
በየመን ዱባብ ግዛት የባሕር ዳርቻ ላይ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ 20 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም አይኦኤም ገለጸ። ታይዝ በተባለው ግዛት በሚገኘው ዱባብ አካባቢ ጥር 10/2017 ዓ. ም. አደጋው እንደደረሰ ተገልጿል። በአደጋው 11 ወንዶች እና ዘጠኝ ሴቶች የሆኑ ኢትዮጵያውያን የሞቱ ሲሆን፣ ጀልባው በአጠቃላይ 35 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ይዞ እየተጓዘ ነበር። የመናዊ ካፕቴን እና ጂቡቲያዊ ተባባሪ የነበረው ጀልባ የተገለበጠው አል ሃጃጂህ የተባለ አካባቢ አቅራቢያ እንደሆነ አይኦኤም በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። የመንግሥታቱ ድርጅት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት አይኦኤም ዛሬ ጥር 14 ቀን 2017 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ ከአደጋው 15 ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ሁለት የመናዊ የጀልባው ሠራተኞች በሕይወት ተርፈዋል። ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ከከፍተኛ እንግልት በኋላ ወደ ባሕር ዳርቻ በሕይወት መድረሳቸው በመገልጫው ተካቷል። ከጂቡቲዋ ሐማርታ የተነሳው ጀልባ ላይ ለደረሰበት የመገልበጥ አደጋ ምክንያቱ ከፍተኛ ንፋስ መሆኑ ተነግሯል። የየመን አይኦኤም ቅርንጫፍ የሥራ ኃላፊ አብዱሳቶር ኢሶቭ እንዳሉት አሰቃቂው አደጋ “ስደተኞች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ የሚያልፉት አሰቃቂ ሁኔታን” የሚያስታውስ ነው። “አንድም ሕይወት ቢሆን ዋጋው ብዙ ነው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ችግሩን ከሥሩ ለመንቀል የሕገ ወጥ ስደትን ምክንያትን ማስወገድ አለበት። በዚህ መንገድ የስደተኞች ክብር ይጠበቃል” ሲሉም አሳስበዋል። የሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችን ሰንሰለት ለመበጣጠስ እና ለስደተኞች የተሻለ መንገድ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ቢቀጥልም አሁንም በርካቶች ሕይወታቸውን እያጡ ነው። በባሕር በሚያቋርጡ ስደተኞች ላይ ከሚደርሰው አደጋ አንጻር የየመን የባሕር ዳርቻ አካባቢ ከዓለም የከፋው ቦታ ነው ሲል አይኦኤም ገልጿል። እአአ በ2024 ብቻ አይኦኤም 60,000 ስደተኞች የመን መድረሳቸውን መዝግቧል። ከ2014 ጀምሮ ባሕር ላይ ባጋጠማቸው አደጋ 3,435 ሰዎች መሞታቸውን እና የደረሱበት እንደማይታወቅም ተቋሙ መዝግቧል። ከእነዚህ መካከል 1,416 ሰጥመው ነው ሕይወታቸውን ያጡት። የአሁኑ ክስተት ስደተኞች የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ የሚደረግ ጥረት ያለውን ሚና የሚያሳይ መሆኑን የስደተኞች ተቋሙ ገልጿል። “በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በድህነት ምክንያት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በየመን በኩል አድርገው ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ይሰደዳሉ። በእነዚህ አገራት የሚጠብቃቸው ብዝበዛ፣ ጥቃት እና ለሕይወት የከፋ ሁኔታ ነው” ብሏል አይኦኤም። በየመን በኩል ለሚያልፉ ስደተኞች የጤና አገልግሎት፣ ምግብ፣ መጠለያ እና ከለላ በመስጠት አይኦኤም ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል። ሆኖም ግን አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር እንደማይመጣጠን ጠቅሷል። “ዓለም አቀፍ ትብብር እና የገንዘብ ድጋፍ ሲጨምር በጋራ የስደተኞችን ደኅንነት በመጠበቅ ነፍስ ማዳን ይቻላል” ብሏል።ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ከየመን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ተገልብጣ ቢያንስ 49 ሰዎች በተመሳሳይ መሞታቸው አይዘነጋም። ጀልባዋ 260 የሚጠጉ ሰዎችን አሳፍራ የነበረ ሲሆን፣ ለመገልበጥ የበቃችውም በከባድ ነፋስ ምክንያት ነው ተብሏል። በተጨማሪም ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ብቻ በተከታታይ በደረሱ ሁለት አደጋዎች 60 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ባሕር ውስጥ ሰምጠው ለሞት መዳረጋቸው መዘገቡም ይታወሳል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአውሮፓውኑ 2024 ብቻ 97,000 ስደተኞች በጦርነት ውስጥ ወደ ምትገኘው የመን ገብተዋል። በየመን ያለው ጦርነት እና በቅርቡ የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ቢሆንም ስደተኞች ወደ አገሪቱ በአደጋኛ የባሕር ጉዞ መግባታቸውን ቀጥለዋል። ከጂቡቲ በመነሳት በሕገወጥ መንገድ በቀይ ባሕር በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት በሚጓዙ ስደተኞች ላይ ተመሳሳይ አደጋ በተደጋጋሚ ሲደርስ ቆይቷል። በዚህ አደገኛ መንገድ የሚጓዙት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ለሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ከመክፈላቸው በተጨማሪ እንግልት እና በደል እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።