Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 937

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ይፋ መደረጉ ተሰማ

$
0
0

መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ የተወሰኑ የውጭ ሚዲያዎችና ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ የአገር ውስጥ የግል ሚዲያዎች ብቻ እንዲዘግቡት በተደረገው፣ የኢትዮጵያን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ዓርብ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ ተደረገ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት፣ ‹‹ለኢኮኖሚና ለፋይናንስ ምኅዳራችን ታሪካዊ በሆነ እጥፋት፣ የኢትዮጵያን የመጀመሪያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ደወል ደውልናል። ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ባላት፣ ለብልፅግና ሰፊ ዕምቅ አቅምና ምቹ መንገድ እየተነጠፈላት ባለችው ኢትዮጵያ ሙዓለ ነዋይዎን ያፍሱ፤›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓላ ገበያ ሥራ መጀመር ባብዛኛው የዘርፉ ባለሙያዎች ‹‹ታሪካዊ›› በመባል የተሞካሸ ሲሆን፣ ባንኮች ሊያደርሱት አልቻሉም የተባለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በመፍታት የምጣኔ ሀብት ዕድገቱን ያፋጥናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የሰነደ ሙዓለ ገበያ አክሲዮኖች፣ የዕዳ ሰነዶችና ሌላ ማንኛውም በሀብት የተደገፈ ሰነደ ሙዓለ ነዋይ ዓይነት መብት ጥቅም ወይ ሰነድ፣ በአሁናዊ ሰዓት (Real-time) እንዲሻሻ የሚያስችል፣ እስከዛሬ በኢትዮጵያ ካለው የአክሲዮኖች አሻሻጥ የተለየ በቴክኖሎጂ ብቻ የተደገፈ የገበያ ሥርዓት ነው፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሰሃራ በታች በቀዳሚዎቹ የሚመደብ ምጣኔ ሀብትና የሕዝብ ብዛት ቢኖራትም፣ የሰነደ ሙዓለ ገበያ ከሌላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ሆና ቆይታለች፡፡ በንጉሡ የመጨረሻ አሠርት ዓመታት፣ ኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ገበያ ብታቋቋምም፣ ሶሻሊስታዊ ደርግ ካገደው በኋላም ልማታዊው ኢሕአዴግም ለማስጀመር ፍላጎት አልነበረውም፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት የማድረግና በርካታ የማሻሻያ ዕርምጃዎችን መውሰዱን ተከትሎ የሰነደ ሙዓለ ገበያም ሊጀምር ችሏል፡፡ በተለይ በባለፉት 30 ወራት ውስጥ በርካታ ዝግጅቶች ሲደረጉ የከረሙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባልሥልጣንና የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የተቋቋሙና በርካታ ሕጎች የፀደቁ ሲሆን ገበያውን ለማስጀመር በርካታ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ በሰነደ ሙዓለ ገበያው ላይ ከዘጠኛ በላይ ብቃት ያላቸው ድርጅቶች አክሲዮኖቻቸውን እንዲሸጡ ዕቅድ መያዙን ሪፖርተር በዝግጅቱ ወቅት ከነበሩ ምንጮች ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ ድርጅቶቹም በአብዛኛው ባንኮች፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችና ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ (IFRS) እና ግልጽና ተጠያቂ መዋቅር ያላቸው ድርጅቶች ይሳተፉበታል፡፡ ወጋገን ባንክ ከግል ባንኮች የመጀመሪያ በመሆን መካተቱን (LISTED) ተገልጿል፡፡ ከአምስት ያላነሱ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አክሲዮኖቻቸውን በሙዓለ ገበያው ላይ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ይህም የቴሌን አሥር ከመቶ ያካትታል፡፡ ‹‹ዛሬ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ገበያን የማስጀመሪያ ደወል ደውለናል፡፡ ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብትና የፋይናንስ አቅርቦት ይህ ታሪካዊ ወቅት ነው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሙዓለ ገበያ ነው፡፡ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ይህ ትልቅ ማበረታቻ ነው፤›› ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ካሳሁን በበኩላቸው፣ ‹‹በዘርፉ ናይጄሪያና ግብፅ ከደረሱበት ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከአምስት አሥርት ዓመታት ቆይታ በኋላ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ  በይፋ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ 500 ሚሊዮን ብር (አራት ሚሊዮን ዶላር) ለመሰብሰብ አቅዶ፣ ከ1.26 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም ወደ አሥር ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ መሰብሰቡን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ማስታወቅቸው ይታወሳል።

ዜና ምንጭ ሪፖርተር https://www.ethiopianreporter.com/137335/


Viewing all articles
Browse latest Browse all 937

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>