
በአገሪቱ የውኃ ተፋሰሶች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አስገዳጅ የአጠቃቀም ታሪፍ የሚጥል ደንብ ዝግጅት ተጠናቆ፣ በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ተገለጸ። የውኃ ተፋሰሶች አጠቃቀምና ታሪፍን የተመለከተ ጥናት ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ ከቆየ በኋላ፣ ድንጋጌዎችን አካቶ የተዘጋጀው ደንብ የመጨረሻ ረቂቅ በገንዘብ ሚኒስቴር እየታየ መሆኑን፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ሰኞ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም. አስታውቋል። የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ይህን ያስታወቁት፣ የተቀናጀ የውኃ ሀብት አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካበቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት ነው። የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ደኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ የውኃ ታሪፍ አሰባሰብ በዝርዝር የተደነገገበት ሰነድ በገንዘብ ሚኒስቴር ታይቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ተልኳል ብለዋል፡፡ ከብዙ አገሮች ልምዶች ተቀምሮ የተዘጋጀ ነው የተባለው ሰነድ፣ ለምሳሌ የመስኖ ውኃ ተጠቃሚዎች በአንድ እርሻ በአንድ ሔክታር መሬት ላይ ስንት ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በመጠቀም ነው ያመረቱት የሚለው ታሳቢ ተደርጎ ተመን ወጥቶለታል ብለዋል። የቀረበው ታሪፍ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ገንብቶ ለሚያመነጭበት ውኃ፣ ውኃ ገድቦ የሚያለማ ግለሰብና የመስኖ ሚኒስቴር ለሚጠቀሙባቸው የመስኖ ግድቦች፣ ‹‹በውኃ ተፋሰሶች ዳርቻ የተገነቡ ሆቴሎችና የመጠጥ ውኃ አመንጪዎቸ የሚጠቀሙት የውኃ መጠን ተለክቶ ክፍያውን እንዲከፈጽሙ ይደረጋል›› ሲሉ ሚኒስትር ደኤታው አስረድተዋል። የሚሰበሰበውን ታሪፍ በውኃ አካላቱ ላይ መልሶ ኢንቨስት በማድረግ፣ የውኃ አካላቱ ሥነ ምኅዳር እንዲጠበቅ ሥራ ላይ እንደሚውል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውኃ አካላት አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ በሰጡት አስተያየት፣ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚወጣው ደንብ ለሰዎችና ለእንስሳት ውኃ መጠጥ አቅራቢዎች፣ ለግብርና መስኖ ውኃ ተጠቃሚዎች፣ ለኃይል ማመንጫ፣ ለቱሪዝምና ለሌሎችም በውኃ አጠቃቀማቸው መሠረት እንዲከፍሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ‹‹ደንቡ ተዘጋጅቶ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደና የቆየ በመሆኑ፣ ከጊዜው ጋር የሚሄድ የዋጋ ማስተካከያና ማሻሻያ ተደርጎበት በፍጥነት እንዲፀድቅ ግፊት እያደረግን ነው፤›› ብለዋል። በፓርላማው ውይይት የተደረገበት የተቀናጀ ውኃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የሆነው ረቂቅ አዋጅ፣ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት የሚያቋቁሙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ያላትን የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር የውኃ ሀብት በፍትሐዊነትና በዘላቂነት መጠቀም እንድትችል ያደርጋታል ተብሏል፡፡ በረቂቁ እንደተመለከተው የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን፣ የተፋሰስ ተጋሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮችን፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ከንቲባዎችን፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካላት የበላይ አመራሮችን በአባልነት እንደሚይዝ ተገልጿል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አገሪቱ ባሏት ተፋሰሶች ብዛት ከ28 በላይ እንደሆኑ ቢነገርም፣ በረቂቁ እንደተብራራው በዚህ ድንጋጌ በአገሪቱ መልከዓ ምድር ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ተፋሰሶች የኃይድሮሎጂ ወሰን መሠረት በማድረግ ከእነ ንዑስ ተፋሰሶቻቸው 12 መሆናቸውንና መጠሪያ ስማቸውም ተካቷል፡፡ በረቂቁ በዓባይ ተፋሰስ፣ የአይሻ ተፋሰስ፣ የአዋሽ ተፋሰስ፣ የባሮ አኮቦ ተፋሰስ፣ የደናኪል ተፋሰስ፣ የገናሌ ዳዋ ተፋሰስ፣ የመረብ ተፋሰስ፣ የኦጋዴን ተፋሰስ፣ የኦሞ ጊቤ ተፋሰስ፣ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ፣ የተከዜ ተፋሰስና የዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡