ሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ አኩሪ ታሪክ፣ ቀደምት የሥልጣኔ ባለቤትና ከ3000 ዘመን በላይ የመንግስትነት ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር ናት፡፡ የሰው ልጅ ዛሬ ለደረሰበት የዕድገትና የስልጣኔ ደረጃ መሰረት የሆኑ ቁሳዊና መንፈሳዊ ትውፊቶችን በማበርከት ለዓለም ስልጣኔ ታላቅ አስተዋፅዖ አበርክታለች,,
በየዘመናቱ ነፃነቷን ለማጥፋት የወረሯትን የውጭ ተስፋፊዎችና ቅኝ ገዥዎች በተደጋጋሚ ጊዜ ድል በማድረግ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷንም አስከብራ ኖራለች፡፡ ሀገራችንን በእብሪት ለመውረር የመጣውን የኢጣሊያን ወራሪ በመደምሰስ በዓለም ለመጀመሪ ጊዜ ጥቁር የሰው ልጅ ዘር ነጭ ወራሪዎችን ማሸነፍ እንደሚችል በአድዋ ታሪካዊ ድል ያስመሰከረች ብቸኛ የጥቁር ሰው ዘር መኩሪያና መመኪያ ሃገር ነች፡፡ ቅኝ ገዥዎችና ኢምፔሪያሊስቶች አፍሪካን ለመቀራመትና የተፈጥሮ ሃብቷን ለመዝረፍ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ስር ለማዋል በተደረገው ወረራ ተስፋፊዎችን በመመከት በቅኝ ገዥዎች ሥር ያልወደቀችና ለመላዉ ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌት ሐገር ነች፡፡ አብዛኛዎቹ አፍሪካዊ ሀገሮች ድንበሮቻቸውና ማንነታቸው በቅኝ ገዥዎች ፍላጎት እንዲወሰን ሲደረግ ሀገራችን ወራሪዎችን በመቋቋም የራሷን የድንበር ወሰንና ማንነት በራሷ መወሰን የቻለች ብቸኛዋ አፍሪካዊ ሀገር ናት፡፡
በሃገር ውስጥም የንግድ መስመሮችንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለመቆጣጠር እንዲሁም አንዱ አካባቢ በሌላው ላይ የሥልጣን የበላይነትን ለመያዝ በርካታ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ተካሄደዋል፡፡ በየዘመናቱ በተካሄዱ በእነዚህ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ብዙ ህይወትና ንብረት ጠፍቷል፤ ብዙ ሰቆቃዎችም ተፈፅመዋል፡፡ በየጦርነቱ አሸናፊ የሆኑ ኃይሎችም ተሸናፊውን በማስገበር ከአንደኛው የሃገሪቱ ጫፍ እስከ ሌላኛው የሀገሪቱ ጫፍ ድረስ የግዛት መነሻቸውንና ስልጣናቸውን በማስፋፋት ሃገሪቱን ሲያስተዳድሯት ኖረዋል፡፡ በዚሁም ምክንያት የባህል የሃይማኖት የቋንቋና የልማድ ውርርሶች ከእንደኛው ወገን ወደሌላኛው ወገን በስፋት ተሸጋግረዋል፡፡ በጋብቻና በማህበራዊ ትስስሮችም የበርካታ ጎሳዎች ዉህደትና የስነ ልቦና ጥምረት እንዲዳብር ምክንያት ሆኗል፡፡ ሀገራችን የበርካታ ገፀ ምድርና ከርሰ ምድር ኃብት፣ አስደናቂ የተፈጥሮ ውበትና የሰው ልጅ ቀደምት ስልጣኔ መገለጫ የሆኑ ቅርሶች ባለቤት፣ ሰፊ መሬትና የሰው ኃይል ያሏት ታላቅ ሐገር ናት፡፡ ሀገራችን የተለያዩ የአየር ፀባያት ባለቤት ስትሆን ለሰው ልጅ መኖሪያና ለአዝርዕት መብቀያ ተስማሚ ተፈጥሮ በሰፊው የተለገሳት ሀገር ናት፡፡ በርካታ በጥቅም ላይ የዋሉና ገና ያልተነኩ የተፈጥሮ ስጦታየፈሰሰባትም ምድር ናት፡፡
ሆኖም የዚህ አኩሪ ታሪክ፤ ባህልና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት የሆነች ሃገራችን ዛሬ በቀሪው የዓለም ሕዝብ ፊት የምትታወቀው በርሃብተኝነት፣ በተመፅዋችነት፣ በስደትና በእርስ በእርስ ጦርነት ባለቤትነቷ ነው፡፡ የሰው ልጅ ዛሬ ከረደሰበት የአስተዳደርና የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ እንዳንደርስ ያደረገን በሃገራችን ተንሰራፈተው በቆዩና አሁንም ባሉ የአስተዳደርና የፖለቲካ ሥርዓት ብልሹነቶች ምክንያት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በፖለቲካ እድገት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚና በማህበራዊ እድገትም የዓለም ሃገራት የመጨረሻዎቹ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ሕዝቧ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶችን ተቀብሎ ለበርካታ ዘምናት ተቻችሎ የኖረ ቢሆንም ዛሬ እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያይና አንድነቱ እንዲላላ እየተደረገ ነው፡፡ ሃገራችን በተቀበለቻቸውና ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እውቅና ያገኙ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚያከብራቸውና የሚጠብቃቸው ባለቤት አጥተዋል፡፡ የኢኮኖሚ መርሃችንም በጥናትና በአስተማማኝ መሠረት ላይ ያልተጣለ በመሆኑ ካለንበት የድሕነት አዘቅት ሊያወጣን አልቻለም፡፡ ፍትኃዊ የንብረት ስርጭትና የሥራ እድል ባለመኖሩ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው የኑሮ ደረጃ እጅግ እየተራራቀ መጥቷል፡፡ ዜጎችም የዜግነት እኩልነት ክብራችን ተነፍገን አብዛኛዎቻችን በሃገራችን ጉዳይ ባይተዋር ሆነናል፡፡
ዛሬ የዚህ ትውልድ አካል የሆንን ዜጎች ይህንን የተዛባ አካሄድ የመቀየርና ሃገራችንን የተሻለች ሃገር የማድረግ ኃላፊነት አለብን ብለን እናምናለን፡፡ በመሆኑም የሰማያዊ ፓርቲያችን ራዕይ፣ ተልዕኮና ዓላማ ለሃገራችን ካለን ጥልቅ ፍቅር፣ለፍትሃዊ አስተዳደር መስፈን ካለን ፅኑዕ እምነትና ከሰው ልጅ ምክንታዊ አስተሳሰብ ይመነጫሉ፡፡ ፍትሕ እንዲሰፍን የምንፈልግ ሃገራችንንም በእውነት የምንወድ ከሆነና በሰው ልጅ ምክንያታዊ አስተሳሰብ የምንገዛ ከሆነ ችግሮቻችን በሰላማዊ መንገድ፣ በመነጋገር፣ በመደማመጥና በመግባባት ብሔራዊ እርቅና መከባበርን በመፍጠር የሚፈቱ ናቸው ብለን እናምናለን፡፡
ፓርቲያችን በሃገሪቱ ህገ-መንግስት መሠረት በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ትግል በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውስብስብና ፈርጀ ብዙ ችግሮች ተላቆ እያንዳንዱ ዜጋ በነፃነት ሃሳቡን የመግለፅ፣ የመደራጀት፣ የፈለገውን የመደገፍና የመቃወም፣ በፈለገው ሙያና የሥራ መስክ የመሰማራት፣ ሃብት የማፍራትና የሃብቱ ባለቤት የመሆን እንዲሁም የግል ስብዕናውን የማሳደግ መብቱ የተረጋገጠ እንዲሆን እንታገላለን፡፡ ሐገራችን ከድህነትና ከጦርነት የተላቀቀች፣ ፍትሕና ሰላም የሰፈነባት እንድትሆን የፖለቲካ ሥልጣን በመያዝ የዜግነት ድርሻችንን ለመወጣትና ራዕያችንን እውን ለማድረግ ሰማያዊ ፓርቲያችንን መስርተን ኑ በጋራ ጥላችንን እንሰባሰብ እንላለን፡፡
የምንታገልላት ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ አሁን ለምትገኝበት ችግር ዋነኛው ምክንያት ገዥዎች ለሀገር፣ ለህዝብና ለሉዓላዊነቷ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ሰማያዊ ይህን የተሳሳተ የገዥዎች አስተሳሰብ በተቃራኒ ለዜጎቿ ምቹ፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረና ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚያስፈልጉ ሀገራዊ እይታዎችን አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል፡፡ እነዚህም፡-
ሀ. ኢትዮጵያ ሀገራችን በኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ገዥነት ስር የሚገኘውን መሬት፣ ውሃ፣ የአየር ክልል፣ በከርሰ ምድርና በከርሰ ውኃ የሚገኘው ሃብት፣ በአየር ክልሉ ያለው የድምፅና የምስል ሞገድ ባለቤት ሉዓላዊ ሀገር ናት፡፡
ለ. የኢትዮጵያ ያልተመለሱ የድንበርና የይገባኛል ጥያቄዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የአስተዳደር ወሰን አሁን በኢትዮጵያ መንግስት ሥር የሚገኘውና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተመዘገበዉ ክልል ነው፡፡
ሐ. በኢትዮጵያ ውስጥና በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው፡፡
መ. የኢትዮጵያ ሕዝብም በኢትዮጵያ ጉዳይ ባለሙሉ የሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ ሃገሪቱን የማስተዳደር ሥልጣን ከሕዝብ ይመነጫል፡፡
ሠ. የኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ ሉዓላዊነት አይነጣጠሉም፤ለሌላም አይለቀቁም፡፡
ረ. ኢትዮጵያውያን በግል ያላቸው የዜግነት መብትም ሆነ በወል የሚጋሩት የህግ፣ የፖለቲካ የማህበራዊና የባህል መብት የአንድነታቸው ዓይነተኛ መሰረት ነው፡፡
ሰ. ኢትዮጵያ ሀገራችን የረጅም ጊዜ አኩሪ ታሪክ፣ የበርካታ ገፀ-ምድርና ከርሰ-ምድር ሃብት ባለቤት፣ አስደናቂ የተፈጥሮ ውበትና የሰው ልጅ ቀደምት ሥልጣኔ መገለጫ የሆኑ ቅርሶች ያሏት ታላቅ ሃገር ናት፡፡
ሸ. ሃገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ወግና ሥርዓት አሸብርቃ የኖረች፣ በብዙ ዓይነት ሃረጎች ተሳስረውና በታሪክ ተቆራኝተው የጋራ አመለካከትና ኢትዮጵያዊ ማንነትን በማዳበር ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው በአንድነት የኖሩ ዜጎች ሃገር ናት፡፡ እነዚህ ዜጎች በየዘመናቱ የተለያዩ አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና ደርሶባቸዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን የዜጎች የአስተዳደርና የፍትህ ጥያቄ በአግባቡ አልተፈታም ወይም መብታቸው አልተከበረም፡፡ በመሆኑም ሁሉም ዜጎች የዜግነት መብታቸው እንዲከበርና በሃገር ጉዳይ ላይ ተገቢው ድርሻና ተሳትፎ እንዲኖራቸው አሁንም ፅኑ ትግል የሚያስፈልጋት ሃገር ናት፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ኑ ራሳችንን ነፃ በማውጣት የሀገራችንን እጣ ፈንታ እንወስን!
* ሰላም – አንድነት – ተስፋ *
የአብሮነት የከለላና የዋስትና ምልክት በሆነው ጃንጥላ መሰባሰብ ምርጫዎ ይሁን!
