Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 938

ፍርድ ቤት ‹‹የሕግ መሠረት የለውም›› ባለው ግብር ማስከፈያ መመርያ ላይ ከተማ አስተዳደሩ ምላሽ ሰጠ

$
0
0

       ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

  • በአዲስ አበባ ካሉ 800‚000 ሕንፃዎችና ቤቶች ግብር የሚከፍሉት 120‚000 ብቻ መሆናቸው ተገልጿል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ የጣሪያና ግድግዳ ግብር ለማስከፈል ተግባራዊ ያደረገው መመርያ ‹‹የሕግ መሠረት የለውም›› ብሎ ላሳለፈው ውሳኔ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‹‹በሚገባ ሥልጣን አለው›› ሲል ምላሽ ሰጠ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ በከተማው ፋይናንስ ቢሮ በኩል ተግባራዊ የተደረገው፣ የጣሪያና የግድግዳ ግብር መመርያ አወጣጥ ‹‹መርሆዎችን ያልተከተለ ነው›› ተብሎ በፍርድ ቤት መሻሩን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ‹‹ከሕጉ አንፃር ፍርድ ቤት ወስኗል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤት ሁሌ ትክክል ቢወስን ኖሮ፣ ይግባኝም ቀጥሎ ያሉ ክርክሮችም ባልኖሩ። ነገር ግን የከተማ አስተዳደሩ በሚገባ ሥልጣን አለው፤›› በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጣሪያና ግድግዳ ግብር ተግባራዊ በመደረጉ ምክንያት እናት ፓርቲ ‹‹ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው›› በማለት በከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ ቢሮ ላይ ክስ መሥርቶ ሲከራከር ከቆየ በኋላ ጉዳዩን ሲመለከተው የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጣሪያና የግድግዳ ግብር ተግባራዊ እንዳይደረግ ቢወስንም፣ የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ ማክሰኞ ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ግብር ከፋዮችን ያለ ቅጣትና ወለድ የሚያስከፍልበት ጊዜ እየተጠናቀቀ መሆኑን በመጥቀስ፣ ግብሩን እንዲከፍሉ ማሳሰቢያ ማውጣቱንና በዚህም መነሻነት ነዋሪው ‹‹መፈጸም ያለበት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ወይስ የገቢዎች ቢሮ ማሳሰቢያ?›› የሚል ጥያቄ እያነሳ መሆኑን መዘገባችንም አይዘነጋም።

ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም. አራተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔውን  ባካሄደበት ወቅት፣ የምክር ቤቱ አባል ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ጉዳዩን አስመልክቶ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ‹‹ከቤት፣ የጣሪያና ግድግዳ ግብር ጋር ተያይዞ ምጣኔ (Rate) አልጨመርንም፣ ሠንጠረዡም በአንድ ካሬ ሜትር ተሠልቶ የሚሰጠው ምጣኔ ያው ነው። ለምክር ቤቱም ይህንን ጥያቄ ለሚጠይቁ የከተማችን ነዋሪዎችም ግልጽ እንዲሆን የተቀየረው የኪራይ መጠኑ ነው፤›› ብለዋል።

በተጨማሪም ከንቲባዋ በ1968 ዓ.ም. ይህ ሕግ ሲወጣ አንድ ካሬ ይከራይበት የነበረው ዋጋ ዛሬ ላይ አይከራይበትም ብለው፣ ‹‹ያኔ አሥር ብር የነበረው ዛሬ 300 ወይም አምስት መቶ ወይም አንድ ሺሕ ብር ደርሷል። የአንድ ካሬ ግብር ክፍያ የሚሰላበት መጠን ያው ነው፣ ነገር ግን ቤቱ የሚከራይበት ገንዘብ መጠን ስለተቀየረ ሥሌቱን አሁን በተቀየረው የገንዘብ መጠን ብቻ ነው ያደረግነው። ይኼ ነው ለውጡ ሌላ ለውጥ የለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

ወ/ሮ አዳነች፣ ‹‹በየጊዜው የማይከፍሉ የግብር ሥርዓቱ ውስጥ ያልነበሩ ብዙ ናቸው›› ያሉ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ወደ 800,000 የሚጠጉ ሕንፃዎችና ቤቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ግብር የሚከፍሉት ግን 120,000 ብቻ ነበሩ ሲሉ ወቅሰዋል።

‹‹ይህ የግብር ሥርዓቱን ያዛባዋል፣ ኢ ፍትሐዊነትን ያነግሣል። ትልልቅ ሕንፃዎች ያላቸው አይከፍሉም፣ ደሳሳ ጎጆ ያላቸው የከተማችን ነዋሪዎች ግን ይከፍላሉ። ከ1968 ዓ.ም. እስከ 1970 ዓ.ም. ድረስ ባለው የግብር ሥርዓት ውስጥ የገቡት 120,000 የሚደርሱት ነዋሪዎች ይከፍላሉ፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ትልልቅ ሕንፃና ቤቶች የገነቡ አይከፍሉም። ጭቃ ቤቶች ይከፍላሉ፣ በብሎኬትና በዘመናዊ መሣሪያ የገነቡ አይከፍሉም። እንደዚህ ዓይነት ሥርዓቶች ናቸው የተስተካከሉት፤›› ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

ከንቲባዋ በገለጻቸው በተደጋጋሚ በካሬ ሜትር የሚከፈለው የግብር ምጣኔ መጠን እንዳልተቀየረ የገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን አንድ ቤት በጭቃም ይሁን በብሎኬት ወይ በእንጨት የተሠራ ይሁን፣ በዚያን ዘመን ይከራይበት የነበረው የማከራያ ዋጋና የዛሬው ዘመን ዋጋ ስለሚለያይ፣ በከተማ አስተዳደሩ የሚመለከተው ቢሮ አሁን በገበያው ላይ ያለውን ዋጋ ጥናት ማድረጉን አስታውቀዋል።

‹‹አጥንተን ትክክለኛ የአሁኑን ዋጋ በሚመጥን የግብር ምጣኔ ክፍያውን ካመጣነው በአንድ ጊዜ ለውጡ ለከፋዮች ከባድ ሊሆን ይችላል በሚለው ስለወሰንን፣ ለመኖሪያ ቤት ሲሆን አሁን ከሚያወጣው ዋጋ 50 በመቶ ብቻ ነው ያስከፈልነው። ንግድ ቤቶች ሲሆኑ ደግሞ የአሁኑን ዋጋ 75 በመቶ ነው እንዲከፍሉ የተደረገው። ይህም ማለት አንድ ሕንፃ በአሁኑ የገበያ ጥናት መሠረት አንድ ሚሊዮን ብር የሚከራይ ከሆነ፣ የአንድ ሚሊዮኑን 75 በመቶ ብቻ ነው ግብር እንዲሰላበት ያደረግነው፤›› ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከግብር ምጣኔ ስሌትና የካሬ ሜትር ዋጋ ኪራይ ክፍያ በዘለለ፣ ጥያቄዎችን ስላስነሳው የቤት፣ የጣሪያና ግድግዳ ግብር መመርያ ሕጋዊነት በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም፣ ‹‹ከሕጉ አንፃር ፍርድ ቤት ወስኗል ላሉት፣ ፍርድ ቤት ሁሌ ትክክል ቢወስን ኖሮ ይግባኝም ቀጥሎ ያሉ ክርክሮችም ባልነበሩ። ነገር ግን ከተማ አስተዳደሩ በሚገባ ሥልጣን አለው። ሥልጣኑም በአዋጅ ቁጥር 80/1968 አንቀጽ 9፣ ንዑስ አንቀጽ አንድና ሁለት ላይ መመልከት እንችላለን፤›› ብለዋል።

ከንቲባዋ አስከትለውም የንዑስ አንቀጾቹን ይዘት ለምክር ቤቱ በንባብ አሰምተዋል። በንባባቸውም፣ ‹‹በንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከሥራና ቤት ሚኒስትር ጋር በመመካከር ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስችል ደንብ ያወጣል፤›› ይላል ሲሉ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን ሲሰጡም ‹‹ደንቡንም እኛ ሳንሆን 1968 ነው በዚያኑ ወቅት አዲስ አበባ መስተዳደር ያወጣው፤›› ብለዋል።

በተጨማሪም፣ ‹‹ደንቡም ሆነ አዋጁ የደንቡን ድንጋጌዎች ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን የሥሌት ሠንጠረዥ ተያያዥ ሲያደርግ ደግሞ፣ የቤቶችን የኪራይ ዋጋ በየዓመቱ እያጠና ማስተካከል ይችላል ይላል። ምንም የሚያሻማ ትርጉም የሚያስፈልገው ነገር የለም፤›› በማለት አስረግጠው ተናግረዋል።

ሕጉ በቅርቡ በፀደቀው የንብረት መሠረት አዋጅ የሚተካ እንደሚሆን የገለጹት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች፣ ‹‹እኛ ግን እስካሁንም የሚያስቆመንም አካል የለም፣ ተወስኖብን ግብር አትሰብስቡ ያለንም የለም። ግብር እየሰበሰብን ነው ያለነው፣ አብዛኛውም ግብሩን ከፍሏል። ፍርድ ቤት ሄደው የሚከራከሩ አሉ፡፡ እሱ ደግሞ ሕጋዊ ሒደትን ተከትሎ የሚኬድበት መብት ነው፣ ችግር ያለው አይመስለኝም፤›› ሲሉ ማብራሪያቸውን ደምድመዋል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 938

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>