
በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ በተፈፀመ ጥቃት ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ደግሞ መፈናቀላቸው ነዋሪዎች ተናገሩ።በዞኑ ጌራ ወረዳ ዋላ በተባለ ቀበሌ የካቲት 6/2017 ዓ.ም.
አቶ ዛኪር አባ ኦሊ የተባሉ ባለሀብት መገደላቸውን ተከትሎ “ወጣቶች” የነዋሪዎችን ማንነት እየለዩ ቤቶችን እና ንብረቶችን ማቃጠላቸውን የዓይን እማኞች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። በቀበሌው ጊዮርጊስ በተባለ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ አንድ አባት ረቡዕ ሌሊት ለሐሙስ አጥቢያ “የጥይት ተኩስ” መስማታቸውን ጠቅሰው፤ ተኩሱ አላባራ በማለቱ ከነቤተሰባቸው መደናገጣቸውን ገልፀዋል።”ተኩስ ሲበዛ ተደናገጥን። ያወቅነው ነገር የለም” በማለት ክስተቱን የተናገሩትረ አገልጋዩ፤ ከከባድ ተኩስ በኋላ ወጣቶች እና “ልዩ ኃይል” በተሽከርካሪ ወደ ቤታቸው ሲቃረቡ በሌሊት ልብሳቸው ሮጠው ማምለጣቸውን ተናግረዋል።ቤታቸው ሲቃጠል የአምስት ዓመት ልጃቸውን እና ባለቤታቸውን ይዘው በአቅራቢያ ወደ ሚገኝ ጫካ ማምለጣቸውን የተናገሩት የሃይማኖት አባቱ ጥቃት የሚፈጽሙት ሰዎች በየመንደሩ እየዞሩ ቤቶችን ማቃጠላቸውን ተናግረዋል።”የለበስኩት ነገር የለም። ሁሉም ንብረቴ ነው የተቃጠለው። ልጄን እና ባለቤቴን ይዤ በመውጣቴ ነው ፈጣሪን የማመሰግነው” ብለዋል።ሌላ ነዋሪም ባለሀብቱን ማን እንደገደላቸው ሳይታወቅ ሐሙስ ሌሊት ጀምሮ ቦሬ በተባለች አነስተኛ ከተማ “የአማራ ተወላጆች” ተለይተው ተፈጽሟል ባሉት ጥቃት መኖሪያ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ትራክተሮች፣ ወፍጮ ቤቶች እንዲሁም የተዘራ እህል “ቄሮ” ሲሉ በጠሯቸው ወጣቶች መቃጠላቸውን ገልፀዋል።በቡና ማምረት እና መፈልፈል ንግድ ላይ ተሰማርተው ነበር የተባሉት ባለሀብቱ ለኢንቨስትመንት መሬት ጠይቀው የ200 ገደማ የአርሶ አደሮች መሬት እንደተሰጣቸው የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ግድያቸው “ከአማራ ተወላጆች” ጋር መያያዙን ገልጸዋል።”አገሩ አይታይም። እሳት በእሳት፤ ነደድ በነደድ ሆነ” ሲሉ የተፈፀመውን ጥቃት የገለፁት አንድ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የዓይን እማኝ፤ ለጥቃቱ መነሻ “ባለሀብቱ ለምን ተገደለ?” የሚል ነው ብለዋል።ጥቃቱ የተፈፀመው በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች ይኖሩበታል በተባለው ቦሬ ከተማ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ቤት ሲጠቁም ነበር ያሉት ወጣት የሚያውቁት የአካባቢው ነዋሪ መሆኑን ገልፀዋል።ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ 10 የሚሆኑ ሠዎች መገደላቸውን የተናገሩት ነዋሪው፤ ከሟቾች ውስጥ አዛኔ አምባዬ የተባሉ ሽማግሌ እንደሚገኙበትም ገልፀዋል። ይህኑ ያረጋገጡ ሌላ ነዋሪ፤ አስካሁንም የገቡበት ያልታወቁ ሰዎች መኖራቸውንም ጠቁመው የምን ያህል ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ አይታወቅም ብለዋል። የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሐሙስ ረፋድ ላይ ወደ ቀበሌው ቢገቡም አካባቢውን ለማረጋጋት ባለመቻላቸው የነዋሪዎች ስጋት አለመቀረፉን ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።”ቤት እየተቃጠለ እንዴት ዝም ይላሉ? ትክክለኛ የመንግሥት አካል ቢሆኑ ቤት እየተቃጠለ ዝም አይሉም። . . . እውነተኛ የሕግ አካል ቢሆኑ ያስቆሟቸው ነበር፤ እረፉ፤ ተረጋጉ ይሉ ነበር” በማለት የፀጥታ ኃይሎች አካባቢውን ባለማረጋጋታቸው ቀያቸውን ጥለው ለመሸሽ መገደዳቸውን ተናግረዋል።”ትክክለኛ ሕጋዊ አካል ቢሆኑ ሁሉንም አስቁመው፤ ሁሉንም አስማምተው ወንጀለኛውን ካለበት ቦታ መፈለግ [ነበረባቸው]” ሲሉ ለደረሰባቸው ጥቃት የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች “የሚጠበቅባቸውን አላደረጉም” ሲሉ ይውቅሳሉ። ጥቃቱ በቦሬ ከተማ እስከ ቀን 10፡00 ድረስ መቆየቱን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ቤት ማቃጠል እና ሰዎችን በማጥቃት ኦባ የተባለ ቀበሌ ድረስ መስፋፋቱን እና ሌሎች ጥቃቶችም መቀጠላቸውን ተናግረዋል።ጥቃቱ በተፈፀመበት ቀን ሐሙስ ዕለት ባለቤታቸውን እና ወላጆቻቸውን አጎራባች ወደ ሆነው ደቡብ ምዕራብ ክልል ማሸሸታቸውን የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ንብረታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ለሦስት ቀናት ቢቆዩም ስጋታቸው ባለመቀረፉ እሳቸውም ከብቶቻቸውን ይዘው መሸሸታቸውን ገልፀዋል።ዞን 2 ተብሎ በሚጠራ ጎጥ 25 ቤቶች መቃጠላቸውን ተከትሎ አርብ የካቲት 7/ 2017 ዓ.ም. ምሽት ላይ ስድስት ልጆቻቸውን እና በሬዎቻቸውን ይዘው ወደ ደቡብ ምዕራብ ክልል እንደሸሹ ሌላ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።የአካባቢው ነዋሪ ሲሸሽ መንገድ ላይ አራት ነፍሰ ጡር እናቶች መገላገላቸውን የተናገሩት ነዋሪው፤ አምስት ላሞችም መንገድ ላይ መውለዳቸውን ገልፀዋል።በደቡብ ምዕራብ ክልል ከፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ አበክቻ ቀበሌ ሰባት ሺህ የሚሆኑ የዋላ ቀበሌ ነዋሪዎች ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ አራት ሰዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።የአካባቢው አስተዳደር እንደተቀበላቸው የተናገሩት ተፈናቃዮች ነዋሪዎች እና አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሚገኝም ገልጸዋል።ሰባት ሺህ 900 የሚሆኑ ተፈናቃዮች መመዝገባቸውን የገለፁት ነዋሪው፤ ነፍሰ ጡር እናቶች እና ህፃናትን ጨምሮ ተፈናቃዮች የተቀቀለ ጥሬ እየተመገቡ እንደሆነ ገልፀዋል።”ችግር ላይ ነን” የሚሉት ተፈናቃዮች መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርስላቸው ተማጽነዋል።ቢቢሲ ክስተቱ ያጋጠመበት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሀዊ ሰዒድ እና ከጅማ ዞን ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጁነዲን መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም።የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ትናንት ዕሁድ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን “ክስተት” ሲል የገለፀ ሲሆን፤ ከባለሀብቱ ግድያ ውጭ ስለተከሰተው ሁነት በዝርዝር ያለው ነገር የለም።ነዋሪዎች “ተደናግጠው” መሸሸታቸውን የጠቀሰው ክልሉ፤ በስም ያልጠቀሳቸው ተቋማት እና ግለሰቦች “ክስተቱን ወደ እምነት እና ብሔር ለመጎተት ሲሞክሩ ታይተዋል” ሲል ከሷል።”ይህም የተቋማቱን ድብቅ ፍላጎት በማጋለጥ እጃቸው እንዳለበት ያሳያል” ሲሉ ክስተቱን ድብቅ ዓላማ ባላቸው ወገኖች ሴራ የተፈጠረ መሆኑን አመለክቷል።