በካሊፎርኒያ ያሉ የአየር ሁኔታ ትንበያ ባለሙያዎች በሎስ አንጀለስ ዙሪያ ያለውን የእሳት ቃጠሎ እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆነው ኃይለኛ ንፋሶች በዚህ ሳምንት እንደሚኖሩ አስጠንቅቀዋል።የእሳት አደጋ የመከላከያ ሠራተኞች በበኩላቸው በሦስት አካባቢዎች የተነሱ እሳቶችን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ባለሥልጣናቱ ቅዳሜና እሁድ በአንፃራዊነት የተረጋጋ ንፋስ የነበረ ቢሆንም ሳንታ አና የተሰኘው ኃይለኛው ንፋስ ከእሑድ ምሽት እስከ ረቡዕ ድረስ ድረስ እንደገና እንደሚነሳና በሰአት 60 ኪሎ ሜትር እንደሚጓዝ አስጠንቅቀዋል። ከንፋሱ መነሳት በፊት በከተማው ዳርቻ እየተቃጠሉ ያሉትን የፓሊሳድስ እና ኢተን የእሳቶች በመቆጣጠር ረገድ የተወሰነ ለውጥ ታይቷል። የአካባቢው የእሳት አደጋ ተከላካዮች ከሌሎች ስምንት ግዛቶች፤ ከካናዳ እና ከሜክሲኮ በመጡ ቡድኖች እየታገዙ ይገኛሉ። የሎስ አንጀለስ ግዛት የህክምና መርማሪ ቡድን እስከ እሑድ ድረስ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ቁጥር ወደ 24 ከፍ አድርጓል። ቢያንስ ሌሎች 16 የደረሱበት እንደማይታወቅ ባለስልጣናቱ ገልጸዋል። ከሟቾቹ ውስጥ 16ቱ ኢቶን የተሰኘው እሳት በተከሰተበት አካባቢ የተገኙ ሲሆን ስምንቱ ደግሞ በፓሊሳዴስ አካባቢ መሆናቸው ታውቋል። በሎስ አንጀለስ ዙሪያ ሦስት አካባቢዎች መቃጠላቸውን ቀጥለዋል።በአሁኑ ጊዜ ትልቁ እሣት የሚገኘው በፓሊሳድስ ሲሆን 9307 ሔክታር መሬትን ሲያቃጥል 11 በመቶውን መቆጣጠር ተችሏል። የኢቶን እሳት በትልቅነቱ ሁለተኛው ደረጃ ሲይዝ ከ5665 ሔክታር በላይ አቃጥሏል። 27 በመቶው በቁጥጥር ስር ውሏል። ከሞላ ጎደል በቁጥጥር ስር በዋለው በሃረስት እሳት 323 ሄክታር መሬት መቃጠሉ ታውቋል። እሳቱ በአሜሪካ ታሪክ አውዳሚው ለመሆን መቃረቡ ተገልጿል። የግል ትንበያ ተቋሙ አኩዌዘር በእሳት ቃጠሎው የተነሳ የደረሰውን ኪሳራ ግምት ወደ ከ250 እስከ 275 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል ሲል የቀድሞ ግምቱን በማሻሻል እሑድ ዕለት አሳውቋል። የእሳት አደጋ ሠራተኞቹ ትልቁን እሳት መቆጣጠር ቢጀምሩም ባለስልጣናት ግን ቀጣዮቹ ንፋሶች “አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ የንፋስ ሁኔታዎች” ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸው፤ መላው የሎስ አንጀለስ ግዛት በእሳት ስጋት ውስጥ ይገኛል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “እንደ አለመታደል ሆኖ እስከ ረቡዕ ድረስ አንዳንድ አስከፊ የንፋስ ሁኔታዎች ወደሚኖሩበት ወደ ከፋ የአደጋ ጊዜ እንመለሳለን” ሲሉ የፓሳዴና የእሳት አደጋ መከላከያ አዛዥ ቻድ አውጉስቲን ለቢቢሲ ተናግረዋል። “አንዳንድ ለውጥ ብናስመዘግብም መጨረሻው አሁንም ቅርብ አይደለም” ብለዋል። የሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ ኃላፊ የሆኑት ክሪስቲን ክራውሌይ በበኩላቸው የአደጋ ዞኖች አቅራቢያ ያሉ ነዋሪዎች ውጡ የሚል ትእዛዝ ከተሰጠ ለመውጣት እንዲዘጋጁ እና መንገዶችን ለአደጋ ከላከያ ሠራተኞች ክፍት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የ67 ዓመቷ የቶፓንጋ ካንየን ነዋሪ አሊስ ሁሱም ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ በአካባቢው የጀመረው አዲስ የእሳት ቃጠሎ በፍጥነት በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረ ቢሆንም እሷ እና ጎረቤቶቻቸው የንፋስ ፍጥነቱ ከፍተኛ ሊሆን የሚችልበት “ማክሰኞ እንዳስፈራቸው” ገልጸዋል። ውጡ የሚለውን ትዕዛዝ ወደ ጎን ብለው የቆዩት ሁሱም፤ ትንበያው በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረው አንጻር “ትንሽ የተሻለ ነው” ብለዋል። እሑድ ዕለት በሳን ፈርናንዶ እና በናሳ ጄት ፕሮፐልሽን ላብራቶሪ (ጄፒኤል) አቅራቢያ አዲስ የእሳት ቃጠሎ ተቀስቅሶ የአካባቢውን ነዋሪዎች ስጋት ላይ ጥሏል። የእሳት አደጋ ተከላካዮች በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ማዕከል እምብርት የሆነውን እና ከፍተኛ ሚስጥራዊ ቴክኖሎጂን የከበበውን የአንጀለስ ብሔራዊ ደን ውስጥ የተፈጠረን አዲስ እሳት እሑድ ዕለት በፍጥነት ማቆም ችለዋል። ነዋሪዎች እንዲወጡ ከታዘዙባቸው አካባቢዎች ዘረፋ የፈጸሙ ቢያንስ 29 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ሁለት ሰዎች ለመስረቅ ሲሉ የእሳት አደጋ ተከላካዮች መስለው ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል። የሎስ አንጀለስ ግዛት ፖሊስ የሆኑት ሮበርት ሉና እሑድ ዕለት በሰጡት በጋዜጣዊ መግለጫ፤ በአካባቢው የሚገኙትን 400 ወታደሮች ለማጠናከር ተጨማሪ የብሄራዊ ጥበቃ አባላት እንዲሰማሩ ጠይቀዋል። የካሊፎርኒያ ገዥ ጋቪን ኒውሶም አንድ ሺህ ተጨማሪ የብሔራዊ ጥበቃ አባላት እንደሚሰማሩ በኋላ ላይ አስታውቀዋል። “በማሊቡ አካባቢ በነበርኩበት ጊዜ የእሳት አደጋ ተከላካይ የሚመስል ሰው አየሁ። ተቀምጦ ስለነበር ደህና እንደሆነ ጠየቅሁት። በካቴና መታሰሩ አልገባኝም ነበር” ሲሉ ሉና ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “አለባበሱ ብቻ እንጂ የሚመስለው የእሳት አደጋ ሠራተኛ ባለመሆኑ ለሎስ አንጀለስ ፖሊስ አሰልፈን ሰጥተነዋል። ከቤት ውስጥ ሲሰርቅ ተይዟል። በስፍራው ያሉ ባልደረቦቻችን እንደዚህ አይነቶቹንም እያስተናገዱ ነው” ብለዋል። በደቡብ ካሊፎርኒያ ግዛት14 ሺህ የእሳት አደጋ ተከላካዮች በ84 አውሮፕላኖች እና በአንድ ሺህ 354 የእሳት አደጋ መኪናዎች በመታገዝ ላይ እንዳሉ ሉና ተናግረዋል።ከቤታቸው እንዲለቁ የተጠየቁ ሰዎች ቁጥር የቀነሰ ሲሆን ወደ 105 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች አሁንም በግዴታ እንዲለቁ የታዘዙ መሆናቸውን እና 87 ሺህ ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ።
የፌደራል የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ኤጀንሲ (ፌማ) ኃላፊ የሆኑት ዲን ክሪስዌል በእሑድ ዕለት ለሲኤንኤን እንደተናገሩት አሁንም ከፍተኛ ስጋት አለ።”ብዙ ሰዎች ወደ አካባቢው ተመልሰው ቤታቸውን ለማየት እንደሚፈልጉ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ንፋሶች በሚነሱበት ጊዜ በየትኛውን መንገድ እንደሚጓዙ አይታውቅም” ብለዋል።የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ኃላፊ ጂም ማክዶኔል በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቤታቸውን እንዲመለከቱ የተገደበ ፈቃድ ተሰጥቶ ነበር። በኋላ ላይ ግን ባልደረቦቻቸው ሁሉም ነዋሪዎች እንዳይመለሱ እየከለከሉ መሆናቸው ተነግሯል።

ባለሥልጣናት የሰው አልባ አውሮፕላን ባለቤቶች በእሳት አደጋው አካባቢዎች እንዳያበሩ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ የሰጡ ሲሆን አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን ወሳኝ ከሆነ አውሮፕላን ጋር በመጋጨቱ መረጃ እያሰባሰቡ ይገኛሉ። አንድ ትንሽ ሰው አልባ አውሮፕላን ሐሙስ ዕለት የእሳት አደጋ መከላከያ አውሮፕላኖች ተጽዕኖ ፈጣሪከሆነው እና “ሱፐር ስኮፐር” በመባል ከሚታወቀው አውሮፕላን ጋር በመጋጨቷ ኤፍቢአይ ፎቶዋን አጋርቷል። አውሮፕላኑ ለተወሰነ ጊዜ ቆሞ ከሥራ ውጭ እንዲሆን ተገዶ ነበር ተብሏል።ሰው አልባ አውሮፕላኑ በአውሮፕላኑ ቀዳዳ መፍጠሩ ታውቋል።

ባለሥልጣናቱ ተጎጂዎችን ተጠቅመው ለማጭበርበር የሚሹ አካላት መኖራቸውን እና የዋጋ ጭማሪ ሲያደርግ የተገኘ ማንኛውም ሰው በህግ እንደሚጠየቅም ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በካሊፎርኒያ ገዥ ኒውሰም እና በተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል ያለው አለመግባባት አሁንም እንደቀጠለ ነው። ጥር 12 ላይ ዋይት ሃውስ እንደሚገቡ የሚጠበቁት ትራምፕ እሳቱን አደጋ ስፍራ እንዲጎበኙ ጥሪ ቢቀርብላቸውም “ብቃት የጎደላቸው” ያሏቸውን ፖለቲከኞች “በአገራችን ታሪክ ውስጥ ከታዩት አስከፊ አደጋዎች ለአንዱ” ተጠያቂ አድርገቸዋል።ዲሞክራት አባሉ ኒውሰም በበኩላቸው ስለእሳቱ የተሳሳተ መረጃ እያሰራጩ ነው በማለት ትራምፕ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
ዜና ምንጭ BBC NEWS