
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 21/2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን አጽድቆ ኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያን ከሚጠቀሙ አገራት መካከል እንድትካተት በር ከፍቷል።
ፋይዳ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ዲጂታል መታወቂያ ‘አንድን ሰው’ በልዩ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ነው ተብሎለታል።
መታወቂያው በሙከራ ደረጃ ሲተገበር ቆይቶ የአዋጁን መውጣት ተከትሎ በይፋ ተግባራዊ መሆን የጀመረው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ተቋማት ለሚሰጡት አገልግሎት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን በአስገዳጅ ጥቅም ላይ እንዲውል በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የተያያዙ ሊያውቋቸው ለሚገቡ ስምንት ወሳኝ ጥያቄዎች ምላሽ እነሆ . . .
ፋይዳ መታወቂያ ምንድን ነው?
የፋይዳ ቁጥር የሚባለው የዲጂታል መታወቂያ ሲሆን፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰዎችን የተመጠነ ግላዊ መረጃዎችን (የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ) በመሰብሰብ “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል መርኅ እያንዳንዱን ዜጋ በልዩ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ያስረዳል።
በውስጡም መሠረታዊ የግል መረጃ የሚባሉትን ስም፣ ፆታ፣ የትውልድ ቀን እና የመኖሪያ አድራሻን ይይዛል። በተጨማሪም ለኮሙኒኬሽን እና ለማረጋገጫ የሚያገለግሉ ኢሜይል እና ስልክ ቁጥርን አካቷል። ዋናው መረጃ ደግሞ ባዮሜትሪክ ነው፤ ይህም የሁለት የዓይን፣ የአስሩም የእጅ ጣቶች እና የፊት አሻራን ይይዛል።
እነዚህ መረጃዎች ከተሰበሰቡ በኋላ ተጨምቆ ወደ 12 አሃዝ ልዩ ቁጥር እና ወደ 16 አሃዝ ተለዋጭ ቁጥር ተቀይሮ ለተመዝጋቢው ይሰጣል።
አንድ ሰው “ተመዝግቦ ቁጥር ደረሰው ማለት ዲጂታል መታወቂያ አለው ማለት ነው” ሲሉ የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ዋና አስተባባሪ አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት ማንኛውም ዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት መሠረታዊ የግል መረጃን በመስጠት የተመዘገበ ነዋሪ የዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት አለው ይላል አዋጁ።
በአካል ጉዳት ወይም በሌላ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ተመዝጋቢው መረጃዎችን መስጠት አለመቻሉ ከተረጋገጠ፣ በፎቶግራፍ ብቻ በመመዝገብ ዲጂታል መታወቂያው ሊሰጥ ይችላል።
በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የሚመዘገቡ እና በዲጂታል መታወቂያ ማስረጃ ላይ የሚገለፁ የግል መረጃዎች በፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ፣ ምዝገባ በሚካሄድበት ክልል የሥራ ቋንቋ እና በእንግሊዝኛ ይሰፍራሉ።
በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የሚመዘገብም ሆነ በዲጂታል መታወቂያ ማስረጃ ላይ የሚወጣ መረጃ ተቋሙ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ሊመዘገብ ይችላል።
ከፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚነት መታገድ ይኖራል?
ለፋይዳ የተመዘገበን ሰው የሚታገድበት ወይንም የሚሰረዝበት አሠራር የለም። ሊደረግ የሚችለው መቆለፍ (ሎክ) ማድረግ ነው።
ይህም ማለት የግለሰቡ የባዮሜትሪክ መረጃ ሳይዘረዝ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ ማድረግ ነው። ይህ ሂደት መረጃዎችን የሚያጠፋ አይደለም።
በተመዝጋቢው ፍላጎት ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የዲጂታል መታወቂያ ልዩ ቁጥር ሊቆለፍ ወይም ከሥራ ውጪ እንዲሆን ሊደረግ ይቻላል።
ለምሳሌ አንድ ሰው ከአገር ቢወጣ እና መታወቂያውን መጠቀም አልፈልግም ቢል መረጃው እንዲቆለፍበት ይደረጋል። ወይም አንድ ሰው በመረጃ ስህተት (በግለሰቡ ወይንም ደግሞ የግለሰቡ ባልሆነ ምክንያት) የፋይዳ ቁጥር ካገኘ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ የሚደረግ ይሆናል።
አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ቁጥሩ ለሌላ ሰው አይሰጥም። የተመዝጋቢው ሞት ከተረጋገጠ፤ ተቋሙ ልዩ ቁጥሩ ሳይቀየር እንደጸና እንዲቆይ እና ለማረጋገጥ አገልግሎት ሥራ ላይ እንዳይውል እንደሚደረግ በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።
የግላዊ መረጃዎች ጥበቃ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?
ማንኛውም ተመዝጋቢ ፈቃዱን በግልጽ ሳይሰጥ በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የተመዘገቡ የግል መረጃዎችን መውሰድ፣ ማሰራጨት፣ ማተም፣ መጠቀም፣ መረጃውን መስጠት ወይም ቅጂውን ለሦስተኛ ወገን ወይም አካላት መስጠት ወይም ይፋ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን አዋጁ ደንግጓል።
አቶ ዮዳሄ እንሚሉት የአንድ ሰው አሻራ በፋይዳ መታወቂያ የመረጃ ቋት ውስጥ ስለገባ ባለቤትነቱን አጣህ ወይም መሥሪያ ቤቱም መረጃውን እንደልቡ ያደርገዋል አለመሆኑን እና በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የተሰበሰበ ማንኛውም የተመዝጋቢ ግላዊ መረጃ ባለቤት ተመዝጋቢው ነው።
“የግል መረጃ እንዲሰጥ የሚፈቀደው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ ከመጣ ብቻ ነው። ስለሆነም ለሦስተኛ ወገን (ለግለሰብም ሆነ ለመንግሥት) መረጃው ያለ ግለሰቡ ፈቃድ አይተላለፍም።”
ስለዚህም መረጃዎች በሕግ ጥበቃ የሚደረግለት ከመሆኑ በተጨማሪም የተቆለፈ ወይንም ኢንክሪፕት የተደረገ መሆኑን ማስተማመኛ የሚሰጡት ኃላፊው፣ የተቋሙ የመረጃ ሠራተኞች (ተቆጣጣሪዎች) እንኳን መረጃውን እዲያገኙ አይደረግም።
በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የተሰበሰበ የማንኛውም ተመዝጋቢ ግላዊ መረጃ ያለ ተመዝጋቢው ፈቃድ ለሌላ ሰው መግለጽ፣ ማስተላለፍም ሆነ እንዲለወጥ ማድረግ የተከለከለ መሆኑንም አዋጁ በግልጽ አስቀምጧል።
በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት የግል መረጃ ሊገለጽ ወይም ሊተላለፍ የሚችል ሲሆን፣ በዚህ ሁኔታ በተገቢው ሁኔታ የተላለፈው መረጃ የሚያገለግለው ወይም ጥቅም ላይ የሚውለው ለተፈለገው አገልግሎት ብቻ እንደሚሆንም ደንግጓል።
ፋይዳን አስገዳጅ ያደረጉ ተቋማት የትኞቹ ናቸው?

አገልግሎታቸውን ከፋይዳ ጋር መታወቂያ ጋር ያስተሳሰሩ ተቋማት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል ኢትዮ ቴሌኮም የሚጠቀስ ሲሆን፣ ሌሎች ከ30 በላይ ተቋማትም ተመሳሳዩን ማድረጋቸውን አቶ ዮዳሄ ገልጸዋል።
በርካታ ተቋማት አገልግሎታቸውን ከማስተሳሰራቸው በተጨማሪ አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳ መታወቂያን አስገዳጅ ሲያደርጉ፤ የገቢዎች ቲን ቁጥርን ለማውጣት የፋይዳ መታወቂያን መያዝ ቅድመ ሁኔታ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ የባንክ አካውንት ለመክፈት ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ በግዴታ እንዲቀርብ ያደረገ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ደንበኞች የትኛውንም የባንክ አገልግሎት ለማግኘት የፋይዳ መታወቂያ እንዲይዙ ይገደዳሉ።
ከሰኔ 24/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ አስገዳጅ አሠራር በሀገሪቱ “ዋና ዋና ከተሞች” ተግባራዊ መሆን ይጀምራል። ከዚያም በሚቀጥለው ዓመት ታኅሣሥ ወር ደግሞ በመላው ሀገሪቱ የባንክ አካውንት ለመክፈት የፋይዳ’ ዲጂታል መታወቂያ መያዝ አስፈላጊ እንሚሆን ተገልጿል።
በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ አስተዳደር ስር የሚገኙ በርካታ አገልግሎቶች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በአስገዳጅነት እንደ ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጡ ይገኛል።በተጨማሪም በርካታ የፋይናንስ እና ቴሌኮም ተቋማት አገልግሎቶች፣ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች፣ ሰነድ ማስመዝገብ እና ማረጋገጥ፣ የትራንስፖርት እና መጓጓዣ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በፋይዳ መታወቂያ አማካኝነት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።