
በቀረበባቸው ከባድ የዲስፕሊን ክስ ጥፋተኛ የተባሉ ሁለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ከሥራ እንዲሰናበቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወሰነ። ምክር ቤቱ ማክሰኞ ጥር 6/2017 ዓ.ም. ውሳኔውን ያሳለፈው የፓርላማው የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ከተወያያ በኋላ ነው። የዳኝነት ሥልጣንን በሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ ክፍል መሠረት ማንኛውም ዳኛ በተወሰኑ ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር የጡረታ ዕድሜ ከመድረሱ በፊት ከፈቃዱ ውጪ ከዳኝነት ሥራ እንደማይነሳ ያትታል። ከእነዚህ ሁኔታዎች አንዱ በዳኞች አስተዳደር ውሳኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በክልል ምክር ቤቶች ከግማሽ በላይ ድምጽ ሲጸድቅ መሆኑ ሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሯል። ይህን ተከትሎ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በሁለቱ ዳኞች “በቀረበባቸው ከባድ የዲስፕሊን ክስ ጥፋተኛ ናቸው በማለት ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ” ውሳኔ አቅርቧል። ይህ ውሳኔ እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነው። አዱኛ ረጋሳ እና አክሊሉ ዘሪሁን የተባሉት ሁለት ዳኞች “የተሰጣቸውን ሹመት ያለአግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል” ተከሰው ጥፋተኛ በመባል የእስር ቅጣት ተወስኖባቸው ነበር። ይህን ተከትሎ የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በሁለቱ ዳኞች ላይ የዲስፕሊን ክስ አቅርቧል። ቋሚ ኮሚቴው ለምክር ቤቱ ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ምርመራ ማድረጉ ተጠቁሟል። በጉባኤው ምርመራ መሠረተ አንደኛ ተጠሪ ተብለው የቀረቡት ዳኛ አዱኛ ረጋሳ፤ “ገንዘብ እና ቼክ ተቀብለው የዳኝነት ሥልጣናቸውን ለአድሎአዊነት ሥራ መጠቀማቸው የተረጋገጠ” መሆኑ ተገልጿል። የዳኛው ድርጊት “የዳኛ መታመን እና ክብርን የሚቀንስ እንዲሁም የተቋሙን ታአማኒነት የሚጎዳ እና የሀቀኝነትን መርኅ የሚፃረር” መሆኑን የጠቀሰው ጉባኤው የአቶ አዱኛ ረጋሳን የጥፋተኝነት ውሳኔ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ሁለተኛ ተጠሪ የሆኑት ዳኛ አክሊሉ ዘሪሁን በበኩላቸው “በያዙት መዝገብ አፋጣኝ ትዕዛዝ እንዲሰጥ በማግባባት፤ በ1ኛ ተጠሪ እና አፈፃጸም መዝገብን በሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ባስከፈቱ ግለሰቦች መካከል ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ” ተከስሰዋል። ዳኛ አክሊሉ የአስር ሚሊዮን ብር ቼክ በመቀበል አንደኛ ተጠሪ ለሆኑት ዳና አዱኛ “የሰጡ መሆናቸው” እና ለራሳቸው ደግሞ 100 ሺህ ብር መቀበላቸው፤ “በቀረቡት ማስረጃዎች የተረጋገጠ” መሆኑ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ሰፍሯል።ይህ የዳኛው ድርጊት “አድሎአዊነት መኖሩን የሚያረጋግጥ፣ የዳኝነት ሙያ የቆመለትን የሀቀኝነት መርኅ የሚቃረን እና ራስን ለማበልፀግ እንዲሁም ሌላ ያልተገባ ጥቅም ለማስገኘት የተደረገ” መሆኑንም የውሳኔ ሃሳቡ አክሏል። ሁለቱ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የተወሰኑ ቅሬታ ነጥቦችን በማንሳት የጉባኤው ውሳኔ እንዲሻርላቸው ጠይቀዋል። ዳኞቹ በጋራ ካረቀረቧቸው ቅሬታዎች መካከል ቀዳሚው በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የተጣለው ቅጣት “መርኅ አልባ እና በአንድ ጥፋት ሁለቴ ያለመቀጣትን የቅጣት መርኅ የሚፃረር [ነው]” ይላል። ከዚህ በተጨማሪ ዳኞቹ “የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ በሐሰት የተቀነባበረ እና ኢ-ታአማኒ መሆኑን” የሚገልጽ ቅሬታ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም ዳኞቹ የተጣለባቸው የቅጣት ውሳኔ ላይ የይግባኝ አቤቱታ አቅረበው በቀጠሮ ላይ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል። ዳኛ አክሊሉ በበኩላቸው የቀረበባቸው “የዲሲፕሊን ክስ እና የሥነ ምግባር ደንብ ጥሰት በግልጽ እና በዝርዝር ያልቀረበ መሆኑን” አንስተው ቅሬታ አቅርበዋል። “የምስክርነቱ ይዘት ወጥነት የሌለው እና ሊታመን የማይችል ፍሬ ነገሩ ግምታዊ መሆኑን” የቀረበባቸውን ክስ “በሚገባ ያስተባበሉ” መሆኑን ገልጸዋል። የዳኞችን ቅሬታ ጭብጥ መሠረት በማድረግ ቋሚ ኮሚቴው ምርምራ በማድረግ የደረሰበትን ድምዳሜ ለፓርላማው አቅርቧል። “በወንጀል ጥፋተኛ መባል በዲሲፕሊን ሊያስጠይቅ አይችልም ማለት አይደለም” ያለው ቋሚ ኮሚቴው፤ በሁለቱም ዳኞች የተነሳው የክሱ የቅጣት መርኅ የሆነውን በአንድ ጥፋት ሁለቴ ያለመከሰስ መብትን የሚፃረር ነው የሚለውን መከራከሪያ ሳይቀበለው ቀርቷል። ተጠሪ ዳኞቹ “ያልፀና ውሳኔን መሠረት አድርጎ ጉባኤው በዲስፕሊን እኛን መክሰሱ አግባብ አይደለም” በሚል ያቀረቡት መከራከሪያ በቋሚ ኮሚቴው ተቀባይነት አላገኘም። የምስክሮችን ኢ-ተአማኒነት በተመለከተ ቋሚ ኮሚቴው “[ምክር ቤቱ] የቀረቡትን ማስረጃዎች እና ምስክሮች ታአማኒነት የመፈተሽና ውሳኔ የማሻሻል ሥልጣን የሌለው” መሆኑን በመጥቀስ “ዳኞች የክስ መከራከሪያ የሆነውን የምስክሮቹን ኢ-ታማኒ መሆን ምክር ቤቱ ሊመረምረው ሚችለው አይደለም” ብሏል። በመሆኑም ቋሚ ኮሚቴው የሁለቱ ዳኞች ድርጊት “በገለልተኝነት መርኅ ስር የሚገኙትን ያለ አድልዎ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሥራ መሥራቱን የማረጋገጥ ኃላፊነት፣ የዳኛ እንዲሁም የተቋሙን መታመን የሚሸረሸር” መሆኑን ጠቅሷል። ቋሚ ኮሚቴው “በዳኝነት ሥራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደራሉ ተብለው የሚገመቱ ማናቸውም ስጦታዎችን፣ ብድርን እና ጥቅማ ጥቅምን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያለመቀበል ኃላፊነትን እና ዳኛ የዳኝነት ሥልጣኑን መከታ በማድረግ እራሱን ለማበልፀግ ወይም ለሌላ ሦስተኛ ወገን ያልተገባ ጥቅም ለማስገኘት ኃላፊነትን ያለመወጣት መርኆዎችን ጥሰው በመገኘታቸው” ከሥራ እንዲሰናበቱ ሲል ውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል። ምክር ቤቱም የውሳኔ ሃሳቡ ላይ ከተወያያ በኋላ የሁለቱን ዳኞች ስንብት ውሳኔ በሁለት ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
ዜና ምንጭ BBC NEWS