
ኖቲንግሀም ፎረስት የዘንድሮው ፕሪሚዬር ሊግ ያልተጠበቀ አስደናቂ ቡድን ሆኗል። ኖቲንግሀም የሊጉ መሪ ሊቨርፑልን ይረታ ይሆን?
“ባለፈው መስከረም ሊቨርፑልን በሜዳው አሸንፈዋል። አሁን ደግሞ በሜዳቸው ይህን ከደገሙ የሚያስገርም ነው የሚሆነው” ይላል የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን።
ፎረስት በሁሉም ውድድሮች ሰባት ጨዋታዎች አሸንፏል። ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ያገኝ ይሆን?
ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ የሰሜን ለንደን ደርቢ ነው።
ሱተን አርሰናል ያሳለፈው ሳምንት ከባድ ነው፤ ቶተንሀም ደግሞ ሊቨርፑልን መርታት ችሏል ይላል።
እነሆ የ21ኛ ሳምንት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት።
ማክሰኞ

ብሬንትፈርድ ከማን. ሲቲ
ብሬንትፈርድ በኤፍ ኤ ዋንጫ ጨዋታ በአስደናቂ ሁኔታ ከታችኛው ሊግ በመጣው ፕላይመዝ ተሸንፈው ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል።
እርግጥ ነው ብሬንትፈርድ በሊጉ ከባድ ጨዋታዎች ይጠብቋቸዋል። ከሲቲ ቀጥሎ በሚመጣው እሑድ ከሊቨርፑል ይጫወታሉ።
ንቦቹ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በሜዳቸው ያደረጓቸውን ግጥሚያዎች ተሸንፈዋል። በተቃራኒው ሲቲ ወደ አቋሙ እየተመለሰ ይመስላል።
ይህን ጨዋታ ሲቲ የሚረታ ይመስለኛል። ሀላንድ ጎል ያስቆጥራል ብዬ እገምታለሁ።
ግምት፡ 1 – 2
ቼልሲ ከበርንመዝ
ይህም ጨዋታ ፈታኝ ይመስላል። ቼልሲ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። ወጣቱ የቼልሲ ቡድን የጨዋታ መደራረብ የከበደው ይመስላል።
ቦርንመዝ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገዱም። ዕድል የመፍጠር እና ጎል የማስቆጠር ችግር የለባቸውም።
ቼልሲ ምናልባት ወደ አሸናፊነታቸው ይመለሳሉ የሚል ግምት ቢኖረኝም ጨዋታው በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅ ውስጤ ይነግረኛል።
ዌስት ሀም ከፉልሀም
ግራሀም ፖተር የዌስት ሀም አሠልጣኝ ሆነው በሜዳቸው የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ነገር ግን ቡድናቸው ጎል ከየት እንደሚያመጣ የማውቀው ነገር የለም።
ፉልሀም መልካም አጨዋወት ያለው ቡድን ቢሆንም ከሰሞኑ ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖታል።
ምንም እንኳ ባለፊት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ባይሸነፍም ብዙ አቻ ወጥቷል። ውስጤ ለፉልሀም ቢያደላም በዌስት ሀም ሜዳ በመሆኑ አቻ ይወጣሉ የሚል ግምት አለኝ።
ግምት፡ 1 – 1

ኖቲንግሀም ፎረስት ከሊቨርፑል
ሊቨርፑል ከሰሞኑ አቋማቸው ተዳክሟል ማለት ይቻል ይሆን?
በካራባዎ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ በመጀመሪያው ጨዋታ በቶተንሀም ተሸንፈዋል። በሊጉ ከዩናይትድ አቻ ወጥተዋል።
የአርን ስሎት ቡድን በ6 ነጥብ ከአርሰናል እና ፎረስት ከፍ ብሎ ሊጉን ይመራል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አለው።
የፎረስት ተከላካይ መስመር ጠንካራ ነው። አጥቂው ክሪስ ዉድ ደግሞ የፊት መስመሩን ይዞታል። ይህ ጨዋታ ለሊርፑል ቀላል ይሆናል የሚል ግምት የለኝም።
ግምት፡ 1 – 1
ረቡዕ
ኤቨርተን ከአስተን ቪላ
ዴቪድ ሞየስ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ተመልሰዋል። ነገር ግን ሥራው ቀላል ይሆንላቸዋል ማለት ቀላል አይደለም። ሞየስ የኤቨርተንን ችግር ይቀርፉት ይሆን?
የኤቨርተን ተከላካይ ከግብ ጠባቂው ጀምሮ አስተማማኝ ቢሆንም ትልቁ ችግሩ ያለው አጥቂው መስመር ላይ ነው።
አስተን ቪላዎች ደግሞ ድል ቢቀናቸውም ጎል ያስተናግዳሉ። ለዚህ ነው ይህን ጨዋታ ቪላ እንደሚረታ ነው የማስበው።
ግምት፡ 0 – 2
ሌስተር ከክሪስታል ፓላስ
ሌስተር ከአምስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ በኤፍ ኤ ዋንጫው ድል ቀንቷቸዋል። ከዚህም ጨዋታ ነጥብ ማግኘት ግድ ይላቸዋል።
ነገር ግን ጨዋታው ለቀበሮዎቹ ቀላል የሚሆን አይመስለኝም። ምክንያቱም ፓላስ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ወደ ውጤት ተመልሰዋል። ካለፉት ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነው የተሸነፉት።
ግምት፡ 1 – 2
ኒውካስል ከዎልቭስ
ይህን ጨዋታ መገመት ቀላል ነው።
ኒውካስል አሁን ባለው አቋማቸው ሦስት ዋንጫዎች ለማሸነፍ የሚጥሩ ይመስላሉ። ያለፉትን ስምንት ጨዋታዎች ረትተዋል።
ዎልቭስ በአዲሱ አሠልጣኝ ቪቶር ፔሬራ የመጀመሪያዎቹን ጨዋታዎች ቢያሸንፉም በፎረስት ተሸንፈዋል።
አሌክሳንደር ኢሳክ አስደናቂ አቋም ላይ ነው።
ግምት፡ 3 – 0

አርሰናል ከቶተንሀም
አርሰናል ከባድ ሳምንት ላይ ነው። አሁን ባለው አቋም ከአርሰናል ይልቅ ቶተንሀም ለዋንጫው የተሻለ ዕድል ያለው ይመስለኛል።
ቡካዮ ሳካ በመጎዳቱ ምክንያት የአርሰናል የአጥቂ መስመር ተጎሳቁሏል።
ቢሆንም የቶተንሀም ጨዋታ ለአርሰናል የሚመች ይመስላል። የሚኬል አርቴታ ቡድን ጫናን ተቋቁሞ መልሶ ማጥቃት ይችላል ማለቴ ነው።
ይህ የደርቢ ጨዋታ ውጤት ለቶተንሀሙ አሠልጣኝ አንጅ ፖስቴኮግሉ የበለጠ የሚያስፈልጋቸው ይመስለኛል።
ቶተንሀም ጎል ማስቆጠሩ የማይቀር ነው። አርሰናል በዋንጫ ፉክክሩ መቀጠል የሚፈልግ ከሆነ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ አለበት። መድፈኞቹ ያደርጉታል ባይ ነኝ።
ግምት፡ 2 – 1
ሐሙስ
ኢፕስዊች ከብራይተን
ኢፕስዊች አሁን ያሉበት አቋም ጥሩ ይመስላል። ቢሆንም ይህ ጨዋታ ያሸንፋሉ የሚል ግምት የለኝም።
ባለፈው መስከረም በአሜክስ ስታድየም በነበረው ጨዋታ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል። ብራይተን ከሜዳቸው ውጪ ቢሆኑም ጨዋታውን በድል ይወጡታል እላለሁ።
ግምት፡ 1 – 2

ማንቸስተር ከሳውዝአምፕተን
ዩናይትድ በኤፍ ኤ ዋንጫ ጨዋታ ወደ አርሰናል ሜዳ ተጉዞ በ10 ተጫዋች ጫና ተቋቁሞ ማሸነፍ ችሏል። ያሳዩት አቋም የሚገርም ነው።
ከዚያ ቀደም ወደ አንፊልድ ተጉዘው በሊጉ አቻ ወጥተው ተመልሰዋል።
በቀጣይ ሦስት ጨዋታዎች በሜዳቸው ያደርጋሉ።
ከሳውዝአምፕተን ጋር በሜዳቸው የሚያደርጉት ጨዋታ ቀላል ይሆናል የሚል ግምት የለኝም። ምክንያቱም በአንዳንድ ጨዋታዎች የሚጠበቅባቸውን ያክል ሲያደርጉ አይታዩም።
ቢሆንም ይህን ጨዋታ ማሸነፋቸው አይቀርም።