Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

በጋዛ ጦርነት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር እስካሁን ከተገለጸው በላይ ከፍተኛ መሆኑን ጥናት አመለከተ

$
0
0

ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው የጋዛ ጦርነት የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እስካሁን ካወጣው በከፍተኛ ሁኔታ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ‘ዘ ላንሴት’ በተባለው ታዋቂ የህክምና መጽሔት ላይ የወጣ ጥናት አመለከተ።

ጥናቱ በዩናይትድ ኪንግደም መሪነት የተካሄደ ሲሆን፣ ሐማስ በእስራኤል ላይ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት የመጀመሪያዎቹን ዘጠኝ ወራት ጊዜን የሚሸፍን ነው። ጥናቱ የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ያወጣውን መረጃ፣ ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎች በበይነ መረብ ላይ የሚያጋሩትን እና የሐዘን መግለጫዎችን በመጠቀም የተቀናበረ ነው። በዚህም መሠረት ከመስከረም መጨረሻ አስከ ሰኔ መጨረሻ 2016 ዓ.ም. ድረስ 64,260 ፍልስጤማውያን በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ምክንያት ለህልፈት ተዳርገዋል፣ ይህም ማለት በወቅቱ በጦርነቱ ተገድለዋል ተብሎ ይፋ የተደረገው አሃዝ በ41 በመቶ ያነሰ መሆኑን አመልክቷል። በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ “ከጋዛ የሚወጣ ማንኛውም መረጃ ሊታመን የሚችል አይደለም” በማለት ለሐማስ የሚያደላ ነው ብሏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የሚወጣውን አሃዝ አስተማማኝ ነው በማለት ይቀበለዋል። የጤና ሚኒስቴሩ የሚያወጣው የሟቾች አሃዝ ሰላማዊ ሰዎችን እና ተዋጊዎችን ለይቶ የማያስቀምጥ ቢሆንም፣ በቅርቡ በመንግሥታቱ ድርጅት የወጣ ሪፖርት እንዳመለከተው በስድስት ወራት ውስጥ የጦርነቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸው ተረጋግጧል። የሐማስ መረጃ የሚታመን አይደለም የምትለው የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባለፈው ነሐሴ “ከ17 ሺህ በላይ ሽብርተኞች ተደምስሰዋል” ቢልም እዚህ ቁጥር ላይ እንዴት እንደረሰ ግን ግልጽ አይደለም። ጦሩ በጋዛ ዘመቻው ዒላማ የሚያደርገው ተዋጊዎችን ብቻ እንደሆነ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ወይም ዝቅተኛ እንዲሆን እንደሚጥር ገልጿል። እስራኤል እስካሁን ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን በነጻነት ወደ ጋዛ እንዲገቡ ስላልፈቀደች በቦታው እየሆነ ያለውን እውነታ በገለልተኝነት ለማረጋገጥ አዳጋች አድርጎታል። በጦርነቱ የተገደሉት ሰዎች አሃዝ እስካሁን እየተገለጸ ካለው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ያመለከተውን ጥናት የሠራው የባለሙያዎች ቡድን በሌሎች ጦርነቶች የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ለማወቅ ጥቅም ላይ የዋለውን ዘዴ ጥቅም ላይ አውሏል። በጋዛው ጦርነት የተገደሉትን ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ለማግኘት በተደረገው ሙከራ ወቅት ተመራማሪዎቹ ምን ያህል መደጋገም ሊከሰት ይችላል የሚለውንም ተመልክተዋል። በዚህም በጦርነቱ በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር የጋዛ ጤና ሚኒስቴር የሆስፒታል አሃዝን መሠረት በማድረግ ከሚያወጣው በእጅጉ ከፍ ያለ መሆኑ ተገልጿል። የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በየዕለቱ በጦርነቱ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር የሚያወጣ ሲሆን፣ መረጃውንም ከሆስፒታሎች፣ ከቤተሰቦች እና “ከአስተማማኝ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች” ነው የሚያሰባስበው። አጥኚዎቹ የሟቾችን በገመገሙት ጊዜ የጤና ሚኒስቴሩ 37,877 መገደላቸውን ያሳወቀ ሲሆን፣ ‘ዘ ላንሴት’ ላይ የታተመው ጥናት ግን በተመሳሳይ ወቅት የተገደሉት ሰዎች ከ55,298 እስከ 78,525 ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል። ዝርዝር የቴክኒክ ትንተናን መሠረት በማድረግ የሪፖርቱ አሃዞች ትርጉም በሚሰጥ ሁኔታ ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተጠቅሷል። ጥናቱ ጨምሮም በጦርነቱ ከተገደሉት መካከል ፆታቸው እና ዕድሜያቸው ከታወቁት መካከል 59 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች፣ ልጆች እና አዛውንቶች ናቸው። የጋዛው ጦርነት የተቀሰቀሰው ሐማስ ወደ እስራኤል ግዛት ዘልቆ በመግባት በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት 1,200 የሚሆኑ ሰዎችን ገድሎ ሌሎች 251 ሰዎችን በማገት ወደ ጋዛ ከወሰደ በኋላ ነው። ለዚህም ምላሽ እስራኤል ግዙፍ ወታደራዊ ጥቃት በጋዛ ላይ ከፍታ እስካሁን እያካሄደች ትገኛለች። የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን ከ46,000 በላይ አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ ሰዎች በእስራኤል ዘመቻ ጋዛ ውስጥ ተገድለዋል።

ዜና ምንጭ BBC NEWS


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>