Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

በተያዘው ወር መጨረሻ  አዲስ ፖስፖርትና ቪዛ  ይፋ ይደረጋል ተባለ

$
0
0

በውጭ አገር የሚታተመውን ፓስፖርትና አገሪቱ ለውጭ ዜጎች የምትሰጠውን ቪዛ በአዲስ ይዘትና ኅትመት በአገር ውስጥ ታትሞ በተያዘው ወር የካቲት 2017 ዓ.ም. ይፋ እንደሚደረግ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።የአገልግሎት ተቋሙ ይህን የገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋና መሥሪያ ቤቱ ተገኝቶ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ነበር።በመጪዎቹ ሳምንታት ይፋ ይደረጋል የተባለው አዲሱ ፓስፖርት በቀለም በዲዛይንና በይዘት በአገልግሎት ላይ ካለው ፖስፖርት በእጅጉ የላቀ ነው የተባለለት ሲሆን፣ የውስጥ ገጾቹ  በአራቱም የአገሪቱ ክፍል ያሉትን እንደ አክሱም ጎንደር የጀጎል ግንብ የቡና ምርትና ሌሎች የአገሪቱን ባህላዊና ታሪካዊ የተፈጥሮ ቅርሶች የታተሙበት መሆኑ ተገልጿል።ለውጭ አገር ዜጎች የሚሰጠው የመኖሪያ ፈቃድ፣ ቪዛና ፖስፖርቱም በአዲስ ይዘት  በተመሳሳይ ጊዜ ይፋ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው አዲስ የታተመው የቪዛ ስቲከር ወይም ተለጣፊ ቪዛ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በደብዳቤ እንዲያውቁት  ተደርጓል።ኢትዮጵያ እየተጠቀመችበት ያለው ቪዛ አገሪቱን አይመጥንም በሚል ማብራሪያ የሰጡት የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ፣ መዝገቡ አገሪቱ የምትሰጠው  ቪዛ ላይ በእጅ  ሲፃፍ የነበረውን አሠራር ወደ ዲጂታል የቀየረና ጥንቃቄ የተሞላበት ነው ብለዋል።በተጨማሪም በሥራ ላይ የነበረው  የአስቸኳይ የጉዞ ሰነድ በወረቀት ይታተም የነበረ በመሆኑ ኤርትራውያንና የሌሎች አገር  ዜጎች ስደተኛ ነን በሚል በቀላሉ  ይወጡበት እንደነበር ገልጸዋል። በአዲሱ ኅትመት ይህ የጉዞ ሰነድ ሙሉ ባዮሜትሪክ መረጃ ተመዝግቦ የሚሰጥ በመሆኑ የማጭበርበር ዕድል የማይታሰብ እንደሚሆን ተናግረዋል።

‹‹የውጭ ዜጎች ዝምብለው ሲፋንኑበት የነበረ ሒደት በመሆኑ፣ አሁን ይህን ዓይነት መሰል አሠራሮች በማስወገድ በዲጅታል መንገድ  ወደ ቋት የሚገባውን መረጃው በማስቀመጥ የፀጥታና የመረጃ  ተቋማት በቀላሉ መረጃውን ወስደው የሚፈልጉትን የሕግ ማስፈጸም ሥራ መሥራት ይችላሉ፤›› ብለዋል።አዲስ ቴክኖሎጂ በውስጡ አካቶ በአገር ውስጥ ይመረታል የተባለው አዲስ ፓስፖርት፣ ቪዛ እና የመኖሪያ ፈቃድ ሰነድ በውጭ አገርና ኩባንያ ቁጥጥር የነበረውን የማምረት ሥራ በአገር  ውስጥ በባለቤትነት ይመራል ተብሏል። 

የአገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በሰጡት ማብራሪያ ነባሩ ፖስፖርት እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም.  እንደሚሰጥና አዲሱ ፖስፖርት የካቲት 2017 ዓ.ም መታተም እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ከ20 ዓመታት በፊት ሥራ ላይ የዋለ ቴክኖሎጂ በመጠቀሜ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል የሚለው ተቋሙ፣ በአዲስ መልኩ የገጠመው ቴክኖሎጂ የተሟላ አገልግሎት በብቃትና በጥራት ማስተናገድ ይቻላል ብለዋል። የአገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር  ባቀረቡት ማብራሪያ፣ በሥራ ላይ ያለው  ፓስፖርት ላምኔት ተደርጎ የሚሠራ በመሆኑ በዩጋንዳና ሱማሌ ላንድ የኢትዮጵያን ፓስፖርት ቡክሌት እየወሰዱ ኮፒ በማድረግ የሚያሠራጩ መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በአዲሱ አሠራር ስምንተኛው ትውልድና ጊዜው የደረሰበት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ የሚታተም ፖስፖርት መሆኑም ማንም በቀላሉ ሊያባዛው አይችልም ብለዋል። በተጨማሪም በሥራ ላይ ያለው ፖስፖርት  በውጭ አገር የሚታተም በመሆኑና የኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ዓይነት ሚና የሌለው በመሆኑ፣ አምራቹ ድርጅት እንደፈለገ እያመረተ መሸጥ፣ መስጠት የሚያስችለው የነበረ ሲሆን፣ አዲሱ ፖስፖርት ዲዛይንና ኅትመት በኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ሥር  ነው ብለዋል።የአገልግሎት ተቋሙ ከወራት በፊት ባደረገው ማሻሻያ አምስት ሺሕ ብር፣ በሁለት ቀን የሚደርስ አስቸኳይ ፓስፖርት 25 ሺሕ ብር እንዲሁም በአምስት ቀን የሚደርስ አስቸኳይ ፓስፖርት 20 ሺሕ እንዲሆን ተደርጓል። በተመሳሳይ ለጠፋ ፓስፖርትና ለዕርማት ከ13 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ብር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles