Quantcast
Viewing all articles
Browse latest Browse all 938

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ይፋዊ ጉብኝት በአዲስ አበባ

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ብርቱ አለመግባባት ከተፈጠረ ከአንድ ዓመት በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በላይ በሁለቱ አገራት ብሎም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ ቆይቷል። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ቅዳሜ ጥር 3/2017 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ለሐሰን ሼክ ሞሐሙድ “እንኳን ወደ ኢትዮጵያ መጡ” በማለት መልዕክት አስፍረዋል። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ በሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በስፍራው ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል። ቀደም ብሎም የፕሬዝዳንት ሐሰን ጽህፈት ቤት – ቪላ ሶማሊያ ባሰራጨው መግለጫ የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአዲስ አበባ የሚያደርጉት ጉብኝት የሚካሄደው “በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግብዣ” መሠረት መሆኑን ጠቅሷል። አክሎም የጉብኝቱ ዓላማ በቅርቡ በሁለቱ አገራት መካከል አንካራ ቱርክ ውስጥ የተፈረመውን ስምምነት መሠረት በማድረግ “የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር እና የጋራ ጉዳዮች ላይ” ለመነጋገር መሆኑን በማመልከት፣ የታደሰው የሁለቱ አገራት ትብብር የአዲስ ምዕራፍ ጅማሬ ነው ብሏል። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ይፋዊ ጉብኝት ለምን ያህል ቀናት እንደሚቆይ እና ስለተያዙ መረሃ ግብሮች እንዲሁም ስለ ጉብኝቱ ዓላማ በኢትዮጵያ በኩል የተባለ ነገር የለም። ኢትዮጵያ ሶማሊያ የሉዓላዊ ግዛቴ አካል ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ የባሕር በር አጠቃቀም እና ዕውቅና መስጠትን ይሚለከታል የተባለውን የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር ከባድ ውዝግብ ውስጥ መግባቷ ይታወሳል። ስምምነቱ ሉዓላዊነቷን የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለተባበሩት መንግሥታት አቤቱታ ያቀረበችው ሶማሊያ፣ የኢትዮጵያን አምሳደር ከሞቃዲሾ በማስወጣት የራሷን አምባሳደር ከአዲስ አበባ ጠርታለች። በተጨማሪም ከ15 ዓመት በላይ በሶማሊያ ሰላም ሲያስከብር የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቷ እንዲወጣ ጠይቃ ነበር። በተጨማሪም ሶማሊያ ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ክሶች በተደጋጋሚ መሰንዘሯ አለመግባባቱ በአፍሪካ ቀንድ ሌላ ግጭት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሮ ቆይቷል። ነገር ግን የሁለቱም አገራት ወዳጅ በሆነችው በቱርክ በኩል ሲደረግ የነበረው ተከታታይ ጥረት ውጤት አፍርቶ በፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን አማካኝነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ሐሰን ባለፈው ታኅሣሥ መጀመሪያ ላይ ውጥረቱን የሚያረግብ እና ግንኙነታቸውን የሚያድስ ስምምነት ላይ መደረሳቸው መገለጹ ይታወሳል። ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን “ታሪካዊ” በማለት የጠሩት ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል “ሰላም እና ትብብር ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ” እንደሚሆን በመጥቀስ፣ መሪዎቹ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለማሥራት መስማማታቸውን የሚገልጽ ሰነድ ይፋ ተደርጎ ግንኙነታቸው ለመቀጠል ተስማምተዋል። ከሳምንታት በፊት ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ በኩል ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዳቸው ወደ ሌላኛው አገር በማቅናት ውይይት መደረጉ የተዘገበ ሲሆን፣ አሁን የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት ጉዞ ለስምምነቱ መጠናከር ጉልህ እርምጃ ነው።

ዜና ምንጭ BBC NEWS


Viewing all articles
Browse latest Browse all 938

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>