በደቡባዊ ኦስትሪያ አንድ ተጠርጣሪ ባደረሰው የስለት ጥቃት የ14 አመት ህጻን ተገድሎ አምስት ሰዎች ቆስለዋል።ፖሊስ እንዳለው ተጠርጣሪው የ23 ዓመቱ ሶሪያዊ ጥገኝነት ጠያቂ ነው። ይህ ተጠርጣሪ ከጣሊያን እና ስሎቬንያ ጋር በሚያዋስነው ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ ቪላች ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሏል።ፖሊስ ግለሰቡ ለምን ይህን ጥቃት ለመፈጸም እንደፈለገ እስካሁን ምክንያቱን ማወቅ አልተቻለም።ነገር ግን በምርመራው ላይ ከአክራሪነት ጋር የተያያዘ ከሆነ በሚል የሽብር መርማሪ መኮንኖችን ፖሊስ አሳትፏል ሲል ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግሯል።ድርጊቱ የተፈፀመው በአገሬው አቆጣጠር ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በከተማው ዋና አደባባይ አካባቢ ነው።ጉዳት ከደረሰባቸው አምስት ሰዎች መካከል ሁለቱ እስከ ቅዳሜ አመሻሽ ድረስ በከባድ ሁኔታ ላይ ነበሩ።አንድ በአካባቢው መኪና እያሽከረከረ የነበረ ሾፌር በስለት ተጨማሪ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አድርጓል በሚል ፖሊስ አወድሶታል።ይህ የዕቃ አመላላሽ ተሽከርካሪ ሾፌር በስለት ጥቃት እያደረሰ የነበረውን ወጣት ሆን ብሎ በመኪናው ገፍቶ ጥሎታል።ተጠርጣሪው ብዙም ሳይቆይ በሁለት ሴት ፖሊሶች ተይዟል። እስከ ቅዳሜ አመሻሽ ድረስ በምርመራ ላይ ነበር ሲል ፖሊስ ተናግሯል።ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ሁለተኛ ጥቃት ሊኖር ይችላል የሚል ጥርጣሬ በመፈጠሩ ፖሊስ የባቡር ጉዞ እንዲዘጋ አድርጓል።ይሁን እንጂ የአካባቢው ፖሊስ ለቢቢሲ እንደተናገረው ሌላ ጥቃት አድራሽ አልነበረም።የኦስትሪያ ሕግ መሠረት የአጥቂው ማንነት ለጊዜው አልተገለጸም። ነገርግን ፖሊስ በአካባቢው ይኖር የነበረ የ23 አመት ሶሪያዊ መሆኑን አረጋግጧል።ይህ ወጣት ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ነበረው እና በጥገኝነት ማመልከቻው ላይ ውሳኔ እየጠበቀ ነበር። ፖሊስ እነዳለው በዚህ ጥቃት አራት ሰዎች ክፉኛ ቆስለዋል ። አምስተኛው ሰው ቀላል ጉዳት ደርሶበታል. የተገደለው አዳጊ ማንነትም እስካሁን አልተገለጸም።በኦስትሪያ በጥገኝነት ሕጎች ላይ በተደረጉ ሀገራዊ ክርክሮች እና ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረ የፖለቲካ ቀውስ የቀኝ አክራሪው የፍሪደም ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የበላይ ሆኖ መውጣቱን ይታወሳል። ሆኖም ጥምር መንግሥት መመሥረት አልቻለም። የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኸርቤት ኪክል በሰጡት መግለጫ ኦስትሪያ “በጥገኝነት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለባት” ብለዋል። ከሰሞኑ በሙኒክ በተመሳሳይ በአንድ አፍጋኒስታናዊ ጥገኝነት ጠያቂ የመኪና ጥቃት ደርሶ እናትና ልጅ መገደላቸው እና ሌሎች በርካቶች መቁሰላቸው ይታወሳል።
↧