖርፊሮሞናስ የተባለውን የባክቴሪያ መጠን በብዛት እንደተገኘ ተናግረዋል።
ፕሬቮቴላ የተባለው የባክቴሪያ ቡድን ከአነስተኛ ናይትሬት ጋር የተገናኘ ሲሆን፣ ይህም የአልዛይመር በሽታ ስጋት ባለባቸው ሰዎች ላይ በጣም የተለመደ ነበር ብለዋል።
ተመራማሪዋ “እንደ ቀይ ሥር፣ ጎመን፣ ሰላጣ እና የመሳሰሉ ቅጠላ ቅጠሎች ያሉ ምግቦችን እንዲመገቡ፤ አልኮል እና የተቀነባበሩ ጣፋጭ ምግቦችን እንዲቀንሱ እንመክራለን” ሲሉ አክለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ምክትል ቻንስለር እና የምርምር ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አኒ ቫንታሎ “ወደፊት እነዚህን [የአፍ] ናሙናዎች በጠቅላላ ሐኪም ቀጠሮ ወቅት እንሰበስባለን እና አንድ ሰው ከፍ ያለ አደጋ ላይ ከሆነ ቀድሞ እንዲጠቁም ልናደርግ እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።