Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

በ1.5 ቢሊዮን ብር ይገነባል የተባለው የመንገድ ፕሮጀክት ሁለት የመንግሥት ተቋማትን እያወዛገበ ነው

$
0
0

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንና አማካሪው የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከአራት ዓመታት በፊት በ1.5 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ውል በተገባበት 65.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ፕሮጀክት ምክንያት ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ታወቀ። ‹‹የአላባ – ዳምቦያ – ዱራሜ – አንጌቻ ዋቶ መንገድ በሚል ስያሜ ለሚጠራውና በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ቀጣሪነት ለሚያከናወነው የመንገድ ግንባታ አማካሪ ድርጅት ሆኖ የተሾመው የመንግሥት ተቋም፣ የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበበልኝ መኩሪያ፣ እ.ኤ.አ ጥቅምት 10 ቀን 2024 በተጻፈና ሪፖርተር በተመለከተው የቅሬታ ደብዳቤ (Dissatisfaction Letter)፣ ሥራ ተቋራጭ የሆነው የኮርፖሬሽኑ የግንባታ ክንውን አጥጋቢ ከሚባለው በእጅጉ ያነሰ መሆኑ ተገልጿል። የመሥሪያ ቤት ደብዳቤ መለያ ቁጥራቸውና ተደራሽ የሆኑበት ቀን በዝርዝር የተቀመጡ 30 የግንባታ አፈጻጸም ቅሬታዎች፣ እንዲሁም ከትራፊክ አስተዳደርና ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ የግንባታ ሥራዎችን አፈጻጸም የተመለከቱ 19 ደብዳቤዎች አማካሪው ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን መጻፉን ደብዳቤው አስታውሷል። ከዚህ ባለፈም እጅግ የዘገየ ነው የተባለውን የግንባታ አፈጻጸም ለማሻሻል በነሐሴ አጋማሽ 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሦስቱ አካላት ውይይት ማድረጋቸውን፣ እንዲሁም በግንቦት ወር ዳምቦያ በሚገኝ የሥራ ተቋራጩ ቢሮ (Site Office) በተመሳሳይ የተደረጉ ምክክሮች ውጤት አለማስገኘታቸውም ተብራርቷል። ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በደብዳቤው፣ በመስከረም ወር በግንባታ ጣቢያዎቹ በአካል ተገኝቶ ምልከታ ያደረገ የክትትልና የቁጥጥር ቡድን አባላት ያቀረቡት ሪፖርት፣ በወቅቱ በግንባታ አካባቢው የነበረው የአየር ሁኔታ ለግንባታ አመቺ ቢሆንም፣ ለግንባታ ወሳኝ የሚባሉ የሥራ ክፍሎች በጊዜያዊነት ሥራ አቋርጠው መመልከቱንና ይህም የሆነው በሥራ ተቋራጩ ምክንያት መሆኑን አሳውቋል። የክትትልና የቁጥጥር ቡድኑ በመስክ ምልከታው በግንባታ ጣቢያዎች የሲሚንቶና የነዳጅ እጥረት መኖሩን፣ ለግንባታዎቹ ወሳኝ፣ በቂ የሆነ የተማረና ያልተማረ የሰው ኃይል በሥፍራው አለመገኘቱን፣ የሥራ ተቋራጩ ቁልፍ የሆኑ የግንባታ ቁሳቁሶችን (ግሬደር፣ ሮለር፣ የውኃ ተሽከርካሪዎች፣ ሎደሮች፣ ኤክስካቫተሮች፣ ዶዘሮችና የመሳሰሉትን) በበቂ ሁኔታ አለማጓጓዙን ሪፖርት ማድረጉ በአማካሪው ደብዳቤ ተጠቅሷል።  የግንባታ ቁሳቁሶችና የሰው ኃይል ለረዥም ጊዜያት ያለ ሥራ ተቀምጠዋል ያለው ደብዳቤው፣ ይሁንና በቅርብ ጊዜያት የተወሰነ እንቅስቃሴ የታየበት የመንገድ ዳር ተፋሰስ ሥራም እየተከናወነ ያለው በሁለት ግንበኞች ብቻ በመሆኑ፣ ‹‹በቀን ከአሥር ሜትር ያልበለጠ አጥጋቢ ያልሆነ አፈጻጸም የታየበት ነው፤›› ብሏል። ‹‹በአንድ በኩል በቅርቡ የቀረበውን ሲሚንቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የሰው ኃይል በግንባታ ሥፍራው የለም፤›› ያለው አማካሪ ድርጅቱ፣ በሌላ በኩል የሥራ ተቋራጩ ያሉትን ሥራዎች መጠን የሚስተካከል ብዛት ያለው ሲሚንቶና ነዳጅ እያቀረበ አይደለም ብሏል። በእነዚህ ምክንያቶች ሥራ ተቋራጩ አራት ዓመታት ባለፈው የግንባታ ቆይታው እስከ መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ማከናወን የቻለው 18.70 በመቶውን ብቻ መሆኑን ጠቅሶ፣ ግንባታው መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ 271 በላይ የሥራ ቀናት ማሳለፉን ጠቁሟል፡፡ በኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው የተፈረመው ደብዳቤ፣ ‹‹ከካሳ ክርክር ጉዳዮች ነፃ ተደርጎ ለግንባታ ከተላለፈው 37 ኪሎ ሜትር አንፃር ሲታይ፣ የተመዘገበው እጅግ ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም መሆኑና መታገስ ከሚቻለው በላይ ነው። ይህም የሥራ ተቋራጩ አሁን ሥራዎቹን እያከናወነ ባለበት ፍጥነት ከቀጠለ፣ በውል የገባውን ግዴታዎቹን መወጣት እንደማይችል ይጠቁማል፤›› ይላል። ሁኔታውን በተመለከተ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አንድ ኃላፊ በበኩላቸው፣ ተቋማቸው ግንባታው በተቻለ መጠን ሁሉ እየተከናወነ ነው ብለው፣ አብዛኞቹ ቅሬታዎች መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ካለመገንዘብ የሚመነጩ ናቸው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ‹‹የኅብረተሰቡን ቅሬታ እንረዳለን፡፡ መንገዱ ከምባታ፣ ሐዲያና ሃላባን የሚያገናኝ ወሳኝ እንደ መሆኑ ቶሎ እንዲጠናቀቅ ያለው ፍላጎት ይገባናል፡፡ እኛም ብንሆን ቶሎ ማጠናቀቅ ነው የምንፈልገው። ምክንያቱም አሁን ግንባታው እየተራዘመ መጥቶ ለኮርፖሬሽኑ ኪሳራ እስከ መሆን ደርሷል። እስካሁን ድረስ ከቀጣሪው የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግም አልተጠየቀም፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅት እንደ መሆኑ ብዙ ችግሮችን ተሸክሞ ነው መንገዱን እየገነባ ያለው፤›› ብለዋል። በተለይም በቅርብ ወራት ግንባታው እየተፋጠነ ነው ብለው፣ በአማካሪው አለ የተባለውን የሰው ኃይል እጥረት፣ በቂ ያልሆነ የሲሚንቶና የነዳጅ አቅርቦት፣ እንዲሁም የግንባታ አቅርቦትና ማጓጓዝ ችግሮች ግን ሐሰት ናቸው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ የበጀት፣ የዕቃዎችና የመሣሪያዎች ወይም የሰው ኃይል እጥረት የለብንም ካሉ በኋላ፣ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ፈተና የሆነው የካሳ ክፍያዎች ጉዳይ (Right of Way Issues) በጊዜው ተጠናቀው አለመተላለፋቸው ነው ሲሉም አክለዋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ መንገዱ 65.1 ኪሎ ሜትር ከሆነ ወደ ግንባታ ስንገባ የካሳ ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ አልቆ ነው መረከብ ያለብን። ይሁንና ከዚህ ጉዳይ ነፃ ነው ከተባለው መንገድ ግንባታ አንፃር እንኳን ሲታይ፣ እኛ ጋ ያለው መረጃ የሚያሳየው 65 በመቶ ግንባታ አከናውነናል። ነገር ግን የካሳ ጉዳይ ያልተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች ፈተና ሆነውብናል፤›› ብለዋል። ይሁንና አማካሪ ድርጅቱ የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ደብዳቤ፣ የሥራ ተቋራጩ ከካሳ ጉዳዮች ነፃ ከተደረገለት 37 ኪሎ ሜትር ውስጥ፣ እስካሁን ግንባታውን ያከናወነው የአራት ኪሎ ሜትር የንዑስ – ቤዝ (Sub – Base Layer) ሥራ ብቻ መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪም የሥራ ተቋራጩ በአራት ዓመታት ቆይታው አላከናወናቸውም ከተባሉት ሥራዎች መካከል፣ በፕሮጀክቱ ውስጥ የተካተቱ አሥራ ሦስት ድልድዮች ግንባታ በፍፁም አለመጀመር፣ ከ18 የወለል ንጣፎች (Slab Culverts) መካከል አንድ ብቻ የተሠራ መሆኑን፣ ከ52 የቧንቧ መስመሮች (Pipe Culverts) ውስጥ 13 ብቻ መሠራታቸው ተገልጿል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አጠቃላይ ከተመደበው 1,566,019,570 ብር ውስጥ፣ ለግንባታ ሥራው ጅምር የሚያስፈልጉት የግንባታ ግብዓቶች ለማጓጓዝና ሥራ ለማስጀመር ብቻ የሚሆን 311,775,660.90 ብር ቅድመ ክፍያ ለሥራ ተቋራጩ ማስተላለፍን ጨምሮ እስካሁን ባለው ሒደት የሚጠበቁበትን የውል ግዴታዎችን መወጣቱን አማካሪ ድርጅቱ በደብዳቤው ገልጿል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአፋጣኝ ስህተቶቹን እንዲያርምና ግንባታውን በፍጥነት ወደማከናወን እንዲመለስ የሚያስችለውን የማገገሚያ ዕቅድ እንዲያቀርብ ከአማካሪ ኮርፖሬሽኑ ምክር ቢያቀርብም፣ ቃል ከመግባት በዘለለ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ጠቅሶ የቅሬታ ደብዳቤው ከደረሰው ዕለት ጀምሮ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ካልተሻሻለ፣ በገባው ውል መሠረት ዕርምጃዎችን ወደ መውሰድ እንደሚሸጋገር አሳውቋል። ደብዳቤው ከተጻፈ ሁለት ወራት ቢያልፉም በኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽኑ ላይ የተወሰደ ዕርምጃ እንደሌለ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኃላፊ አረጋግጠዋል፡፡ በሌላ በኩል ከሌሎች ምንጮች መረዳት እንደተቻለው የመንገዶች አስተዳደር ቀጣይ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ፣ የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን ሪፖርት እየተጠባበቀ እንደሚገኝ መረዳት ተችሏል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>