
በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የሚገኙ አምስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሒጃብ መልበስ መከልከላቸውን ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ ሙስሊሞች ቁጣቸውን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ። ማክሰኞ ጥር 13/2017 ዓ.ም. ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንዲስተጓጎሉ እና እንዲታሰሩ ምክንያት የሆኑ እርምጃዎችን የሚያወግዝ ሰልፍ በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ተካሒዷል። ተማሪ አሚራ ሙስጠፋ ሃይማኖታቸው “በማንኛውም ሁኔታ ሒጃብ እንድናደርግ ስለሚያዝ፤ሒጃብ አትልበሱ በሚል ክልከላ የተፈጠረውን የትምህርት መስተጓጎል እንደምትቃወም” ትናገራለች። “ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ መልበሳቸው ከማንኛውም ነገር ሊያደናቅፋቸው አይገባም” የምትለው አሚራ፣ ሒጃብ መልበስ “የአንዲት ሙስሊም ሴት ክብር እና ማንነት መገለጫ ነው” ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች። አሚራ አክላ በተለይ በአክሱም ከተማ ተማሪዎች ሒጃብ እንዳይለብሱ መከልከሉ በማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ሕይወታቸው ላይ ጫና እየፈጠረ እንዳለ አስረድታለች። “በራስ መተማመን እንድናጣ ያደርጋል። ሒጃብ መልበስ ሃይማኖቱ የሚያዘው ስለሆነ ይህ ከልጅነታችን ስናደርገው የነበረ ጉዳይ ነው። ትምህርት ቤት ውስጥ ሒጃብ መልበስ ክልክል ነው ሲባል አንዲት ሙስሊም ተማሪ እንዴት ብላ ነው የምትማረው?” ስትል ትጠይቃለች። ራኒያ ኻሊፋ የተባለች ሌላ ሙስሊም ሴት በሃይማኖቱ ሒጃብ ማድረግ የሴት ልጅ ግዴታ መሆኑን በመጥቀስ “ሒጀብ አትልብሱ ብሎ ማስገደድ ክብሯን መንካት ነው” ትላለች ባለፈው ታኅሣሥ መጨረሻ መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ እንዳይለብሱ በመከልከላቸው ትምህርት ማቋረጣችን ተከትሎ የከተማዋን ትምህርት ቢሮ መውቀሱ አይዘነጋም። ራኒያ ለአንዲት ሙስሊም ሴት ተማሪ “ሒጃብ አትልበሺ ማለት ትምህርት ቤት አትምጪ ማለት ነው” ትላለች። ይህ ክልከላ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ሊያስገድዳቸው እንደሚችልም ትናገራለች።ይህ ሃይማኖታዊ ጉዳይ እና ሰብዓዊ መብት በመሆኑ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ይህን እንዲያከብሩ ራኒያ ጥሪ አቅርባለች። በአክሱም ከተማ ሒጃብ መልብስ ከልክለዋል የተባሉት ወርዒ፣ አክሱም፣ አብርሀ አፅብሀ፣ ቀዳማዊ ምኒሊክ እንዲሁም ክንደያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው። የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ኃላፊ ሼክ አደም አብድልቃድር ጉዳዩ እስካሁን እልባት እንዳላገኘ በመግለፅ፣ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ችግሩ እስኪፈታ ድረስ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይቀጥለዋል ብለዋል። “ከሁለት ወራት በላይ ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል። ወደ ክልልም ደብዳቤዎች ፅፈናል። ሆኖም መፍትሔ አላገኘንም።”

የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ተወካዮችን ተቀብለው ያነጋገሩት የትግራይ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ባለመሰጠቱ ይቅርታ ጠይቀዋል። “ይህ ጉዳይ በአፋጣኝ መፈታት አለበት። መፍትሔ ከላይ የሚመጣ ሳይሆን ከሕዝቡ ጋር በመመካከር ቢሆን ይመረጣል። ጥግ የያዙ ሰዎች እንደፈቀዱ ጉዳዩን የሚያሽከረክሩት መሆን የለበትም” ብለዋል። የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሒጃብ የለበሱ ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተከትሎ ብዙዎች ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል። የሕግ ባለሙያው መስጠፋ አብዱል በዚህ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ የሆኑ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ምዝገባ እንዳለፋቸው በማስታወስ ችግሩ ከትምህርት እና ምዘናዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር መፈታቱን ተናግረዋል። ጠበቃው የራሳቸውን መመሪያ የሚተገብሩ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ ተከትለው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በ2000 ዓ.ም. በትምህርት ተቋማት የአለባሰበስ፣ የአምልኮ እና የአመጋገብ ሥርዓትን በተመለከተ የወጣው መመሪያ የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎች ከዩኒፎርም ጋር የሚመሳሰል ሒጃብ ማድረግ ይችላሉ ይላል።