Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

በትግራይ ክልል ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ መከልከል ጋር በተያያዘ  የተቃውሞ ሠልፍ ተደረገ

$
0
0

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ 159 ሙስሊም ሴት ተማሪዎች፣ በሂጃብ ምክንያት ከአንድ ወር በላይ ከተገለሉበት ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ፣ በክልሉ ትምህርት ቢሮና ፍርድ ቤት የተሰጠው ትዕዛዝ እንዲከበር የሚጠይቅ የተቃውሞ ሠልፍ ትናንት ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ ተደረገ።በክልሉ ዋና ከተማ መቀሌ በተደረገው የተቃውሞ ሠልፍ የተገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች፣ ‹‹ሂጃቧን ትለብሳለች፣ ትምህርቷንም ትማራለች›› የሚለውን ጨምሮ፣ የተለያዩ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ፣ የእኩልነትና ሰብዓዊነት መብቶቻቸው እንዲከበሩ የሚጠይቁ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል።በተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፉ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዩች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ አደም አብዱልቃድርና ዋና ጸሐፊው ሐጂ መሐመድ ካህሳይ፣ ላለፉት ሦስት ወራት ያህል ከሁለት ጊዜያት በላይ ለክልሉ ትምህርት ቢሮና ለአክሱም ትምህርት ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ላይ የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ እንዲያስደርጉ የሚያመለክቱ ደብዳቤዎች ቢጻፉም፣ ለውጥ ሊመጣ ባለመቻሉ ሠልፉ መከናወኑን ገልጸዋል።‹‹ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ›› የተባለ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት በታኅሳስ ወር 2017 ዓ.ም. ይፋ ያደረገውና በጉዳዩ ላይ ያደረገው አጭር ምርመራ ሪፖርት፣ በአጠቃላይ በተለይም በአክሱም ሁለተኛ ደረጃ በአንድ ግቢ የሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶችና ወርዒ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች፣ መብታቸውን ለማስከበር ጥያቄ በመጠየቃቸው፣ ከትምህርታቸው ተስተጓጉለው እንደሚገኙ ተማሪዎችና መምህራን ማረጋገጣቸውን ያስረዳል። የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ለአክሱም ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ታኅሳስ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. የአለባበስ ሥርዓትን በተመለከተ በጻፈው ደብዳቤ፣ ከክልሉ እስልምና ጉዳዩች አቤቱታ የቀረበለት መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ መመርያ ስላልወጣ አዲስ ክልከላም ሆነ አዲስ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ በነበረው አሠራር መቀጠል አለበት የሚል ትዕዛዝ አስተላልፏል። ይሁንና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ ይህ የትምህርት ቢሮ ደብዳቤ ትዕዛዝ አሻሚ አገላለጽ መያዙን ጠቅሷል። በምክንያትነት ያቀረበውም፣ አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት፣ ተማሪዎች ሂጃብ አድርገው ለመማር እንደማይፈቅድላቸው፣ ከጦርነቱ በኋላ ትምህርት ሲጀመር ግን ተማሪዎቹ ሂጃብ እየለበሱ ይማሩ እንደነበር በመጥቀስ ‹ከዚህ በፊት የነበረ› የሚለው የትምህርት ቢሮው አገላለጽ ከጦርነት በፊት የነበረውን አሠራር? ወይስ ከፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት በኋላ የመጣውን አሠራር? ለሚለው ግልጽ አቅጣጫ አለማስቀመጡ እንደሆነ ገልጿል። ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ በተማሪዎቹ ላይ በሃይማኖት ምክንያት የመማር መብት አድልኦ በመፈጸሙ ምክንያት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 የተደነገገውን የእኩልነት መብት ጥሰት መፈጸሙን አስረድቷል። በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 ላይ የተደነገገውን የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት፣ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው በትምህርት ተቋማት የአምልኮ ሥርዓት የሚመለከት መመርያ ላይ ‹‹የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎች ከዩኒፎርም ጋር የሚመሳሰል ሂጃብ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ከሂጃብ በቀር ሙሉ ጥቁር ልብስ ሙሉ በሙሉ ፊትን ጨምሮ የመሸፈን ወይም ‹ኒቃብ› በትምህርት ተቋማት መልበስ አይፈቀድም›› የሚል ቢሆንም፣ በተማሪዎች ላይ በመመርያ ደረጃ የተቀመጠውም መብት መጣሱ ታውቋል። የሪፖርተር ምንጮች የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ከደብዳቤ ትዕዛዞች ባለፈ ወደ ከተማው በመጓዝ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መፍትሔ ለማምጣት ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ መቆየቱን አረጋግጠዋል። ይሁንና ጉዳዩን በተመለከተ የትምህርት ቢሮው ዋና ኃላፊ ኪሮስ ጉዕሽ (ዶ/ር)፣ ከሪፖርተር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪና አጭር የሞባይል መልዕክት ቢላክላቸውም ለሳምንታት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበው ቆይተዋል። ተማሪዎች በሂጃብ ክልከላ ምክንያት ወደ ትምህርት ቤቶቹ እንዳይገቡ በተደረገባቸው ክልከላ ምክንያትም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የኦንላይን ምዝገባ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. እንዳለፋቸው፣ በአካል ተገኝተው መመዝገብ የሚችሉበት ጊዜ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ማለፉም ታውቋል። ይህንን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ሊወስደው የሚችለው ዕርምጃ ስለመኖሩ በሪፖርተር ዘጋቢ የተጠየቁት የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መስፍን ቦጋለ፣ ‹‹ጉዳዩ ትምህርት ሚኒስቴርን አይመለከትም፤›› በማለትና አስፀያፊ ስድብ በመሳደብ የአገሪቱን ከፍተኛ የትምህርት ፖሊሲ ከሚያስፈጽመው የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሠራተኛ የማይጠበቅ ተግባር በመፈጸም ስልካቸውን ዘግተዋል። በሌላ በኩል የአክሱም ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ትምህርት ቤት እንዳይገቡ የሚከለክለውን መመርያ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ያገደ ቢሆንም፣ ተማሪዎች ግን ከዕግዱም በኋላ ወደ ትምህርት ቤቶቹ እንዳይገቡ ተደርገው ቆይተዋል። ፍርድ ቤቱ አምስቱ ክልከላውን ያደረጉት ትምህርት ቤቶች በቀረቡባቸው ክሶች ላይ ቀርበው ቃላቸው እንዲሰጡ ለጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀነ ቀጠሮ ሰጥቶ ጉዳዩ በፍትሕ ሥርዓቱ ሒደት ውስጥ ባለበት ነው፣ የማክሰኞ ጥር 13 ቀን የተቃውሞ ሠልፍ በመቀሌ ከተማ የተደረገው። የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎችን ሂጃብ ክልከላን በተመለከተ በክልሉ ዋና ከተማ የተደረገው ሰላማዊ ሠልፍ ከተገደባደደ በኋላ 20 የሚሆኑ የሙስሊም ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ ከጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ውይይት ማድረጋቸውም ታውቋል። አቶ ጌታቸው በጉዳዩ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ችግሩን ሥርዓት ባለው መንገድ ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የትግራይ ሴቶች ሙስሊምም ሆኑ ክርስቲያን ትምህርታቸውን መማር ከማይችሉበት ሁኔታ ወጥተው አንፃራዊ ሰላምን ባገኙበት በዚህ ወቅት፣ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ የሚያደርግ ሁኔታ መፈጠሩ እጅግ አሳዛኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ብንዘገይም አሁንም አልረፈደምና በአፋጣኝ እንዲፈታ እንሠራለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>