Clik here to view.

አወዛጋቢ ፅሑፎች በመለጠፍ የሚታወቁት የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ራሳቸውን ከኤክስ ማግለላቸውን አስታወቁ። የ50 ዓመቱ ጀኔራል ወታደራዊ ፕሮቶኮል በመጣስ ፖለቲካዊ አስተያየቶች በመስጠት ይታወቃሉ። ለወትሮው ይህን የሚያደርጉት በቀድሞው ስሙ ትዊተር አሁን ኤክስ እየተባለ በሚጠራው ማኅበራዊ ድር ነው። ከአውሮፓውያኑ 1986 ጀምሮ ሥልጣን ላይ ያሉትን አባታቸውን ሊተኩ አስበዋል የሚሉ ጭምጭምታዎችም አሉ። በቅርቡ ቦቢ ዋይን የተባለውን የሀገሪቱን ቀንደኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ “አርደዋለሁ” የሚል ማስፈራሪያ መለጠፋቸው ቁጣ ቀስቅሶ ነበር። ባለፈው አርብ ጀኔራል ሙሁዚ ለመጨረሻ ጊዜ በለጠፉት መልዕክት “አሁን ይህን ትቼ [ወታደራዊ] ሥራዎች ላይ ማተኮር ያለብኝ ጊዜ ነው” በማለት ለአንድ ሚሊዮን ተከታዮቻቸው ተናግረዋል። ነገር ግን ጀኔራሉ የኤክስ ገፃቸውን ሲዘጉ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። በአውሮፓውያኑ 2022 ሁለተኛ አልመለስም ብለው ቃል ከገቡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተመልሰዋል። ወታደራዊ ፕሮቶኮል በመጣስ አወዛጋቢ የሆኑ ፖለቲካዊ አስተያየቶችን ይሰጣሉ ሲሉ ብዙዎች ትችት ይሰንዝሩባቸዋል። በ2022 ጎረቤት ሀገር ኬንያን እወራለሁ የሚል ሐሳብ መስጠታቸውን ተከትሎ አባታቸው ሙሴቬኒ ጣልቃ ገብተው ይቅርታ መጠየቃቸው የሚዘነጋ አይደለም። ጀኔራል ሙሁዚ በቅርቡ የቦቢ ዋይንን “ጭንቅላት እቆርጣለሁ” ሲሉ የለጠፉት መልዕክት ከሀገሪቱ ዜጎች ትችት እንዲጎርፍባቸው ምክንያት ሆኗል። ምንም እንኳ ጀኔራሉ አስተያየታቸው ቀልድ ቢጤ ነው በሚል ይቅርታ ቢጠይቁም ቦቢ ዋይን መሰል ዛቻዎችን እንደቀልድ እንደማይመለከት አሳውቋል። የኡጋንዳ መንግሥት ቃለ አቀባይ የጀኔራሉ መልዕክት “እንዲሁ የተሰጠ” እንጂ የሀገሪቱን ኦፊሴላዊ ፖሊሲ የማይወክል ነው ብለዋል። በዩክሬን ወረራ ወቅት ለሩሲያ የሚያደላ ፅሑፍ ለጥፈው ብዙ ተተችተዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ኡጋንዳ ለትግራይ ነው የምታግዘው ማለታቸውም ይታወሳል። ምንም እንኳ ጀኔራሉ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ያልተከተለ መልዕክት ቢያስተላልፉም አባታቸው ሙሴቬኒ ግን ልጃቸውን ከመከላከል ወደኋላ ብለው አያውቁም። ሙሴቬኒ “በጣም ጥሩ ጀኔራል” ሲሉ ይገልጿቸዋል። ጦር ሠራዊቱ በበኩሉ ሕገ-መንግሥቱ የሰጣቸው ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን እየተጠቀሙ ነው ይላል። ጀኔራሉ ለኤክስ ተከታዮቻቸው በላኩት የስንብት መልዕክት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በእምነታቸው ታግዘው እንዲሁም ወታደራዊ ግዳጃቸው ላይ ለማተኮር አቅደው እንደሆነ ተናግረዋል። “በጌታየ እየሱስ ክርስቶስ እርዳታ ይህን ማኅበራዊ ሚድያ ለመሰናበት ወስኛለሁ። አሁን በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት እሠራለሁ” ይላል መግለጫቸው። “ለተወደዳችሁ ተከታዮቼ ለ2014 ጀምሮ ላለፉት 10 ዓመታት ጥሩ ቆይታ አድርገናል” ሲሉም አክለዋል። ተከታዮቻቸው “ታላቁ የፅናት ጀኔራል” የሆኑት አባታቸው ሙሴቬኒን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል። ጀኔራል ሙሁዚ አባታቸው ሙሴቬኒን ይተካሉ ብለው የሚያምኑ በርካቶች ቢሆኑም አባታቸው ግን ይህ እውነት አይደለም ብለው ያውቃሉ። በ1999 ጦር ሠራዊቱን የተቀላቀሉት ሙሁዚ በአስገራሚ ፍጥነት ነው የጀኔራልነት ማዕረግ ያገኙት። የኡጋንዳ ሚድያ ይህን “የሙሁዚ ፕሮጀክት” ሲል ይጠራዋል።
ዜና ምንጭ BBC NEWS https://www.bbc.com/amharic/articles/crked2z1mnko