የፌዴራል መንግሥት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከሚገኙ የፋኖና የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጎ፣ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካይነት እንዲመክር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ፡፡ የፓርላማ አባላቱ ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት የሦስት ዓመት የሥራ ጊዜውን ያጠናቀቀውን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የሦስት ዓመታት አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ፣ ትናንት ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ምክር ቤቱ ባደረገው 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ነው፡፡ ከ288 በላይ የፓርላማ አባላት በተገኙበት የስብሰባ ውሎ ቀርበው ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ በአማራ ክልል ባለው ግጭት የተነሳ ሥራው አለመጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ በትግራይ ክልል በሕወሓት ሁለት ቡድኖች መካከል አለመግባባት ሳቢያ የተሳታፊ ልየታና ምክክር አለመደረጉንም ተናግረዋል፡፡የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ በገዥው መንግሥት በኩል ጉዳዮችን በጦርነት ለመፍታትና ለውይይት ዝግጁ ነኝ ብሎ፣ ለሰላማዊ የውይይትና የምክክር ሒደት ለማካሄድ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹ሁለቱንም የማጣቀስ ችግር አያለሁ፤›› ብለዋል፡፡ በመንግሥትና በታጣቂ ኃይሎች በተለይም በፋኖና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የምክክር ሒደቱ እስኪሞከር ድረስ፣ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ኮሚሽኑንም ይህንን በግልጽ ሊያቀርብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የፓርላማ ተወካይ አቶ ባርጢማ ፈቃዱ በበኩላቸው፣ ኦሮሚያ ክልል ውይይቱ ተካሄደ ተብሎ ቢነገርም ሥራው ተከናውኗል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ምክክሩ እንዲሳካ አጀንዳ አለን የሚሉ ጫካ የገቡ ሰዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ የምክክር ኮሚሽኑ መንግሥትን በመግፋት የተኩስ አቁም ስምምነት ተካሂዶ፣ መጥተው ሊወያዩ ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በትጥቅ ትግል የሚሳተፉ ድርጅቶችና ቡድኖች ለግላቸው ሳይሆን እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ በመኖሩ እንታገላለን ነው የሚሉት ብለዋል፡፡ ነገር ግን ታጥቀው ትግል የሚያካሂዱ ሰዎች የሚወክሉት ሕዝብ ቢኖርም፣ በኦሮሚያ ያልተሳተፈ ወረዳ እንደሌለ ጠቅሰው፣ በአማራ ክልልም ስምንት ወረዳዎች ብቻ እንደቀሯቸው ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል የአጀንዳ መሰብሰብና ክልላዊ ምክክር ሒደትም በቅርቡ እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡በአገሪቱ ከአጠቃላይ 1,232 ወረዳዎች ውስጥ 100 ወረዳዎች እንደሚቀሩት የገለጹት ዋና ኮሚሽነር መስፍን (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ተኩስ ይቁም ከተባለ ከሁሉም ወገን መቆም አለበት፡፡ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ ወደኋላ መቅረት የለበትም፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት ከታጣቂዎች ጋር ተኩስ አቁሞ ውይይትና ምክክር ይደረግ የሚለውን ‹‹ምክር ቤቱ ይዞት እንደሚሄድ ተስፋ አለኝ፤›› ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ይህንን ሐሳብ በየቦታው ያሉት ይሰሙታል ብዬ አስባለሁ፣ አስቻይ ሁኔታው በጣም ወሳኝ ነው፣ ይህንን የምንደግፈው ነው፤›› ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የሥራ ዘመን ለአንድ ዓመት ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በሦስት ተቃውሞ በአብላጫ ጽምፅ አፅድቋል።