ሆኖም ግን እየሆነ ያለው የዚህ ተገላቢጦሽ ነው፡፡ እየተሮጠ ያለው ጥያቄ እንደሌለው ጥሩ ነገር ተደርጎ አፍሪካን አንድ አድርጎ የሚያስተዳድር አንድ መንግስት ለመመስረት ነው፡፡ ኒሮ የተባለው እብድ የሮም ንጉስ የሮም ሕዝብ አንድ አንገት ብቻ በኖረውና በቀላሁት ነበር በሚል አባባሉ ይታወቃል፡፡ ሃገሮች ሉዓላዊነታቸውን አሳልፈው ክፍለ ዓለሚቱን ለሚያስተዳድር ቢሮክራሲ ሲያስረክቡ ሕዝቦቹ ከሚጠቀሙት ይልቅ የሚያጡት ይበዛል፡፡ እርስ በእርስ ወደ ጦርነት ላለመግባት በኢኮኖሚያዊ ጥቅም መተሳሰር እና ጠቅልሎ ሉዓላዊነትን አሳልፎ መስጠት ለየቅል ናቸው፡፡
አንድ አፍሪካ?
ፖለቲካዊ ውሕደት ያላት አፍሪካን ለመገንባት “አብዮተኛ” ልጆቿን ቀድመው የጀመሩት በ19ኛው ክ/ዘመን ጠቅልለው ቅኝ ሊገዙ የመጡት ወራሪዎች ነበሩ፡፡ የአፍሪካ ቅርምት እየተባለ በሚታወቀው ወረራቸው ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ፖርቱጋል፣ ቤልጄም እና በኋላ ላይ ደግሞ ጣልያን እና ጀርመን አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ተቆጣጥረው፣ አንዳቸው የሌላቸው አንድ የማድረግ ሕልም እንቅፋት ሁነዋል፡፡ ስለዚህም በግዜው አፍሪካን አንድ አድርጎ የመግዛት ሕልማቸው በእርስ በእርስ ፍክክራቸው ሳብያ ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
አብዮተኞቹ ልጆቿ በ20ኛው ክ/ዘመን አንድ እናደርጋታለን ብለው ሲነሱ ፓን አፍሪካዊነት የሚባል ርዕዮት አነግበው ነበር፡፡ ይህ ርእዮት መላ አፍሪካውያን ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚጠራ ሲሆን ለኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ሽግግር አንድነት አስፈላጊ ነው በሚል እምነት ላይ ተመስርቶ አፍሪካውያንን ለማዋሃድ የሚሰራ ነው፡፡ ርእዮቱ አፍሪካውያን አንድ አይነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን እጣቸውም የተሳሰረ ነው ይላል፡፡ በዚህም መሰረት አፍሪካውያን ከቅኝ ገዢዎች ነጻ በወጡበት ማግስት ነበር ለመዋሃድ መጣደፍ የጀመሩት፡፡
የመጀመርያው አጠቃላይ ውሕደት ያስፈልጋል በሚሉት በጋናው ኩዋሚ ኑኩርማ እና በጊኒው ሴኩ ቱሬ እ.ኤ.አ. በ1958 ዓ.ም የጋናና ጊኒን ህብረት በመፍጠር ጀመሩት፣ በ1961 ማሊ የታከለችበት ቢሆንም በቀጣዩ አመት ጥምረቱ ሊፈርስ ችሏል፡፡ የሚመራቸው ርእዮተ ዓለም ከፓን አፍሪካዊነት ጋር አስተሳስረው ማርክሲስታዊነት ነበር፡፡ ከዚህ የከሸፈ ሙከራ ቀጥሎ አፍሪካን አንድ ለማድረግ የሚወተውቱት እንዴት መሆን እንዳለበት ሳይስማሙ ቀርቶ በሁለት ቡድን ተከፍለው ነበር፡- ፓን አፍሪካዊነትን በማቀንቀን የሚታወቁት የጋናው ኩዋሚ ንኩርማ የሚመሩትና አልጀሪያ፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ማሊ እና ሊብያ የሚገኙበት የካዛብላንካ ቡድን እና የሴኔጋሉ ሊዮፖል ሴዳር ሴንግሆር የሚመሩት ናይጄርያ፣ ላይቤርያ እና ኢትዮጵያ የተቀበሉት የሞነሮቭያ ቡድን ነበር፡፡ የካዛብላንካው አጠቃላይ ውህደት እንዲደረግ ሲሉ የሞነሮቭያው ቡድን ደግሞ ፖለቲካዊ ውህደቱን ያልተቀበለው ሲሆን ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጥቅም የሚያስጠብቁ ትብብሮች እናድርግ ብለው ነበር፡፡ የመጀመርያዎቹ ተራማጅ፣ ማርክሲስታውያን ተደርገው የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሁለተኞቹ ደግሞ ካፒታሊስትና ብሔራውያን ነበሩ፡፡
በኋላ ላይ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፣ አዲስ አበባ ባደረጉላቸው ግብዣ ተገኝተው ልዩነታቸውን ሊፈቱ ችለዋል፡፡ ከዚህም በመከተል የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እ.ኤ.አ. በግንቦት 25፣ 1963 ዓ.ም መስረተዋል፡፡ ሲመሰረት ዓላማው ያደረገው የአፍሪካውያንን ትብብር ማጠናከር፣ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ ነጻነት ማስጠበቅ፣ ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ በጋራ መቆም፣ ቅኝ ግዛት ስር ያሉትን የነጻነት ትግላቸውን መርዳት እና በዓለም መድረክ ነጻ ወይም ገለልተኛ መሆን የሚሉ ናቸው፡፡ ይህ የአንዲትን ሃገር ሉዓላዊነት የማይዳፈር ሃሳብ እንደመሆኑ ንጉሱን ጨምሮ 32 መስራቾች ፊርማቸውን አኑረው ተቀብለውታል፡፡
ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ሕብረት?
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የቆመለት ዓላማ ያለፈበት ነው በሚል በ1990ዎቹ ድርጅቱ እንዲቀየር የሊብያው የቀድሞ መሪ ጋዳፊ ሲወተውቱ ከቆዩ በኋላ እ.ኤ.አ. በመስከረም 9፣ 1999 ዓ.ም በሲርጥ እወጃ የአፍሪካ ሕብረት እንዲመሰረት ተወሰነ፡፡ እ.ኤ.አ. በግንቦት26፣ 2001 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተመስርቶ፣ በሐምሌ 9፣ 2002 ዓ.ም ስራ እንዲጀምር በደርባን፣ ደቡብ አፍሪካ ታወጀ፡፡ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የአፍሪካ ሕብረት ስሙን ብቻ ሳይሆን ግቡንም ቀይሮ፣ የፓን አፍሪካዊነት ቅዥትን ጨምሮ ነበር የመጣው፡፡ ተቋሙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ውሕደት መፍጠር ግቡን አድርጎ የተመሰረተ ሲሆን ይህን ለማሳካትም በስሩ የተለያዩ ተቋማትን ፈጥሯል፡፡ በኢኮኖሚው የአፍሪካ ሕብረት ግብ ነጻ የንግድ ቀጠና፣ የቀረጥ ማሕበር፣ አንድ ገበያ እና አንድ ማእከላዊ ባንክ መመስረት ነው፡፡ የአፍሪካ ማእከላዊ ባንክ (በአቡጃ፣ ናይጄርያ)፤ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ባንክ (ትሪፖሊ፣ ሊብያ)፤ የአፍሪካ ሞኒታሪ ፈንድ (ያኦንዴ፣ ካሜሮን) የሚሆኑ ፋይናንሳዊ ተቋማት መስራች ኮሚቴ ተቋቁመው በተጠቀሱት ሃገራት ከትመዋል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት “አፍሮ”የተባለ አንድ የአፍሪካ የመገበያያ ገንዘብ እ.ኤ.አ. በ2023 ዓ.ም (ከአስር ዓመት በኋላ) የማስጀመር እቅድ አለው፡፡
ለዚህም ነው ዛሬ ላይ አፍሪካዊነትን የሚያወድስ ፕሮፖጋንዳ ያለማቋረጥ የምትሰሙት፡፡ በቻይና ስጦታ የቆመው አዲሱ የአፍሪካ ሕብረት መሰብሰብያ እና ቢሮዎች የያዘው ሕንጻ ሲመረቅ የፓን አፍሪካዊነት አውራ ሰው በሚል የኩዋሜ ንኩርማ ሃውልት ሲቆምለት፣ የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ሃውልት ባለመሰራቱ ኢትዮጵያውያን “ልሂቃንን” ያስከፋ ነበር፡፡ ባርነትህን መውደድ ይሉታል እንዲህ ነው፡፡ አፄ ኃይለ ስላሴ ዛሬ ቢኖሩ አሁን ባለው የአፍሪካ ሕብረት እንደማይስማሙ ማንም ማሰብ የሚችል ሰው የሚቀበለው ነው፣ ሃውልታቸው አለመሰራቱም እንደመልካም እንጂ እንደ መዘንጋት መታየት አልነበረበትም፡- በተዓምር መንግስታቸውን አሳልፈው “ለአፍረካዊ መሪ” አይሰጡም ነበርና፣ ቀድሞ የነበረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትንም ሲቀበሉ እንዲህ ያለውን የካዛብላካው ቡድንን ሃሳብ ሽረው ነበር፡፡ የሆነው ሁኖ አፍሪካውያኑ “ልሂቃን”በነጻነት ለዘመናት የኖረችው ሃገርን ለፓን አፍሪካዊነት ርእዮት ፕሮፖጋንዳ አስፍተው ስለሚጠቀሙባት ኢትዮጵያውያኑን ለማባበል የሆነ መፍትሄ ማበጀታቸው አይቀሬ ነው፡፡ (ይህን እውነት የሚያስታውሳችሁ አታገኙም፣ ዓለም አቀፋዊ አለቆቻቸው አይፈቅዱላቸውምና፡፡)
እ.ኤ.አ.በሐምሌ 2007 ዓ.ም በአክራ፣ ጋና በተደረገው ስብሰባ ላይ “የሞቀ ክርክር” ከተደረገበት በኋላ የሕብረቱን መንግስት (እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ) ለመመስረት የሚደረገው ጉዞ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውሕደት በማጠናከር ይበልጥ መሰራት እንዳለበት፣ በአፍሪካ ሕብረትና በቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ኮሚሽኖች መሃከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከርና የአፍሪካ መንግስት የሚመሰረትበት የጊዜ ገደብ እንዲቀመጥ የሚያዝ ውሳኔ አውጀዋል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ውህደት (አንድ ገንዘብ፣ ገበያና ማእከላዊ ባንክ) ለመመስረት መሯሯጡ ቀውስ ውስጥ የገቡትና በመቀላቀላቸው እየተቆጩ ያሉትን የዩሮ ዞን አባሎችን ልምድ አለማስተዋል ነው፣ በምን ስሌት ነው አንድ ህዝብ የራሱን ገንዘብ የማተም መብቱን (“የወርቅ እንቁላል የምትጥል ዳክዬን”) አሳልፎ መስጠቱ የሚጠቅመው? ሥልጣን ይበልጥ ወደታች እየወረደ በመሄድ ፈንታ በክፍለ ዓለም ደረጃ ማዋሃዱ ነጻነታቸውን ለማግኘት የተዋደቁ ሕዝቦችን በምን ስሌት እንደሚወክል አይገባም፡፡
“የአፍሪካ ህብረት ዋና ዘፈኑ ኋላ ቀር አፍሪካውያን ከበዝባዥ ምእራባውያን ነፃ መውጣት ከፈለጉ በህብረት ራሳቸውን ማጠንከር አለባቸው የሚል የተበዳይነት ስሜት በሚፈጥረው ቁጭት ጥቁሮች ለህብረት እንዲፋጠኑ የሚማፀን ነው፡፡ እውነቱ ግን ስልጣንን ወደ ላይ በመስቀል ተጠያቂነታቸው ግልፅ ያልሆነ አህጉራዊ ቢሮክራሲ በመፍጠር ዓለምን ለመግዛት ለሚሹ አፍሪካን አኮላሽቶ ለማስረከብ ያቀደ ይመስላል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ከሌሎች ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር በጥምረት የሚሰራ ሲሆን የነሱ ተላላኪ እንጂ አንድም የራሱ አቋም ያራመደበት ግዜ የለም፡፡ አሁን ደግሞ የአሜሪካ ሰራዊቶች በአፍሪካ እያደረጉ ካሉት መስፋፋት ጋር በጥምረት እየሰራ ይገኛል፡፡” ስለ አጠቃላይ ዓለም አቀፋዊ አካሄዱ
የሉላዊ አገዛዝ ደረጃዎች ይመልከቱ፡፡
ዓለምን አንድ አድርጎ ለመግዛት ያለው ቀጥተኛ ላልሆነ ቅኝ አገዛዝን ብቻ ነው ሕብረቱ የሚጠቅመው፡፡ ሲጀመርም አንድ አድርጎ ለመግዛት የሞከሩት ቅኝ ገዢዎች መሆናቸውን እናስታውስ፡፡ በአንድ አፍሪካ ስም ተታለው ወይም ከዓለም አቀፋውያኑ ጋር አብረው ሊሰሩ የሚችሉ መሪዎች ገሚሶቹ ፍሪ ሜሶን ሲሆኑ፣ የቀሩት ደግሞ የተባሉትን ሁሉ የሚፈጽሙ ሊበራሎች ወይም ደግሞ በተቃራኒው ያሉት አለም አቀፋውያን ሶሻሊስቶች ናቸው፡፡ ጎዳናዎችን በአፍሪካ ሃገራት መሰየምና ሉዓላዊነትን አሳልፎ መስጠት ይለያያሉ፡፡
ቀጥለን ለምእራባውያን ኢምፐርያሊዝም ቁልፍ የሆነውን የፍሪሜሶን ማህበር በአፍሪካ ያለውን ሚና ካመጣጡ እስከ ፖለቲከኞች ጋር ያለውን ትስስር በማየት የፓን-አፍሪካዊነት ዲስኩር ባዶነትን እንታዘብበታለን፡፡
ፍሪሜሶን እና አፍሪካውያን
ፍሪሜሶን“… በርግጠኝነት በመቶዎች ዓመታት በሚያከራክር ሁኔታ ደሞ በሺህ አመታት የሚቆጠር እድሜ ያለው የሚስጥር ማህበር ነው፡፡ ፍሪሜሶናዊነት እራሱን እንደ በጎ አድራጎት ድርጅት አድርጎ ያቀርባል፡፡ ይህ እውነት የሚመስለው ከሚመለምላቸው ሰዎች 97 መቶኛ የሚሆኑት “ሰመያዊ መዓርግ” ከሚባሉት ከመጀመርያዎቹ ሶስት መዓርጎች ስር የሚገኙት ገራገሮች ባላቸው ግብረገብና ከማህበረሰቡ የተሻሉ ግለሰቦች ቀናነት የሚታይ በመሆኑ እውነት ሊያስመስለው ይችላል፡፡ እውነቱ ግን ከፍ ያሉት መዓርጎች በፍሪሜሶን መክብብ ውስጥ ኮር (ማህል) ቦታውን የያዙ ጥቂቶች ለዓለም አቀፋዊ የበላይነት ግባቸው በመሳርያነት ነው የሚያውሉት፡፡” ማለት ይቻላል፡፡ ይበልጥ ለማግኘት
ፍሪሜሶኖች — FREEMASONS ማንበብ ይችላሉ፡፡
ፍሪሜሶን ማህበር ሚስጥራቱን ከመካከለኛው ምስራቅ
ገዳዮቹ ወይም ሀሻሺን ከሚባሉት ጋር ግንኙነት በፈጠሩት
ቴምፕላሮቹ አድርጎ በመጣው ባእድ ሚስጥር (ሰይጣን አምልኮ) ጋር የተቀላቀለ እምነት ማህበር እንደመሆኑ፣ የመካከለኛው ምስራቅ ቁንጮ ግብጽ ደግሞ ከአፍሪካ በቀዳሚነት መሰል የሚስጥር ማህበር በማንሳቀስ ትጠቀሳለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1004 ዓ.ም ዳር ኡል ሂክማት ወይም የእውቀት ቤት በስድስተኛው ከሊፋ ሀኪም ሲመሰረት ማለት ነው፡፡
[1] ቀጥሎ ደግሞ ሞሮኮን እናገኛለን፡ ሞሮኮ በሱፊ ሚስጥራት አማካኝነት እራሳቸውን ከፍሪሜሶኖች ጋር አንድ እንደሆኑ አድርገው ያያሉ፡፡ የአሜሪካ መስራች አባቶች አብዛኞቹ ፍሪሜሶን መሆናቸው ይታወቃል (አገር፣ መንግስት፣ ሃይማኖት የማይቀበለው አብዮተኛው ኢሉሚናቲ አካል ግን አይደሉም)፡፡ ጆርጅ ዋሽንግተን እንኳ ኢሉሚናቲን የሚያወግዝ ደብዳቤ ጽፏል፡፡
[2] እናም አሜሪካ ነጻነቷን ስታውጅ በቅድሚያ እውቅና የሰጠቻት እ.ኤ.አ. በ1777 ሞሮኮ ነበረች፡፡ ለመጀመርያው ፕሬዚደንቷም ጆርጅ ዋሽንግተንም የሞሮኮ ባንዲራ ተለግሶለታል፡፡ የሞሮኮ ባንዲራ በቀይ መደብ ላይ ባለ አምስት ጫፍ የተጠላለፈ አረንጓዴ ኮከብ ያለው ሲሆን ኮከቡን ሞሮኮዎች የሱሌይማን ማሕተም ይሉታል፡፡
[3] በሰሜን አፍሪካ ዘመናዊው ፍሪሜሶን የተስፋፋው ከፈረንሳይ አብዮትና ከናፖሊዮን ጦርነቶች ጋር ተያይዞ ነበር፡፡ ያንግ ተርክ የተባሉት የቱርክ አብዮተኞች ፍሪሜሶንን ወደ ሶርያና ግብጽ ወዳሉት ብሔራውያንና አብዮተኞች እንዲተዋወቁ አድርገዋል፡፡ በግብጽ ፍሪሜሶን የፈረንሳይ እና ብሪታንያ ሽኩቻ መሳርያ ሁኖ ነበር፡፡ መጀመርያ ወደ ግብጽ የመጡት እ.ኤ.አ. በ1798 በናፖሊዮን ሰራዊት ነበር፡፡ ኢሲስ ሎጅ የተባለውን ቅርጫፍ ሲመሰርት ናፖሊዮን ሙስሊም እምነትን እንደማይነካ በራሪ ወረቀት በትኖ ነበር፡፡ ኢሲስ ሎጅ 95 መዓርጎች ያሉት ስርዓት ይከተል ነበር፣ በእያንዳዱ መዓርግ እድገት አባሉ ቃለ መሃላ እየፈጸመ ይሸጋገራል፡፡
[4]
እ.ኤ.አ. በ1830 ደግሞ ጣልያን በአሌክሳንድርያ፣ ግብጽ የካርቦናሪ ሎጅ ከፍታ ነበር፡፡ ይሄኛውም ሎጅ እንደላይኛው በውዝግብ የተሞላ ሲሆን በተለይ ፖለቲካዊ ሁኖ በመገኘቱ መንግስት ይከታተለው ነበር፡፡ ሌላም ባለ95 መዓርግ (መምፊስ ራይት) ስርዓት የሚከተል ሜኔስ ሎጅ የተባለም ተመስርቶ ነበር፡፡
[5] ሌሎችም የመምፊስ ራይት የሚከተሉ ሳሙኤል ሆኒስ በተባለ ሰው የፈረንሳይ ሎጆች በአሌክሳንድሪያ፣ ኢስማኢልያ፣ በሰይድ ወደብ፣ ስዊዝ እና ካይሮ በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ1845 አል አሕራምን በአሌክሳድርያ መስርቷል፡፡ ይህ በግብጽ ገዢዎች እውቅናን ሊያገኝ የቻለ ሲሆን ብዙ የመንግስት ባለስልጣናትም አባል ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ከነዚህም ዝነኛው ኢሚር አብደል-ጋዛኢሪ፣ ፈረንሳዮችን አልጀርያ የተዋጋውና ሶርያ በግዞት እያለ ክርስትያኖች በዳማስከስ ጭፍጨፋ ሲደርስባቸው መቶዎችን በመሸሸግ ያዳነው ይገኝበታል፡፡ ሌላው የመምፊስ ራይት ተከታይ ዝነኛው ሰው ሳልቫቶሬ ዞላ ነው፣ እ.ኤ.አ. በ1849 በስኮቲሽ ራይት ስርአት የሚከተል የጣልያን ሎጅ በአሌክሳድርያ መስርቷል፡፡
[6] እ.ኤ.አ.በ1866 እውቅና አግኝተው የግብጽ የተለያዩ ሎጆች በአንድ ማህበር ሆኑ፣ ከፍተኛ መዓርጎቹ በግብጽ ግራንድ ኦርየንት እንዲሰጡና የመጀመርያዎቹ ሦስት መዓርጎች ደግሞ በግብጽ ናሽናል ግራንድ ሎጅ እንዲሰጡ ተደረገ፡፡
ከዲቭ ኢስማኤል የተሰኘው የግብጽ ንጉስ፣ በኢትዮጵያ በአፄ ዮሐንስ 4ኛ ዘመነ ንግስና መላ የናይል ተፋሰስንና የቀይ ባህርን ለመቆጣጠር በማሰብ ወረራ ፈጽሞ ክፉኛ የከሸፈበት ሲሆን በሃገሩ የሜሶኖች የበላይ ጠባቂ ነበር፣ ልጁ ተውፊቅም አባል እንዲሆን አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1881 ልጁና የመንበረ ሥልጣኑ ተኪ የሆነው ከዲቭ ተውፊቅ ፓሻ የመላ ግብጽ ሎጆች ግራንድ ማስተር ሊሆን ችሏል፡፡
[7]
በአፍሪካ የፍሜሶን ጅማሮን ታሪክ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም፤ እስክናሰፋው ድረስ ለግዜው ማግኘት የቻልነውን እንዳስሳለን፡፡ አውሮፓውያኑ ፍሪሜሶናዊነትን ወደ አፍሪካ ሲያመጡ መጀመርያ የከፈቷቸው ሎጆች በቅኝ ገዢ ፍሪሜሶኖች የተከፈቱ እንደመሆናቸው ለነጮች ሰፋሪዎች (ነጋዴዎች፣ ታጣቂዎችና ሰራተኞች) የሚሆኑ ብቻ ነበሩ፡፡ የፈረንሳዩ ግራንድ ኦርየንት የመጀመርያ ሎጁን በጥቁር አፍሪካ የመሰረተው እ.ኤ.አ. በ1781በሰይንት ሉ፣ ሴኔጋል ነበር፡፡
[8]ቀጥለውም ቅኝ አገዛዛቸው ስር ባስገቧቸው ሃገሮች ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ፣ ማዳካስካር፣ ጊኒ እና ኮንጎ ቅርንጫፎቻቸውን ከፍተዋል (ሞሮኮዎቹና ሙር ህዝቦች እየተባሉ የሚታወቁት ከላይ እንዳየነው ቀድሞኑ ከፍሪሜሶን ፍልስፍና ጋር በሱፊ ፍልስፍናቸው ምክንያት አንድ ነበሩ ማለት ይቻላል)፡፡
የዳች ኢስት ኢንዲያ ካምፓኒ አባል የሆኑ ቅኝ ግዛት አስፋፊዎችም በበኩላቸው በኔዘርላንድ ግራንድ ኢስት ስር ፈቃድ በመውሰድ በደቡብ አፍሪካ የመጀመርያውን የፍሪሜሶን ሎጅ፡ ሎጅ ጉድ ሆፕ (ሎጅ ቁ. 12) እ.ኤ.አ. በ1772 መስርተዋል፡፡
[9]
ፍሜሶኖቹ ለመበዝበዝና ለመጨፍጨፍ የመጡ ነበር፡፡ ታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ናይጄል ዎርደን እንደሚለው፡
እዚህ ኬፕ ጋር ሰፋሪዎች እንዲመጡላቸው አልፈለጉም፣ ያገራቸውን ሰዎችን ካሰፈሩ ወጪው ይጨምርባቸዋል፡፡ ስለዚህም ወደ ባርያ ጉልበት ፊታቸውን አዞሩ፡፡ ዳች ኢስት ኢንድያ ካምፓኒ (ቪኦሲ) ወደ ኬፕ ታውን ከ1658ጀምሮ 63,000 ባሮችን አምጥቷል፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ፣ ከህንድ፣ ከኢንዶነዢያ የመጡ ነበር፡፡ ባርነቱ እስከ 1838 ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ በዛን ዘመን ዜጎች ባርያ ይገዙ ነበር፣ ኬፕ ታውን የባርያ ማህበረሰብ ሆነች፡፡
[10]
በቅኝ አገዛዝ ዘመን ፍሪሜሶኖች ነጻ አውጪ ሁነው ቢታዩም እንኳ ቅኝ ገዢዎቹም ፍሜሶኖች ነበሩ፡፡ የቦር ጦርነት (1899-1902) እየተባሉ የሚታወቁት፣ የብሪቲሽ ግዛትን የሚያስፋፉ ጦርነቶችን በዋናነት ሲያንቀሳቅሱ የነበሩት ፍሜሶኖቹ፡ ሴሲሊ ሮድስና የክቡ ጠረጴዛ ቡድን አጋሮች ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ አብዛኛውን የደቡብ አፍሪካ የወርቅ እና የአልማዝ መአድን የሚገኝበትን ቦታ ለመቆጣጠር ችለዋል፡፡
[11]በብሪታንያ ቅኝ ገዢነትና ኢምፐርያሊዝም አጥብቆ የሚያምነውና ይህን እንዲፈጽም የሚስጥር ማህበር መስርቶ ሃብቱን ለማህበሩ የተናዘዘው ሴሲሊ ሮድስ በአፖሎ ዩኒቨርሲቲ ሎጅ ነበር ፍሪሜሶን የሆነው፡፡ ዓለምን ሁሉ በብሪታንያ ስር ለማድረግ ባለው ሃሳብ ፍሪሜሶን ላይ ባየው እንከን ነበር የራሱን የሚስጥር ማህበር የመሰረተው፡፡
[12]
በምእራብ አፍሪካ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1791 ቡላን ሎጅ በፖርቺጊስ ጊኒ፤ በ1810 ቶሪድዞንያን ሎጅ በኬፕ ካስል፣ ኬፕ ኮስት፤ በ1820ሎጅ ኦፍ ጉድ ኢንተንት በፍሪታውን፣ ሴራልዮን፤ በ1833 ሰይንት ጆንስ ሎጅ በጎልድ ኮስት (የዛሬይቱ ጋና) ተመስርተው የነበሩ ሲሆን አሁን የሉም፡፡
[13]በ1859 ጎልድ ኮስት ሎጅ በጎልድ ኮስት (የዛሬይቱ ጋና)፤ በ1867 ሌጎስ ሎጅ በናይጄርያ ተመስርተዋል፡፡ በ1913 የሰሜንና ደቡብ ናይጄርያ ዲስትሪክት ግራንድ ሎጅ የተመሰረተ ሲሆን የሰሜኑና ደቡቡ መዋሃድ ተከትሎ በ1916 ስሙ የናይጄርያ ዲስትክት ግራንድ ሎጅ ተባለ፡፡ አይሪሾቹ ደግሞ በ1897 የማክዶናልድ ሎጅ ካላባር መስርተዋል፡፡ ስኮቲሾቹ ደግሞ በ1915 ሎጅ አካዳሚክ ቁ.1150ን ለመጀመርያ ግዜ መስረተዋል፡፡ በዚህ መልኩ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገሮች ቅርንጫፎቻቸውን ከፍተዋል፣ በኢትዮጵያ በይፋ የሚታወቅ ቅርጫፍ የላቸውም፡፡
ዛሬ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሎጆች በመላው አፍሪካ ይገኛሉ፡፡ ሚስጥራዊ እንደመሆናቸው ታሪካቸውን በተሟላ መልኩ አጥርቶ መዘገብ ይከብዳል፡፡ ከላይ ያለው በቂ ባይሆንም አጠቃላይ ምስሉን ያሳያል፡፡ ቀጥለን ከስር ዛሬ አፍሪካን እየመሩ ያሉ ፍሪሜሶን ፕሬዚደንቶችን እንተዋወቃለን፡፡
ፍሪሜሶንን ያገዱ የአፍሪካ መሪዎች
የአፍሪካ ሕብረተሰብ ሃይማኖታዊ በመሆኑና ፍሪሜሶኖች አውቆም ሆነ ተታሎ ቢክዱትም የመጨረሻ ሚስጥሩ ሰይጣን አምልኮ በመሆኑ ፍሪሜሶን መሆን ዛሬ ላይ አወዛጋቢ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1963 የኮትዲቯሩ መሪ ፌሊክስ ሁፌት ቦኒ እያሴሩብኝ ነው በማለት ሶሻል ዲሞክራት የነበሩት ተቃዋሚዎቹን ብዛት ያላቸው ከፈረንሳይ ግራንድ ኦርየንት ጋር የተገናኙ ፍሪሜሶን የሆኑትን ሲያሳድድ ነበር፡፡ ፍሪሜሶንም ታግዶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በ1970 “ሁሉ ነገር ፈጠራ ነው” ብሎ እራሱ በማስተባበሉ እግዱን አንስቶ ለሜሶኖቹ ስልጣን ሁሉ ሰጣቸው፡፡
በዛየር ሞቡቱ እ.ኤ.አ. በ1965 ስልጣን ሲይዝ ፍሪሜሶንን ያገደ ሲሆን፣ ተመልሶ በ1972 አንስቶታል፡፡ በማዳጋስካር ፕሬዚደንት ዲዴር ራትሲራካ በመጀመርያ ስልጣን ዘመኑ (1975-93) ፍሪሜሶን ታግዶ የነበረ ሲሆን በ90ዎቹ ተመልሶ መጥቷል በ96 የማዳጋስካር ግራንድ ናሽናል ሎጅ ተመስርቷል፤ በዲዴር ሁለተኛው ስልጣን ዘመኑ (1997-2002) የሚስጥር ማህበሩ አልተነካም፡፡ በጊኒ በሴኮ ቱሬ፣ በማሊ በሞዲቦ ኪየታ፣ በቤኒን በማቲዩ ኬሬኮ ፍሪሜሶነሪ ታግዶ ነበር፡፡ በ1980ዎቹ በቤኒን መልሶ ተከፍቷል፡፡ በማሊና ጊኒ መች መልሶ እንደተከፈተ ለግዜው ባላገኘውም ዛሬ ላይ ግን ይንቀሳቀሳሉ፡፡
በላይቤርያ ሳሙኤል ዶ እ.ኤ.አ. በ1980 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ሲይዝ ፍሪሜሶኖችን ክፉኛ አሳድዶ ነበር፡፡ ለዘመናት የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ቢሮ አፍሮ-አሜሪካውያን በሆኑ የሚያዝ የነበረ ሲሆን፣ እኚህም ከጥቁር አሜሪካውያን ግራንድ ኦርደር፣ ፕሪንስ ሃል ቻፕተር እየተባለ የሚታወቀው ፍሪሜሶን ማህበር ጋር የተገናኙ ነበሩ፡፡
በናይጄርያ ደግሞ ፍሪሜሶኖች የኢኮኖሚው አሽከርካሪ የነበሩ ሲሆኑ በ1970ዎቹ መጨረሻ የያኩቡ ጎዎን ወታደራዊ መንግስት የሚስጥር ማህበሩን የሚያግድ አዋጅ አውጥቶ ነበር፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት ስራቸውን አልያም የሚስጥር ማህበሩን እንዲመርጡ ተገደው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ዛሬ ላይ ተመልሰው ይንቀሳቀሳሉ፡፡
አሁን አሁን በሙስሊም ሃገሮች ፍሪሜሶን የተወገዘ ቢሆንም ይንቀሳቀሳል፡፡ በእስልምና ሰፊ ዝና ያላቸውና የሙስሊም ወንድማማችነት መስራቹን ሃሰን አልበናን የቀረጹት ሰዎች ጀማል አልዲና አልአፍጋኒ እና መሃመድ አብዶ ፍሪሜሶኖች ነበሩ፡፡ ፍሪሜሶኖቹ ሳላፊያ የሚባል እንቅስቃሴ መስራቾች ናቸው፡፡ ሌላ ሃሰን አልበናን የቀረጸው የሳላፊያ ህትመት
“ዘ ላይት ሃውስ” አዘጋጅ የነበረው ራሺድ ሪዳ ፍሪሜሶን ነበር፡፡ እራሱም አልበና የማህበሩ አባል ሁኗል፡፡ የአልበናን ንድፈ ሃሳብ በማስተጋባት የሙስሊም ወንድማማችነት ቀንደኛ የንድፈ-ሃሳብ ሰው ሁኖ የተካው ሰዒድ ኩትብ እንኳ የሙስሊም ወንድማማችነት አባል ያልነበረና ሆኖም ግን ፍሪሜሶን የሆነ ሰው ነበር፡፡
[14]
ወደዋናው ታሪካችን ስንመለስ ደግሞ ለምሳሌ በቅርቡ (እ.ኤ.አ. በ2000) የፈረንሳይ ግራንድ ናሽናል ሎጅ ቅርንጫፎቹን በጅቡቲ ከፍቷል፡፡ አባሎች ቁርአን ላይ ሚስጥር እንደማያወጡ ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ፡፡ ሴኔጋልም ቢሆን የኃይል ሚዛኑን የተቆጣጠሩት አብዛኞቹ ፍሪሜሶን ናቸው፡፡
ለአፍሪካውያን የፍሪሜሶን አባል መሆን ከገዢዎቹ ነጮቹ ጋር እኩል ስለሚያደርጋቸው እና በባህላዊ እምነት ያሉት ወይም ደግሞ ሱፊዎቹ የሚስማማ ሁኖ ስለሚያገኙት አባል መሆን ያኮራቸዋል፡፡
ስለዚህም በዚህ አወዛጋቢነቱ ምክንያት በግልጽ የፍሪሜሶን አባል መሆናቸውን ያሳወቁ የአፍሪካ መሪዎች ጥቂት ናቸው፡፡ እናም የሆኑትን ሁሉንም ማወቅ ባንችልም ጥቂቶቹን ማየት ይቻላል፡፡
ፍሪሜሶን የአፍሪካ መሪዎች
የሮማንያ የሜሶኖች ህትመትን እንደዘገበው ከሆነ በ16ኛው የአፍሪካ ሕብረት (እ.ኤ.አ. ጥር 24-32፣ 2011 ዓ.ም) በተካሄደው ጉባኤ የአፍሪካ ፍሪሜሶን ግራንድ ማስተሮች ስብሰባ አደረጉ ብሎ ዘግቦ ነበር፡፡
[15]ግራንድ ማስተሮቹ የየሃገራቸው መሪዎች የነበሩ ናቸው፡፡ ከተሳተፉት ውስጥ አሊ ቦንጎ (ጋቦን)፣ አብዱላዬ ዋዴ (ሴኔጋል)፣ ዴኒስ ሳሶ ንጌሶ (ኮንጎ-ብራዛቪል) ይገኙበታል፣ በስብሰባቸው የፈረንሳዩ መሪ ኒኮላስ ሳርኮዚ ተገኝቶ ነበር፡፡ ከስር በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡
የቀድሞ የኮንጎ ሪፐብሊክ የአሁኗ ኮንኮ-ብራዛቪል የቀድሞ መሪ ፓስካል ሊሱባ እና በሃይል ከስልጣን ያስወገደው ዴኒስ ሳሶ ንጌሶ ፍሜሶኖች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የተለያየ ማህበራት ናቸው፡፡ ሊሱባ የፈረንሳይ ግራንድ ኦርየንት አባል ሲሆን፣ ሳሶ ንጌሶ ደግሞ ከፈረንሳይ ግራንድ ናሽናል ሎጅ ጋር የተገናኘ የሴኔጋል ሎጅ አባል ነው፡፡ ታጣቂዎች በዋና ከተማዋ ከተጋጩ በኋላ የአፍሪካና የፈረንሳይ ፍሪሜሶኖች፡ የፈረንሳይ ግራንድ ሎጅ፣ የአይቮሪኮስት ዩናይትድ ግራንድ ሎጅ እና ግራንድ ኦርየንት እና የካሜሮን ዩናይትድ ሎጅስ በጋራ ሰላም ለማውረድ ሙከራ አድርገው ነበር፣ ባይሳካላቸውም፡፡
[16]
እ.ኤ.አ.በ2009 ያረፈው የጋቦኑ መሪ ኦማር ቦንጎም ፍሪሜሶን ነው፡፡ ፕሬዚደንት ሁኖ የተካው ልጁም አሊ ቦንጎም ፍሪሜሶን ነው፡፡ የፈረንሳይ ናሽናል ግራንድ ሎጅ፣ ግራንድ ማስተር የሆነው ወደጋቦን መጥቶ ነበር አባቱ ይዞት የነበረውን ቦታ ያስረከበው፡፡ አሊ ቦንጎ በዛኑ አመት በሊበርቪሌ የዓለም የሬጉላር ፍሪሜሶነሪ ጉባኤ እንዲካሄድ አድርጓል፣ ጉባኤው እንዲካሄድ አባቱ በሕይወት እያለ ያስጀመረው ጉዳይ ነበር፡፡ በጉባኤው የቀድሞ የፈረንሳይ ግራንድ ኦርየንት ግራንድ ማስተር እና ከ2000-2003 የፈረንሳይ ፕሬዚደንት የሽብርና ወንጀል ልዩ አማካሪ የነበረው አልየን ባዉር ተገኝቶ ነበር፣ ከቀብሩ በኋላ አሊ ቦንጎን ሹሞታል፡፡
ፍራንኮይ ስቴፋኒ የፈረንሳይ ናሽናል ግራንድ ሎጅ ግራንድ ማስተር የሆነው ደግሞ አሊ ቦንጎን የጋቦን ግራንድ ሎጅ ግራንድ ማስተር አድርጎ ሹሞታል፡፡ ይህም አሊ ቦንጎን የሁለቱም፡ የጋቦን ግራንድ ሎጅ እና የግራንድ ኢኳቶርያል ራይት ግራንድ ማስተር እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ አባቱ ኦማር ቦንጎ የሜሶኖቹን ሎች የፖለቲካ ደጋፊዎቹ መመልመያ አድርጎ ይጠቀምበት ነበር፡፡ ኦማር ቦንጎ ፕሬዚደንት ከመሆኑ አስራ አራት አመት በፊት እ.ኤ.አ. በ1953ነበር አባል የሆነው፣ በጋቦን ሁለት የተለያዩ ሎጆችን እንዲመሰረቱ አድርጓል፡፡ አንዱ ግራንድ ራይት ኢኳተርያል – ግራ ዘመም ከሆነው ግራንድ ኦርየንት ጋር የተያያዘውና፤ ሁለተኛው ደግሞ የጋቦን ግራንድ ሎጅ – ቀኝ ዘመም ከሆነው ከፈረንሳይ ናሽናል ግራንድ ሎጅ ጋር የተያያዘው ነው፡፡ የቦንጎን አመኔታ ለማግኘት ፖለቲከኛው ከነዚህ ከሁለቱ የአንዱ መሆን ይገባዋል፡፡ የጋቦን ገዢዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ የነዚህ ሎጅ አባል ናቸው፡፡
[17]ሄግሊያዊ ዲያለክቲክ ማለት እንዲህ ነው፣ ሁለቱንም ጽንፎች ከተቆጣጠርክ የውጤቱ ባለቤት ትሆናለህ፡፡
እ.ኤ.አ.ከ2003-2013 የማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መሪ የነበረው፣ ከ1991 ጀምሮ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሲያደርግ፣ ካገር ሲባረርና አስተዳደር ሲቀየር ሲመላለስ ከቆየ በኋላ ከውጭ አምጥቶ ስልጣን የሰጠውን ፓታሴን ገልብጦ ስልጣን በኃይል እ.ኤ.አ. በ2003 የተቆጣጠረው ፍራንኮይስ ቦዚዜም ፍሜሶን ነው፡፡ በ2013 የዓማጽን ሰራዊት ከሃገር አባሮታል፡፡ የአካባቢው የምእራባውያን ተላላኪ ሃገሮች ቦዚዜን ለማትረፍ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም፡፡ አማጽያኑን ወክሎ የሽግግር መሪ የሆነው አዲሱ የማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መሪ ከውጭ አገሮች ጋር ያሉትን ውሎች እየፈተሸን ነው ብሏል፡፡
ኢድሪስ ዴቢ የቻድ መሪውም ፍሪሜሶን ነው፡፡ ከነዳጅ ተፈጥሮ ሃብቷ የሚገባትን ያህል ያልተጠቀመች ሃገር ስትሆን የዓለም ባንክ በቻድና ካሜሮን የሚያልፍ የነዳጅ ትቦ ሊያዘረጋ ፈንድ ከለቀቀላት በኋላ ፈንዱን ድሆች ልመግብበት ነው ብሎ ካዘዋወረ በኋላ 30 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚሆነውን መሳርያ ለመግዛት ተጠቅሞበታል፡፡
[18]
ጁኔ አፍሪኩዌ የተባለ የፈረንሳይ ህትመት ደግሞ ረዘም ያለ ዝርዝር ያወጣ ሲሆን ከነዚህ መሃከል የአይቮሪኮስት መሪ የነበረው ሎረን ባግቦ ደንብ የማያከብር ፍሪሜሶን (ሽርጥ የሌለው ፍሪሜሶን) ሲለው ከፈረንሳይ ጋር ተባብሮ የባግቦን መንግስት የገለበጠው አላሳን ኦታራም ፍሪሜሶን ነው ይለዋል (የሁለቱን ዝርዝር ከስር እንመለስበታለን)፡፡
[19]ህትመቱ በተጨማሪም በጥር 2011 የባግቦ ባለቤት ሲሞን ባግቦ ፍሪሜሶኖች ላይ ጦርነት በማወጅ ከኮትዲቯር ተጠራርገው እንዲወጡ ጥሪ አቅርባ ነበር፡፡
[20]
በተጨማሪን ከዝርዝሩ የጋቦኑ ኦማር ባንጎ በፊት መሪ የነበረው ምባ፣ የቀድሞ የቶጎ መሪ ናሲንግቤ ኢያዴማ፣ አባቱ ሲሞት መንበረ ስልጣኑን በመረከብ አሁን የቶጎ መሪ የሆነው የኢያዴማ ልጅ ፋኡር ናሲንግቤ፣ ባንከር ነበረውና አሁን የቤኒን መሪ የሆነው ቶማስ ያዪ ቦኒ፣ በአባቱ ቦታ የተተካው የኮንጎው መሪ ጆሴፍ ካቢላ፣ የሴኔጋሉ አብዱላዬ ዋዴ፣ የጊኒው ፕሬዚደንት አልፋ ኮንዴ፣ በመፈንቅለ መንግስት የተወገደው የማሊው መሪ አማዱ ቱማኒ ቱሬ ፍሪሜሶን መሪዎች ብሎ ይዘረዝራቸዋል፡፡
[21]
የቡርኪነፋሶው መሪ ብሌዝ ኮምፓኦሬ ደግሞ ግራንድ ማስተር የነበረ ሲሆን፣ አሁን የቡርኪነፋሶ ሎጅ ግራንድ ማስተር የደህንነት ሚኒስትሩ ጂብሪል ባሶሌ ነው፡፡ የጋቦን ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆነው የማስተሩ አሊ ቦንጎ “ወንድም” ፍሪሜሶን ነው፡፡
[22]
ሌሎችም የቀድሞ የጋና ፕሬዚደንት (2001-2009) የነበረው ጆን ኩፎር፤ አሁን በአፍሪካ ህብረት የሶማልያ ልኡክ የሆነውና ከኩፎር በፊት ለረዥም ግዜ በሁለት የተለያዩ ግዝያት የጋና መሪ የነበረው ጄሪ ጄ. ረውሊንግ፤ የካሜሮኑ ፕሬዚደንት ፖል ቢያ፤ የቡርኪነፋሶው ፕሬዚደንት ብሌዝ ኮምፓኦሬ፤ የኒጀሩ የቀድሞ ፕሬዚደንት ማማዱ ታንጃ፤ የአይቮሪኮስት የቀድሞ መሪ ሮበርት ጉኤ የተረጋገጡ ፍሪሜሶን መሪዎች ናቸው፡፡
[23]
የሴኔጋሉ የቀድሞ መሪ የነበረው አብዱላዬ ዋዴም
“ፍሪሜሶን ፎር ዳሚስ”የሚባል ለጀማሪዎች የተሰራ የፍሪሜሶን ፕሮፖጋንዳ መጽሐፍ ሲያነብ ታይቶ ውዝግብ ከተነሳ በኋላ ቀድሞ የዶክትሬት ዲግሪውን ከሰራ በኋላ ስለሜሶኖች ከጓደኛው ደጋግሞ ሲሰማ ለማወቅ ሲል አባል ሁኖ እንደነበርና የጠበቀውን እውቀት ማግኘት ስላልቻለ ተመልሶ እንደወጣ ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግሯል፡፡
[24]
የታንዛንያው መሪ የነበረው ቤንጃሚን ምካፓ ደግሞ በአንድ ወቅት በዳሬሰላም ፍሪሜሶኖች መቶኛ ምስረታ በአላቸውን በሚያከብሩበት ወቅት የክብር እንግዳ አድርገው ጠርተውት ነበር፡፡ የእንግሊዝ ፍሪሜሶነሪ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ለመጀመርያ ግዜ ሲመጣ ዛንዚባር ነበር ቅርንጫፉን እ.ኤ.አ. በ1904 የከፈተው፡፡
[25]
እራሱን የእኩልነት፣ ወንድማማችነትና ነጻነት ፋና አድርጎ የሚወስድ ማህበር እዚህ ከጠቀስናቸው አብዛኞቹ በብልሹነታቸው ከሚታወቁ መሪዎች ጋር መግጠሙ የሚደንቅ አይደለም፣ በፈረንሳይ የመጀመርያው አብዮት፣ አብዮተኛ ፍሪሜሶኖች ምን እንደሰሩ ታሪክ መዝግቦታል፡፡
[26]
የፍሪሜሶኖች ክህደት፡ የአይቮሪኮስት ልምድ
ከላይ ፍሪሜሶኖች በአፍሪካ ቅኝ አገዛዝ እና ባርያ ንግድ ላይ ተሰማርተው እንደነበሩ አስተውለናል፣ አሁን ደግሞ በዘመናዊ የአፍሪካ ፖለቲካ የአይቮሪኮስት ልምድን በመውሰድ የፈጸሙትን በደል እንመለከታለን፡፡ በ2011 በአይቮሪኮስት ምርጫውን ተከትሎ በተነሳ ውዝግብ “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ” ወድያውኑ ለውረን ባግቦን በማውገዝ ማእቀብ ጥለውበታል፡፡ የሃገሬው ሁኔታ ውስብስብ መሆንና የውጤቱ መቀራረብ ታይቶ ለውሳኔ መቸኮል አይገባም ነበር፣ ሁኔታውን ያወገዘው ብቸኛው መሪ የዩጋንዳው ሙሴቪኒ ነበር፡፡ ያለ አፍሪካ ህብረት እውቅና በምን ስሌት ማን ፈቅዶላቸው ፈረንሳውያኑ ኮትዲቫር ሊገቡ እንደቻሉ ይጠይቃል፡፡
[27]
ሰብአዊነትን ባፋቸው ቢያነሱም፣ ፍሪሜሶናዊነት ለምእራባውያን ኢምፐርያሊዝም፣ እና አዲስ የዓለም ስርዓት ማስፈፀምያ ቁልፍ ነው፡፡
የፈረንሳይ ፍሪሜሶኖች ደግሞ በአይቮሪኮስት ጣልቃ በመግባት ጥቅማቸውን በማስጠበቅ ያሹትን ፈጽመዋል፡፡ ባግቦን ያወገዙት አጎራባች የአፍሪካ መሪዎችና የፈረንሳይ ፖለቲከኞችና ከበርቴዎች ሁሉ የአንድ ሎጅ አባሎች ናቸው፡፡ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች ይተዳደሩ የነበረው በፍሪሜሶኖች ሰፊ ተሳትፎ ነበር፡፡
በአይቮሪኮስት የተደረገው ዘመቻ የዣክ ሺራክ ነበር፡፡
[28]የፈረንሳይ “ሰላም አስከባሪ” ወታደሮች የአይቮሪኮስት አየር ሃይልን እንዲያጠቁ ያዘዘው፣ ሆቴል ዲ አይቮሬን እና የፕሬዚደንት ባግቦን መኖርያ እንዲከቡ ከመቶ በላይ ታንኮች የላከው፣ ምንም ያልታጠቁና ስጋት ያልሆኑ ወጣቶች የፈረንሳይ ወታደሮች ባግቦን እንዳይገድሉ ወይም እንዳይገለብጡ ለመከላከል የተሰለፉት ላይ ተኩስ እንዲከፈትባቸው ያዘዘው ሺራክ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ያፈጠጠ ጣልቃ ገብነት በሃገራችን የማይታሰብ ነው ልትሉ ትችላላቹ፣ ሆኖም ግን የአሜሪካው አፍሪኮም እና ሰው አልባ ተዋጊ አየሮች በአፍሪካ መስፋፋት ይህ እውን ከመሆኑ የሚያግተው እንደሌለ ያሳያል፡፡
የፈረንሳይ ቅጥረኞች/ወኪሎች የሚፈልጓቸውን ከመፈንቅለ መንግስት መታደግ የማይፈልጓቸውን ለመፈንቀል አያመነቱም፡፡ የምርጫውን ውዝግብ ክፍተት ከማግኘታቸው በፊት ባግቦን ለመፈንቀል ያደረጉት ሙከራ በደንብ የተመዘገበ ነው፡፡ የፈረንሳዮች እንቅስቃሴን ያጋለጠ የተለያዩ ስብሰባዎች መዝገብ የያዘ የፈረንሳይ ላፕቶፕ ሊያዝ ችሎ ነበር፡፡
[29]ቡርኪነፋሶ ላይ በተደረገ ስብሰባ መፈንቅለ መንግስት የሚያደርጉበት ዘዴ በደህንነት ዘገባ ላይ ሰፍሮ ነበር፣ እ.ኤ.አ. በሕዳር2006 ላይ በአቢጃን መፈንቅል እንደሚያስነሱ የወሰኑበት ነበር፡፡ ይህ ባግቦን ከምርጫው በኋላ ጣልቃ ገብተው ካስወገዱት ከአምስት ዓመት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ባግቦን የጠሉት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ሲወጡ የተደረጉ አሳሪ ውሎችን ለማስወገድ እየታገለ ስለነበር ነው- ከስር እናየዋለን፡፡ የደህንነት ዘገባው፡
“አላሳን ኦታራ [አሁን ባግቦን የተካው] ስብሰባውን በመክፈት ፖቼትን አስተዋወቀ፡፡ [ፖቼትም]ቀጥታ ከሺራክ መልእክት ይዞ እንደመጣና መልእክቱም “ኤዲኦ (ኦታራ) ልጃችሁና ወንድማችሁ ከ2005 ምርጫ በፊት የአይቮሪኮስት ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ይሆናል፡፡” ሺራክ “ሳንስማማበት በአይቮሪኮስት ትጥቅ መፍታት አይኖርም፡፡ ትጥቅ ከመፍታት በፊት የACCRA III ስምምነት ላይ ድምጸ ውሳኔ መሰጠቱ ወሳኝ ነው፡፡
“መላ ፈረንሳይና ዣክ ሺራክ ኤዲኦ በአምስት ወር ውስጥ ማለትም በሕዳር ስልጣን እንዲይዝ ይደግፉታል፡፡ አሁን ማሊ እና ቡርኪነፋሶ ውስጥ እየሰለጠኑ ያሉ ቅጥረኛ ሰራዊቶች (መርሲነሪስ) መልምለን ጨርሰናል፡፡ … ዓላማችን ኤዲኦን ስልጣን ላይ ማውጣት ነው፡፡ … ነሐሴ ተመልሼ ከፕሬዚደንት ኮምፓኦሬ ጋር እመጣለው፣ ከመርሲነሪዎቹ ጋር አስተዋውቃችኋለው፡፡ ኦታራ ስልጣን ለመያዝ በሕዳር ይመለሳል፡፡”
ቀጣዩ ተናጋሪ ብሌዝ ኮምፓኦሬ ነበር፣ የቡርኪነፋሶ ፕሬዚደንት፣ ፖቼትንና ሺራክን በማመስገን ጀመረ፡፡ የአይቮሪኮስት መንግስት የኦታራ መብትን በመጋፋቱ ከወቀሰ በኋላ የሚከተለውን አለ፡
“በዚህ ነገር እኮ የእኔው ስም ነው እየተበላሸ ያለው፡፡ በቡርኪና የእኔ መኮንኖች መርሲነሮቹን ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሩ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ እደግፋችኋለው፡፡ ከእዛው ሁነን ለእናንተ ነገሮች ቦታቸውን ለማስያዝ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ አትፍሩ፤ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ውጊያውን እናሸንፋለን፡፡ በአምስት ወር ውስጥ ሁሉ ነገር ዝግጁ ይሆናል፡፡”
የአምስት ወሩ እቅድ ሳይሳካ ቀርቶ በቀጣቹ አምስት አመታት የባግቦን መንግስት ለመገልበጥ የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገው ነበር፡፡ አብዛኞቹ ቀድሞ ተደርሶባቸው ተጨናግፈዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ሙከራዎች ዋና ተሳታፊዎቹ የፈረንሳይ መልእክተኞች፣ የፈረንሳይ (የተባበሩት መንግስታት)ሰላም አስከባሪዎች እና በዙርያው ያሉ ከላይ ያየናቸው ከፈረንሳይ ፖለቲከኞችና ቁንጮዎች ጋር የፍሪሜሶን ትስስር ያላቸው የአፍሪካ ፕሬዚደንቶች ናቸው፡፡ አስተግባሪ አካላት ደግሞ አቢጃን መቀመጫቸውን ያደረጉ ድምበር ዘለል የፈረንሳይ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ የፈረንሳይ ወኪሎች/ኤጀንቶች ናቸው፡፡
ይህ የታወቀ የፈረንሳይ አዲስ ቅኝ አገዛዝ (ኒዮ-ኮሎኒያል) ባሕርያት መገለጫ ነው፡፡ የፈረንሳይ ባለሃብቶችንና ፖለቲከኞችን በፈረንሳይ ስም የሚጠቀሙበት ዘዴያቸው ነው፡፡ በአይቮሪኮስት ልዩ የሚያደርገው “ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብም” ከጎናቸው እንዲቆም ማሳመን መቻላቸው ብቻ ነው፡፡
እ.ኤ.አ.በ1960 የአፍሪካ ቅኝ ግዛቶቿን ነፃ ማውጣት ግዴታ ሲሆንባት ፈረንሳይ አሳሪ ውል እያስፈረመች “ለቀቀቻቸው”፡፡ ባስፈረመቻቸው“ፓክት ኮሎኒያል” መሰረት የውጭ ምንዛሪ ክምችታቸው (85 መቶኛ) በፈረንሳይ እንዲቀመጥ ማስገደድ፣ ቁልፍ የሐገሪቱን ጥሬ ሃብት ቁጥጥሩ በፈረንሳይ እንዲሆን፣ በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችሉ ሰራዊቶቿን በሐገሪቱ የማስፈር መብት፣ የጦር መሳርያቸውን በሙሉ ከፈረንሳይ የመግዛት ግዴታ፣ የፖሊስና ሰራዊት የበላይ አሰልጣኝ መሆኗ፣ የፈረንሳይ ቢዝነሶች በቁልፍ ዘርፎች (ውሃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ወደብ፣ ትራንስፖርት፣ ኃይል ወዘተ …) ላይ ሞኖፖሊያቸው እንዲጠበቅ የሚያስገድድ ውል ነበር ያስፈረመቻቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ፈረንሳይ ሃገራቱ ከፍራንክ ቀጠና ውጪ ማስገባት የሚችሉት ኢምፖርት ላይ ብቻ ሳይሆን ገደብ ያደረገችው፣ ከፈረንሳይ ኢምፖርት ማድረግ ያላቸውንም ዝቅተኛ ድርሻ ነግራቸዋለች፡፡ እኚህ ስምምነቶች አሁንም ድረስ ያልተቋረጡና ተፈጻሚነት ያላቸው ናቸው፡፡
[30]ይህን ታቅፈው ነው ፓን-አፍሪካኒዝም የሚደሰኩሩት፡፡
የዚህ አሳፋሪ ውል ቀራጭ የካሜሮኑ ነጻነት ታጋይ ሙሜ በመርዝ እንዲገደል ውሳኔ ያስተላለፈው ጃኩዌ ፎካርት ነበር፣ በወቅቱ የፈረንሳይ የአፍሪካ ፖሊሲ የፕሬዚደንቱ አማካሪ እና የፈረንሳይ ደህንነት ቢሮ በአፍሪካ የሚስጥር እንቅስቃሴ ሰው ከነበረው ከቻርለስ ፓስኳ ጋር በመሆን እ.ኤ.አ. በ1959 የመሰረተው ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው በፕሬዚደንቱ ቢሮ የአፍሪካ የሚስጥር ቡድን እና የአፍሪካና ፈረንሳይ ፍሪሜሶኖች ማገናኛ ሰው ነው፡፡
[31]
በዚህ መልኩ በ1960 አዲስ ነፃ የሚወጡት ሃገሮች የሚረባ ነገር ሳያገኙ ባንዲራ፣ መዝሙር እና በተ.መ.ድ. መቀመጫ ተሰጥቷቸው አዲስ ሃገር ሁነዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር ፎካርት ቁልፍ ሚና የተጫወተው፣ ከላይ እንዳየነው በፋይናንስና ኢኮኖሚ፣ በባህልና ትምህርት እና በብሔራዊ ሰራዊት ዘርፎች አስገዳጅ ውል በመቅረጽ፡፡
በመጀመርያ አስራአንድ ሃገሮች፤ ሞሪታንያ፣ ሴኔጋል፣ አይቮሪኮስት፣ ዳሆሜ (አሁን ቤኒን)፣ ላይኛው ቮልታ (አሁን ቡርኪነፋሶ)፣ ኒጀር፣ ቻድ፣ ጋቦን፣ ማእከላዊ አፍሪካዊ ሪፐብሊክ፣ ኮንጎ ብራዛቪል እና ማዳጋስካር ናቸው፡፡ ቀድሞ በተ.መ.ድ. ባላደራነት ስር የነበሩት ቶጎና ካሜሮን ወደቡድኑ እንዲገቡ ተጠልፈዋል፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ ማሊና የቤልጂየም የነበሩት ሩዋንዳና ቡሩንዲ እና ኮንጎ ኪንሻሳም ተጨመሩበት፡፡ የፖርቱጋል የነበሩት ድንበሮችና ኮሞሮስ እና ለረዥም ግዜ በፈረንሳይ ስር የነበረችው ጅቡቲም በዚሁ ውል ታስረዋል፡፡ እኚህ ሁሉ እስረኞች እ.ኤ.አ. በ1961 አዲስ በተቋቋመው የትብብር ሚኒስትሪ ስር ተደረጉ፡፡ እኚህን ሁሉ ሃገራት በሚፈራረሙት ውል የፈረንሳይ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ እቅፍ ውስጥ እንዲታፈኑ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ ውል ምክንያት ፈረንሳይ በቀኝ ግዛቶቿ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ ሕጋዊ የበላይነት እንዲኖራት አድርጓል፡፡
[32]
ባግቦ ከነዚህ ማሰርያዎች ለመላቀቅ ያደረገው ሙከራ ፈረንሳይን እጅግ ማበሳጨቱ በአካባቢው ያሉ አገሮችን አላስደነቀም፡፡ ያካባቢው ፕሬዚደንቶች ስልጣናቸው ላይ እንዲቆዩ ያደረጋቸው የፈረንሳይ ሰራዊት ነው፡፡ ኢኮኖሚያቸው ደግሞ ሞኖፖል እንዲይዙ የተደረጉ የፈረንሳይ ቢዝነሶች ቁጥጥር ስር ነው፡፡ ፕሬዚደንቶቹ ለዚህ ሲሉ 85 መቶኛ ሃገራዊ ሃብታቸውን እንዲይዝ ለፈረንሳይ ግምጃ ቤት ይሰጣሉ፣ በተጨማሪም ወንበራቸውን እንዳያጡ ለፈረንሳይ ፖለቲከኞች ወፍራም መደለያ ይከፍላሉ፡፡
የአይቮሪኮስት መሪ የነበረው ባግቦ የብሪታንያ እና ካናዳ ልኡካንን በማባረር ቀርቦለት ነበረውን መደለያ (ጥገኝነትና ከክስ ነጻ መሆን) አልቀበልም በማለት ዓለም አቀፋውያኑን ንቀት አሳይቶ በመጋፈጡ አገር ውስጥ የነበሩ 9,500 ጠንካራ ሰላም አስከባሪዎች ተጨማሪ 1,000 እስከ2,000 ኃይል ተጠይቆ
[33]በጉልበት እንዲወገድ ተደርጓል፡፡ በእርሱ ቦታም የረዥም ዘመን ወዳጃቸውን አስቀምጠዋል፣ ፓክት ኮሎንያልም አልተነካም፡፡
ይህን እንደምሳሌ ጠቀስነው እንጂ ለምሳሌ ጋዳፊን ከስልጣኑ እንዲወርድ የተደረገው በተመሳሳይ የብሔራዊ ጥቅሙንና የምእራባውያን የፋይናንስ የበላይነትን የሃገሩን የንግድ ሚዛን በመጠበቅና የወርቅ ክምችቱን በማብዛት ስለተቀናቀናቸው ነው፡፡ ከተባረረ በኋላ ሊብያ በአልቃይዳ ስር ገብታ ብሄራዊ ባንኳ ደግሞ በለንደን ፋይናንስ ከበርቴዎች እጅ ገብቷል፡፡ ለመጀመርያ ግዜም ባለ እዳ ሃገር ሁናለች፡፡
ጊኒ ጋርም ቢሆን መሪዋ መፈንቅለ መንግስት አድርጎ በጊኒ የነበረውን ቁንጮዎቹ ሲያተርፉበት የነበረውን የአደንዛዥ እጽ መስመር ከዘጋና የቀድሞ መሪ ልጅ (የእጹ ንግ ዋና መሪ የነበረውን ከቀጣ በኋላ) እና ከቻይና ጋር የ50 ቢሊዮን የመአድን ማውጣት ውል መፈራረሙ ፈረንሳዮችን መፈንቅል እንዲያደርጉበት አድርጓቸዋል፡፡
[34]
እነዚህ መሪዎች አምባገነን መሆናቸውን ልብ ይሏል፤ ሆኖም ግን ምእራባውያኑ ለዘመናት ወደስልጣን ከማምጣት ጀምሮ ከአምባገነኖች ጋር አብረው የሚሰሩ ሲሆኑ መሪዎቹ ለሃገራቸው የሚጠቅም መስራት ሲጀምሩ ነብስ ግድያ ሙከራዎችና እንዲወገዱ እንደሚያደርጉም ልብ ይሏል፡፡
መደምደምያ
ለምን የተባበሩት መንግስታትና “የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ” ከተበዳዮቹ አፍሪካውያን ሳይሆን ከበዝባዦቹ ጋር እንደሚወግኑ (ከምእራባውያን ትርፍራፊ ለቃሚዎች ውጪ ላሉት) ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፡፡ ስለአፍሪካውያን የአዞ እምባቸውን መራጨት ከመጀመራቸው በፊት ይህን በደላቸውን ሊመልሱ ይገባል፡፡
ይህ የቀኝ ገዢዎች ፖለቲከኞችና ፍሪሜሶኖች ስርዓት የአፍሪካ የወደፊት እጣ መሆን የለበትም፣ ዓይኑን ያወጣ ብልሹ ስርዓትን ለማስጠበቅ ሰራዊት እየላኩ ንጹሐንን መግደል ማንም ቢሆን ዲሞክራስያዊ ሂደት ማስጠበቅ ነው ብሎ አያስበውም፡፡
እየሆነ ያለው እውነት ይህ ነው፡፡ ዓረቦች፣ ህንድና ቻይና ህዝባቸውን ሊቀልቡ ሰፊ የእርሻ መሬት ከአፍሪካ ፈልገው መጥተው ካፒታል ሲያፈሱ ምእራባውያኑ (ያለፈውን አሳፋሪ የባርያ ስርዓትና የቅኝ አገዛዝ ውጊያቸውንና ጭፍጨፋቸውን እና አሁን ያስቀመጡትን አሳፋሪ ውል ዘንግተው)ኢንቨስትመንቱን (ህጸጽ ቢኖርበትም) “አዲሱ የደቡብ-ደቡብ (የድሃ-ድሃ) ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት አዲስ ቅኝ አገዛዝ ነው፣ መሬት ወረራ ነው ወዘተ.” ብለው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የስነ ምህዳር ተቆረርቋሪዎች ወዘተ. ለማዝመትና በሚድያቸው ለማስተጋባት የሚቀድማቸው የለም፡፡
አዲሱ ቅኝ አገዛዝ ግን አሜሪካ ሰራዊቷን በክፍለ ዓለሙ ማሰማራቷ፣ ከአሸባሪዎችና ሙስሊም ወንድማማችነት ጋር ሁና ችግር የምትፈጥረው እና እንደ ፈረንሳይ ያለው አሳፋሪ ውሎችና ደባዎችን አያወሩም (የአሜሪካውን በቀጣይ እመለስበታለው)፡፡ አሜሪካና አጋሮቿ አፍሪካን ቀጣይ አፍጋኒስታን ማድረግ እንጂ በሞኖፖል ሊይዙት የሚፈልጉትን የክፍለ ዓለሚቱን ተፈጥሮ ሃብት መነካካት እንደ ብሔራዊ ደህንነት ስጋታቸው ነው የሚቆጥሩት (በአፍሪካውያን ለአፍሪካውያን ቢሆንም)፡፡ የቀድሞ የአሜሪካ የደህንነት አማካሪው የኪሲንጀር ሪፖርት፡ የብሔራዊ ደህንነት ጥናት ሜሞራንደም 200 (NSSM 200) ይመልከቱ፡፡
ፍሪሜሶን መሪዎች ከምእራባውያን “ወንድሞቻቸው” ጋር በመጣመር የአፍሪካን ሕዝብ ነጻነት እንዳያገኝና ከተፈጥሮ ሃብቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በላይ ሲበዘብዙት ኑረዋል፡፡ አሁንም አፍሪካ በውጭ እዳ እና ጭቆና ተቆልፋ ትገኛለች፡፡ ሜሶኖቹ የባንክ ሂሳባቸውን እያደለቡ ለአፍሪካውያን አምባገነን “ወንድሞቻቸው” መዓርጎች እያከፋፈሉ ቅኝ አገዛዙን አስቀጥለዋል፡፡ ጆሞ ኬንያታ ነጮች መጽሐፍ ቅዱስ ለአፍሪካውያን ሰጥተው አይናችንን ጨፍነን ስንጸልይ መሬቱን ሁሉ ወሰዱት ብሏል ይባላል (ኢትዮጵያውን ቀድመን መጽሐፉን ስለያዝነው ሰጥተው የነጠቁን መሬት የለም፣ ያደረጉትም ሙከራ ከሽፏል)፡፡ ሆኖም ግን ለአፍሪካውያኑ የሜሶን ሽርጥ፣ ሜዳልያና ምልክቶች እያሸከሙ በእጅ አዙር እየገዟቸው ይገኛሉ፣ ይህን ይመስላል ፓን-አፍካዊነት፡፡ ይህን በመሰለ ሁኔታ ነው አንድ አፍሪካ እንዲመጣ ድጋፍ የሚያደርጉት ይህ ደግሞ ለነጻነት ሳይሆን ለባርነት ነው፡፡
“ሃራምቤ”መዝፈን ለመከልከልና የመበደል ስሜት ያወዳጃቸው አፍሪካውያንን ለማጣጣልና አትተባበሩ፣ በጠረጴዛ ዙርያ አትመካከሩ ለማለት አይደለም ይህ የአደባባይ ሚስጥር በግልጽ የቀረበው፣ ይልቁንም በፕሮፖጋንዳ የታወረውን ሕሊናችንን ክፍት አድርገን ሁኔታውን እና አስተሳሰባችንን እንድንፈትሽና መጪውን ትውልድ ለባርነት ሰንሰለት አሳልፈን እንዳንሰጥና ሙት ወቃሽ እንዳናደርገው እንድንጠነቀቅና አካሄዳችንንና ምርጫችንን እንድናርምና መሪዎቻችንንና ፖለቲከኞቻችንን ደግሞ ይህንኑ እንድናሳውቅ ነው፡፡