Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

የሱዳን ጦር በአማጺያን ስር የነበረችውን ቁልፍ ከተማ መቆጣጠሩን አስታወቀ

$
0
0

የሱዳን ጦር በፈጥኖ ደራሽ ኃይል ቁጥጥር ስር የነበረችውን ቁልፍ ከተማ መያዙን አስታወቀ።የጦሩ ግስጋሴ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የሱዳን የእርስ በርስ ደም አፋሳሽ ጦርነት ትልቅ እመርታ ነው ተብሏል።የጦሩ ወታደሮች ዋድ ማዳኒ የተሰኘችው ከተማ ውስጥ ሲገቡ በርካቶች በጎዳናዎች ላይ ያላቸውን ደስታ ሲገልጹ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተጋሩ ይገኛሉ።የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜድቲ የደረሰባቸውን ሽንፈት ባስተላለፉት የድምጽ መልዕክት አምነዋል።ሄሜድቲ በዚህ ብስጭትና ቁጣ በተሞላው መልዕክታቸው ጦሩ ያደረሰባቸው ሽንፈት በአየር እና የኢራን ሰራሽ ድሮኖች የበላይነት ነው ብለዋል። ነገር ግን ሌላ ተጨማሪ 20 ዓመታት ቢፈጅም ድል እስኪቀዳጁ ድረስ በፍልሚያው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።ዋድ ማዳኒ አልጀዚራ የተሰኘችው ግዛት ዋና ከተማ ስትሆን ከሱዳን መዲና ካርቱም 140 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ዋድ ማዳኒ በርካታ ግዛቶችን የሚያገናኝ አውራ ጎዳናዎች ያላት እና በስልታዊ ማዕከላዊ ከተማነቷም ተጠቃሽ ናት። ጦሩ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሶስት ዓመታት በፊት በጋራ መፈንቅለ መንግሥት ቢያደርጉም ነገር ግን በመሪዎቹ መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ አገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች 20 ወራትን አስቆጥሯል። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሁሉንም የሱዳን ምዕራባዊ ዳርፉር ግዛት እና የሃገሪቱን ደቡባዊ ክፍል እንደተቆጣጠረ ነው። ጦሩ ደግሞ የሱዳን ሰሜናዊ እና ምስራቃዊ ግዛቶች እንዲሁም የመዲናዋ ካርቱምን የተወሰነ ክፍል ተቆጣጥሯል። ጦሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለማችን እጅግ የከፋ የመፈናቀል ብሎ በጠራው ቀውስ ዘጠኝ ሚሊዮን ያህል ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በጦርነት እየታመሰች ያለችው ሱዳን ወደ ከፋ የረሃብ ቀውስ እየገባች መሆኑን የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች ቡድን በቅርቡ ገልጿል። ረሃብ ወደ አምስት አካባቢዎች የተዛመተ ሲሆን 24.6 ሚሊዮን ወይም ግማሽ ያህሉ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ቡድኑ ገልጿል። በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የዘር ፍጅት እየፈጸመ ነው ሲል አመራሮቹ ላይ ማዕቀብ ጥሏል። የዳርፉር እና የደቡብ ኮርዶፋን ግዛቶች እጅግ አስከፊ የሆነ ጦርነት እየተካሄደባቸው ሲሆን በዚህም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ ተደፍረዋል እንዲሁም በታጣቂዎች ታፍነው ተወስደዋል። በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪየሎ በጦርነቱ እስከ 150 ሺህ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ በግንቦት ወር ተናግረው ነበር። በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል እየተደረገ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የተደረጉ የሽምግልና ጥረቶች ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>