Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ገንብቻለሁ አለ

$
0
0

መንግሥት ኢሕአዴግ መንግሥት ሆኖ አገሪቷን ሲያስተዳድር ለ14 ዓመታት (ከ1996 እስከ 2010 ዓ.ም.) በአገሪቱ ከገነባቸው ኮንዶሚኒየም የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአምስት እጥፍ የላቀ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ገንብቻለሁ አለ፡፡ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት መረጃ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ 1.5 ሚሊዮን ቤቶች ተሠርተው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ ይህንን ያስታወቁት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ለማፅደቅ፣ ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 14 መደበኛ ስብሰባ ላይ  ነው፡፡ በስብሰባው ወቅት ከምክር ቤት አባላት መካከል የቀረበው የንብረት ታክስ አዋጅ፣ የዜጎችን ሕይወት የሚቀይር እንዳልሆነ፣ መንግሥት የጀመረውን የኮሪደር ልማት ለመጨረስ እንጂ ደሃውን ለመደጎም ለሚደረግ የልማት እንቅስቃሴ ላይ የሚውል ገንዘብ ለመሰብሰብ ያቀደ አለመሆኑን በመጥቀስ ትችት ሰንዝረው ነበር፡፡ በአዋጁ እንደተብራራው በሊዝ ይዞታ ሥሪት በሚተዳደር ማንኛውም የከተማ ቦታ፣ የመጠቀሚያ መብት ከሊዝ ይዞታ ሥሪት ውጪ በሆነ ነባር የቦታ የመጠቀሚያ መብት ላይ የንብረት ታክስ እንዲከፈል ተደንግጓል፡፡ ከንብረት ታክስ ነፃ የሚሆነው  ለአንድ ቤተሰብ መኖሪያነት አገልግሎት እየሰጠ ያለ በከፍተኛ የቦታ ደረጃ እስከ 15  ካሬ ሜትር፣ በዝቅተኛ የቦታ ደረጃ እስከ 30 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባ መኖሪያ ቤት፣ የሃይማኖት ተቋማት ለአምልኮና ለመካነ መቃብር አገልግሎት የሚጠቀሙበት ቦታና ቤት፣  በከተማ ውስጥ ያለ ሙሉ በሙሉ ለግብርና ሥራ የዋለ መሬት ናቸው፡፡ ከምክር ቤት አባላት መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ተወካይ አቶ ባርጠማ ፈቃዱ በሰጡት አስተያየት፣ የኮንዶሚኒየም አሠራር ከዚህ በፊት ችግር የነበረበት ቢሆንም ለዜጎች የቤት አቅርቦት በተለያዩ መርሐ ግብሮች ይቀርብ እንደነበርና ትልቅ ችግር የፈታ አማራጭ ነበር ሲሉ ገልጸውታል፡፡ አሁን ግን የኮንዶሚኒየም ቤት አማራጭ መቋረጡን ጠቅሰው፣ መንግሥት የሚያገኘውን ሀብት የቤት ግንባታ ላይ ለምን አያውልም በማለት ጠይቀዋል፡፡ አክለውም  የንብረት ታክስ አዋጅ ለዚህ የቤት ግንባታ መርሐ ግብር የማይውል፣ ከዜጎች በሚሰበሰብው ገንዘብ ተገንብቶ የሚቀርብ ተመጣጣኝ የቤት አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም የቤቶች ኮርፖሬሽን ዓላማው ቤቶችን ገንብቶ ለዜጎች ቤት ማዳረስ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በተለየ ቢዝነስ ውስጥ ተሰማርቷል ሲሉ ተችተውታል፡፡ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ በንብረት ታክስ አዋጅ የሚሰበሰበው ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግና የጀመራቸውን ሥራዎች የሚያጠናክር፣ ብቃት ያለው የመንግሥት አገልግሎት ለመስጠትና የዜጎችን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየመለሰ ለመሄድ ያግዘዋል ብለዋል፡፡  ‹‹ባለፉት አምስት ዓመታት የቤት ግንባታ ሥራ ተቋርጧል የሚባለው በጣም የተሳሳተ መረጃ ነው፤›› ያሉት ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ዓመታት ተገንብተዋል ያሏቸውን 1.5 ሚሊዮን ቤቶች በማነፃፀሪያ ሲገልጹ፣ ‹‹በዚህ አገር ኮንዶሚኒየም ተጀመረ ከተባለበት ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ የተገነባውና አሁን ባለው መንግሥት የተገነባው ሲነፃፀር፣ በአሁኑ ጊዜ ከአምስት እጥፍ በላይ ገንብተናል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የቤት ግንባታ አልተቋረጠም አጠናክረን ቀጥለናል፤›› ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በንብረት ታክስ አዋጅ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የታችኛው የማኅበረሰብ ክፍልና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከታክስ ነፃ እንዲሆኑ የሚሉ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተው የነበረ ቢሆንም፣ በቀረበው ማስተካከያ እምብዛም ማሻሻያ አልተደረገበትም ተብሎ ከአባላት ቅሬታ ሲነሳ ተደምጧል፡፡ በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ በአራት ተቃውሞ፣ በአሥር ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>