Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ቀዬአችን እንድንመለስ ድምፅ ይሁነን ሲሉ ጠየቁ

$
0
0

ከሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የተቃውሞ ሠልፍ በመቀሌ ከተማ እያካሄዱ ያሉት የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ እንዲሆናቸው ጠየቁ፡፡ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት ወደ ተፈናቀሉበት የመኖሪያ ቀዬ ለመመለስ የሚመለከታቸውን የስምምነት ተፈራራሚ አካላትን ሲጠይቁ ቢቆዩም፣ እስካሁን ምላሽ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት ‹‹ከቤት ንብረታችን ተፈናቅለን በመጠለያ ጣቢያዎች በዳስ ውስጥ ለመኖር ተገደናል›› የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ ‹‹ይህንን ሁሉ ችግርና መከራ ስንቀበል ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለምን ዝም ይላል?›› ሲሉ ሁሉም ወገን ድምፅ እንዲሆናቸው ጠይቀዋል፡፡ ከሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ረቡዕ ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደሚቆይ የተነገረለትን የመቀሌ ከተማ እምብርት በሚባለው ሮማናት አደባባይ በቀንና ምሽት የሚካሄደውን ሠልፍ ያዘጋጀው የፅዕላል ምዕራብ ትግራይ ማኅበረሰብ ሲቪክ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋዬ ተጠምቀ፣ ሠልፉ ከማንም የፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ የተፈናቃዮችን ጉዳይ ብቻ ያነገበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሠልፉ ‹‹ይኣከል›› ወይም ‹‹ይበቃል›› የሚል መሪ መፈክር እንደተሰጠው የጠቀሱት አቶ ፀጋዬ፣ በተለያዩ ምክንያቶች እየተጓተተ የሚገኘው የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች እንግልት ሊበቃና ወደ ቀዬአቸው ሊመለሱ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ተፈናቃዮችን የመመለስና የማቋቋም ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊያገኝ የሚገባው ነው፡፡ በጠለምትና በራያ አካባቢዎች የተወሰኑ ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ሆኖም የብዙ ተፈናቃዮች መኖሪያ ቀዬ የሆነው ምዕራብ ትግራይ አሁንም ድረስ በተስፋፊ ኃይሎች በጉልበት እንደተያዘ ነው የሚገኘው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በሰጠው ይሁንታ መሠረት ተስፋፊ ኃይሉ በጉልበት ከመሬታችን አስወጥቶናል፡፡ ለሰላም ስንል ለአራት ዓመታት በመጠለያዎች እየተንገላታን ኖረናል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ወደ መሬት ወርዶ ችግራችን ዕልባት ያገኛል በሚል በተስፋ ስንጠብቅ ብንቆይም፣ እስካሁን ድረስ የትግራይ ተፈናቃዮች ጉዳይ ወደ ጎን ተብሎ ነው የሚገኘው፡፡ እኛም ኢትዮጵያዊ እንደ መሆናችን ሌላው ሕዝብ ለምንድን ነው ለእኛ ጉዳይ ድምፅ የማይሆነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ፀጋዬ ሠልፉ ለሕወሓት፣ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ለፌዴራል መንግሥቱና ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ አሳሳቢ ባሉት ጉዳይ ላይ መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የተፈናቃዮች ጉዳይ የፖለቲካ ባለመሆኑ እንዲሁም ጦርነቱ የተካሄደው በሁለት የፖለቲካ ኃይሎች እንጂ በሕዝቦች መካከል ስላልሆነ፣ ጉዳዩን ለማጓተትና ለማደናቀፍ ምክንያት የሚደረድሩ በትግራይም ሆነ በሌላ ወገን ያሉ ኃይሎች ከስህተታቸው ታርመው የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወስዱ ነው አቶ ፀጋዬ የጠየቁት፡፡ ስለዚሁ የመቀሌ ከተማ የሦስት ቀናት ተከታታይ ሠልፍ አስተያየት የተጠየቁት የሳልሳዊ ወያነ ትግራይ ፓርቲ (ሳወት) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኔ አፅበሃ፣ የትግራይ ተወላጆች በተለይም የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን መታዘባቸውንና ሠልፉም ይህን ጉዳይ ለዓለም የሚያስተጋባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከምግብ ጀምሮ ትምህርት፣ ሥራ፣ የጤና አገልግሎት፣ መድኃኒትና ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ እያገኙ እንዳልሆነ ተፈናቃዮቹ ሲናገሩ ተመልክቼያለሁ፡፡ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ሲፈረም የትግራይ ግዛታዊ አንድነት ተመልሶ ወደ ቀዬአችን እንመለሳለን የሚል ተስፋ ቢያሳድሩም፣ ነገር ግን እስካሁን ባለመፈጸሙ ተስፋ መቁረጥ እያደረባቸው መሆኑንም ገልጸዋል፤›› ብለዋል፡፡ በትግራይ ከዕለት ወደ ዕለት እየሰፋ የሄደው ፖለቲካዊ ሽኩቻም ቢሆን ችግራቸውን እንዳከፋው ተፈናቃዮቹ መግለጻቸውን አቶ ብርሃኔ ተናግረዋል፡፡ ወደ ቀዬአቸው መመለስ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውና በፕሪቶሪያ ሰነድ የተረጋገጠ መሆኑን በማስመር፣ በሕወሓት ክፍፍልም ሆነ በሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ቁማር ወደ ቀዬአችን መመለስ ልንከለከል አይገባም ሲሉ መጠየቃቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የፌዴራል መንግሥት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትና አመራሮች የጥይት ድምፅ በትግራይ ቢቆምም እኛ ዋጋ እየከፈልን ነውና ወደ ቀዬአችን ይመልሱን በማለት ተፈናቃዮቹ ድምፅ አሰምተዋል፤›› በማለት ስለሠልፉ አብራርተዋል፡፡ ሁለቱም አስተያየት ሰጪዎች የፅዕላል ሲቪክ ማኅበሩ አቶ ፀጋዬም ሆነ የሳወት ፓርቲ አቶ ብርሃኔ፣ ሕወሓት የተፈናቃዮችን ጉዳይ የፖለቲካ ማገቻ ማድረጉን ተቃውመዋል፡፡ ከጦርነቱ በፊት የነበረው የሕወሓት አስተዳደራዊ መዋቅር አብሮ ካልተመለሰ በስተቀር፣ ተፈናቃዮቹ ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው አይመለሱም የሚል አቋም የተወሰኑ የሕወሓት አመራሮች መያዛቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት፣ የአማራ ክልልና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለረዥም ጊዜ እንደ ወልቃይትና ራያ ያሉ አጨቃጫቂ ጉዳዮች በሒደት እስኪፈቱ ድረስ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞው ቀዬአቸው ይመለሱ የሚል አቋም ይዘው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ የሕወሓት አመራሮች በተለይም የሕወሓት ጽሕፈት ቤትን የሚመራው የእነ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ቡድን ግን፣ ተፈናቃዮቹ ሲመለሱ የቀድሞው የሕወሓት መዋቅርም አብሮ ወደ ቦታው መመለስ አለበት የሚል አቋም በመያዙ ጉዳዩ መጓተቱ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና የልማት አጋሮች በጋራ ሆነው ይፋ ባደረጉት መረጃ መሠረት፣ የትግራይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም 2.1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ይጠይቃል ተብሏል፡፡ ተፈናቃዮቹን የማስመለሱ ጥረት ፖለቲካዊ መግባባት ቢፈጥር እንኳ፣ ይህ ሁሉ ገንዘብ ከየት ይገኛል የሚለው በብዙዎች ዘንድ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ የመቀሌው ሠልፍ ተሳታፊዎች ሰባ ካሬ ከሚባለውና ከሌሎች የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ እነዚሁ ሠልፈኞች ባሰሙት መፈክርም በመጠለያ ጣቢያዎች የሰዎች ሞት መከሰትን ጨምሮ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች መዳረጋቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ፣ ተፈናቃዮችን የማስፈሩ ሥራ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈጸም ጠይቋል፡፡ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ፍሰሐ ኪዳኑ በበኩላቸው፣ በትግራይ ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚቻለው ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱ ብቻ ነው የሚል ይዘት ያለው መግለጫ ቀደም ብሎ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>