
በካናዳዋ መዲና ቶሮንቶ ሰኞ፣ የካቲት 10/ 2017 ዓ.ም በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ተሳፍረው ለነበሩ ለእያንዳንዱ መንገደኞች 30 ሺህ ዶላር ሊሰጣቸው እንደሆነ ተገለጸ።
ንብረትነቱ የአሜሪካ የሆነው የዴልታ አየር መንገድ አውሮፕላን በደረሰበት አደጋ ህይወት ባይጠፋም ለተሳፋሪዎቹ ገንዘብ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
አውሮፕላኑ በካናዳዋ ከተማ እንዳረፈ ወደ ጎን ተንሸራቶ በእሳት ከተያያዘ በኋላ ተገልብጦ መቆሙ ተገልጿል።
አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው መቅረቱ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።
የአደጋው መንስዔን በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ ሲሆን እስካሁን ድረስ ይፋ የሆነ ነገር የለም።
አራት የበረራ ሰራተኞችን እንዲሁም 76 ተሳፋሪዎችን ጭኖ የነበረው አውሮፕላን ከአሜሪካ የሚኒያፖሎስ ከተማ ወደ ካናዳ እየተጓዘ ነበር።
የዴልታ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ለተሳፋሪዎቹ የሚሰጠው ገንዘብ ከምንም ጋር ያልተያያዘ እንዲሁም የደንበኞችን መብት የሚነካ አይደለም ብለዋል።
አደጋ ከደረሰበት አውሮፕላን ውስጥ ተሳፋሪዎችን በፍጥነት በማስወጣት ለሰሩት ተግባር የአውሮፕላኑ ሰራተኞች እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪዎች ምስጋና ተችሯቸዋል። በአደጋው ህይወት ላለመጥፋቱ በአውሮፕላኑ የተገጠሙ ልዩ የደህንነት መሳሪያዎች እንደ ምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
ወደ ሆስፒታል ተወስደው ከነበሩት 21 መንገደኞች ውስጥ ከአንደኛው በስተቀር ሁሉም እስከ ረቡዕ ማለዳ ድረስ መውጣታቸውን አየር መንገዱ አስታውቋል። የአየር መንገዱ ዋና ኃላፊ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት የበረራ ሰራተኞቹ ልምድ ያላቸው እና ማንኛውንም ሁኔታ እንዲቆጣጠሩ ሆነው የሰለጠኑ ናቸው ብለዋል።
ዋና ኃላፊው ኤድ ባስቲያን ለሲቢኤስ እንደተናገሩት የአውሮፕላኑ ሰራተኞች “እንደተጠበቀው ተግባራቸውን በጀግነት ተወጥተዋል። ሆኖም የአውሮፕላን ስርዓታችን የተለያዩ ደህንንቶች የተገጠመለት ነው” ብለው በአደጋው የተጎዱትን መንገደኞች በመደገፍ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የአደጋውን ቪዲዮ የገመገሙ ባለሙያዎች የአደጋውን መንስዔ በተመለከተ በርካታ ንድፈ ሃሳቦችን ለቢቢሲ አቅርበዋል። ከነዚህም ውስጥ አንደኛው አስቸጋሪው የክረምት የአየር ጠባይ እንዲሁም አውሮፕላኑ በፍጥነት ወደታች ያረፈበት መሆኑ ተጠቅሷል።
አንድ ተሳፋሪ የአውሮፕላን አደጋውን “በጣም ኃይል የተቀላቀለበት ክስተት” መሆኑን ገልጸው ሲወርድ ድምጹም “የብረት እና ድንጋይ” እንደነበር ያወሳሉ። ሌላኛው መንገደኛ በበኩላቸው ተሳፋሪዎች “እንደ የሌሊት ወፍ ተገልብጠው” እንደነበር አስረድተዋል።
በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው አውሮፕላኑ በተገለበጠ ወቅት በአየር ማረፊያው አነስተኛ የሚባል የበረዶ ብናኝ እየወረደ ነበር።
የአደጋውን መንስዔ የካናዳ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር የሚያካሂዱት እንደሆነ ተገልጿል።
በሰሜን አሜሪካ ባለፈው አንድ ወር ብቻ አራት ትላልቅ የሚባሉ የአውሮፕላን አደጋዎች ተከስተዋል።
በአሜሪካዋ ዋሺንግተን ዲሲ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን ከጦር ሄሊኮፕተር ጋር ተጋጭቶ 67 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።