በሰኔ 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ሲደረግበት ቆይቶ ባለፈው ሐሙስ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በፓርላማ የፀደቀውን የንብረት ማስመለስ አዋጅ፣ መንግሥት ማጥቂያ መሣሪያ እንዳያደርገው የፓርላማው አባላት አስጠነቀቁ፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት በአገሪቱ የግብር፣ የውጭ ምንዛሪ፣ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓትና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ተብሎ ተዘጋጅቶ የቀረበው ሕግ፣ ወደኋላ አሥር ዓመታት ድረስ በመሄድ የሚፈጸም እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ባለንብረቱ ከመደበኛ ሕይወቱ በተለየ ንብረት ካፈራ፣ ንብረቱን በሕጋዊ መንገድ ስለማግኘቱ እንዲያስረዳ የሚያስገድድ ሕግ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ሕጉ ለሕዝብ ውይይት ከተመራ ጀምሮ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የተደነገገውን የዜጎችን ሀብት የማፍራት መብትና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የሚጥስ ነው ተብሎ ተቃውሞ ሲቀርብበት የነበረ ቢሆንም፣ በውይይት ወቅት ሲነሱ የነበሩ የማሻሻያ ሐሳቦች ሳይካተቱበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በሦስት ተቃውሞና በአራት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ በፀደቀው አዋጅ ላይ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት ያላቸውን ሥጋትና ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ የፍትሕ አካላት ገለልተኝነትና የባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ሊታሰብበት ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ፈቲ መኸዲ (ዶ/ር) የተባሉ የምክር ቤት አባል አዋጁ ተፈጻሚ የማይሆንባቸው ተብለው የቀረቡት የሃይማኖት ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የመንግሥት ተቋማትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳይ በየትኛው ሕግ ሊዳኙ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡መሐመድ አብዲ (ፕሮፌሰር) የተባሉ የምክር ቤት አባልም አራት ተቋማት ከንብረት ማስመለስ አዋጅ ነፃ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በተለይም የእምነትና የፖለቲካ ተቋማት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሕጉ እንዲጠየቁ አለመካተታቸው ያሳስባል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሕገወጥ የዶላር ግብይት በእነሱ በኩል እንደሚደረግ በግልጽ ይታወቃል፣ ብዙ ነገር ውስጥ ብለው፣ በአገር ጥቅም ላይ የሚገቡ ድርጅቶች በመኖራቸው እነዚህ አካላት ከዚህ ተግባር ነፃ ይሆናሉ ብለን አንገምትም ብለዋል፡፡ ‹‹የእምነት ተቋማት ብዙ ሥራቸው ዓለማዊ ነው፡፡ ልናምናቸው አንችልም፣ ነፃ መደረጋቸው ሕገወጥ ሀብት የማሸሽ መንገድ በር ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ሌላው የምክር ቤቱ አባል ባነሱት ሐሳብ አዋጁ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ላይ የተደነገገውን ንብረት የማፍራት መብት የሚጋፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በየትኛውም በሕገ መንግሥት በሚተዳደር ማኅበረሰብ ውስጥ የሚወጣ ሕግ ማንኛውም ዜጋ በሕገወጥ መንገድ ሀብት ማፍራት አለበት ብሎ አይደነግግም፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት ሀብትና ንብረት በግለሰቦች፣ በቡድኖችና በድርጅቶች ሲመዘበር እናውቃለን፤›› ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን አሁን በዚህ አዋጅ ወደኋላ አሥር ዓመት መመለስ ያስፈለገበት ምክንያት ለምንድነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡‹‹ተፈጻሚነቱ እጅግ እጅግ ያሠጋኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በማኅበራዊ መስተጋብሩ የተመሠገነ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ይህንን ስል ግን አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ጉድጓድ እየማሰ አያድርም ማለት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ይህ ጉዳይ በሕዝባችን መካከል የመጠራጠር የመከፋፋት የመወነጃጀል ነገር እንዳያመጣ ምን ጥንቃቄ ይደረጋል?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡‹‹ዕድሜ ልካቸውን ውጭ አገር ሠርተው፣ ሽንት ቤትና ኩሽና ጠርገው ወደ አገር ቤት ተመልሰው ቤት ሠርተው ለመኖር ገንዘብ የላኩ ሰዎች ምንጩ ያልታወቀ ተብሎ ገንዘብ ተይዞባቸው የሚንገላቱ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን፤›› ያሉት የምክር ቤት አባሉ፣ በዚህ መጠን ምንጩ ያልታወቀና የታወቀን ሀብት የመለየት ችግር ባለበት በዚህ ጊዜ ይህ ተጨማሪ ሕግ ምን ሊሠራ ይችላል ብለዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ይህ አዋጅ ተፈጻሚነቱ ያሳስበኛል፡፡ ይህንን ሥራ የሚሠሩ አካላት ገለልተኝነት መጠበቅ አለበት፤›› ካሉ በኋላ፣ የአንድ ባለሥልጣን ሀብት ይጣራ ሲባል ምን ያህል ተፈጻሚ ይሆናል ሲሉ ሥጋታችውን ገልጸዋል፡፡‹‹አሥር ዓመት ምን ታስቦ ነው? ያረቀቀው አካል ምን አሳማኝ ምክንያት ይዞ ነው? ለምን ከዛሬ ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን አልተደረገም?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የምክር ቤት ተወካይ አበባው ደሳለው (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ አንድ ሕግ ተፈጻሚነቱ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ባለው የጊዜ ወሰን ብቻ እንደሆነ የሕግ ምሁራን እንደሚናገሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ሕጉ አሥር ዓመት ወደኋላ ተመልሶ እንዲሠራ መደረጉ የሕግን መሠረታዊ መርህ የሚጥስ ከመሆኑም በላይ፣ ይህን ያስፈጽማሉ የሚባሉት የፍትሕ ተቋማት አቅማቸው፣ ገለልተኝነታቸውና ነፃነታቸው ሲገመገም ጥያቄ ውስጥ የገባበት ወቅት ላይ ነን፤›› ብለዋል፡፡በአሁኑ ወቅት ፍትሕ ለማግኘት ረዥም ጊዜ እንደሚወስድ፣ አስፈጻሚ አካላት በፍትሕ አካላቱ ሥራ ጣልቃ እንደሚገቡ፣ በነፃነትና በገልተኝነት ፍትሕ ለማስከበር ሲሞከር ዳኞች ከችሎት ላይ ጭምር እየተነሱ ለእስር እንደሚዳረጉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም አዋጁ አቅመ ደካሞችን የሚያጠቃ፣ አገርን ከመጥቀም ይልቅ የሚጎዳ አደገኛ ነው ብለውታል፡፡‹‹ከዚህ በፊት በነበረው ልምድ ክስ ሲመሠረት የነበረው በፖለቲካ አመለካከታቸው ከመንግሥት ጋር የሚቃረኑ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ላይ ነው፤›› ያሉት አባሉ፣ አዋጁ የሕግ መርህን የሚጥስና ተፈጻሚነቱ የሚያሠጋ ነው ብለዋል፡፡ የቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የንብረት ማስመለስ አዋጁ የሚፀድቀው የአገሪቱ የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓትና የፀረ ሙስና ትግሉ ነፃና ገለለተኛ በሆነ ምኅዳር ቢሆን ኖሮ እንዴት ደስ ባለኝ ነበረ፤›› ብለዋል፡፡‹‹አዋጁ የፖለቲካ ማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን እሠጋለሁ፤›› ያሉት መብራቱ (ዶ/ር)፣ ይህ እንዳይፈጠር ምን ጥንቃቄ ተደርጎበታል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹የእኛ ፖለቲካ ብዙ ውጥንቅጥ ያለበት፣ የምንፈልገውን ከፍ የማንፈልገውን ዝቅ የምናደርግበት ምኅዳርና የጥላቻ ፖለቲካ ውስጥ ያለን በመሆኑ፣ ባለሥልጣናትን ወይም ጥሩ የሚሠሩ ግለሰቦችን ለማጥቃት እንዳንጠቀምበት ምን ዓይነት ጥንቃቄ አለ?›› ሲሉ ምላሽ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ሙሉቀን አሰፋ የተባሉ የአብን ተወካይ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፣ ሕገወጥ ነገርን ማንም አይደግፍም፣ ነገር ግን አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ የተወሰኑ ግለሰቦችን ለማጥቃት የወጣ ሕግ ነው ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ እንዲሁም በሥርዓቱ የማይፈለጉ ባለሀብቶችንና የሃይማኖት መሪዎችን ለማጥቃት የተዘጋጀ አዋጅ ነው ብለዋል፡፡ አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ አዋጁ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ እንዳያፀድቀው ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የምክር ቤት አባላት ግን የቀረበው ጥያቄ ሳቅ ፈጥሮላቸዋል፡፡አወቀ አምዛየ (ዶ/ር) የተባሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካይ ባቀረቡት አስተያየት፣ ‹‹አዋጁ የተወሰኑ ቡድኖችን ለማጥቃት የፖለቲካ አጀንዳ ያለው ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እንደ ምክር ቤት በአንድ በኩል በምክክር ኮሚሽን አገር እናስታርቃለን ብለን እየሠራን፣ በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ሌላ ቁርሾ፣ ሌላ አመፅ፣ ሌላ ሽፍትነት የሚፈጥር ጉዳይ እንዳያመጣ ሥጋት አለኝ፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ደሳለኝ አላምሬ የተባሉት ብልፅግና ፓርቲ ተወካይ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምንጩ ያልታወቀ ሀብት እየተሰበሰበ እንደሆነ ተናግረው፣ ይህ ሀብት ሕጋዊ በሆነ መንገድ መዳኘት አለበት ብለዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ በሰጡት ምላሽ፣ የምክር ቤቱ የመጀመሪያ ድርሻና ኃላፊነት የሕግ ክፍተቶች ካሉ ክፍተቱን መሙላት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የእኛ ድርሻ የሚሆነው የሕጉ አፈጻጸም አሳሳቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕግ ክፍተት የሚታዩባቸውን ቦታዎች መሙላትና አስፈጻሚ አካሉ ምቹ ሁኔታና ቁመና ላይ እንዲደርስ በመከታተልና በመቆጣጠር እንሠራለን፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ አዋጁ ሀብት የማፍራትና የማውረስ ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚፃረር ድንጋጌ የለውም ብለዋል፡፡ የሕጉ መነሻ አሥር ዓመት ወደኋላ ተብሎ የሚነሳውን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ፣ አሁን እጅ ላይ ያለው ንብረት የዛሬ አሥር ዓመት ከነበረ ሰነድና ማስረጃ ይቅረብ እንጂ ሰዎች ያፈሩትን ሀብት ያላግባብ የመውሰድ አንድምታ የለውም ብለዋል፡፡ ‹‹በግለሰቦች እጅ ያለ ምንም ማስረጃና መረጃ በርካታ ሀብቶች ተረጭተው ይገኛሉ፣ እነዚህ ሀብቶች ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
↧