Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

ጀርመን የኤርትራ መንግሥትን ለመገልበጥ አሲሯል ያለችውን የብርጌድ ንሃመዱን ቡድን “በአገር ውስጥ አሸባሪነት”ፈረጀች

$
0
0
የኤርትራ ተቃዋሚዎች በጀርመን

የጀርመን ባለስልጣናት የኤርትራን መንግሥትን የመገልበጥ ዓላማን አንግቧል ባሉት ብርጌድ ንሃመዱ በተሰኘው እንቅስቃሴ ተሳትፎ በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ በስድስት ግዛቶች የፖሊስ ዘመቻ መጀመራቸው ተገለጸ።

በተለያዩ የውጭ አገራት ሁከትና ብጥብጥ አስነስቷል የተባለው የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚው ብርጌድ ንሃመዱ በጀርመን ህግ መሰረት “በአገር ውስጥ አሸባሪነት” መፈረጁን የአገሪቱ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት በመግለጫው ማስታወቁን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ቢያንስ ለባለፉት ሶስት ዓመታት በጀርመን በሚገኘው የብርጌድ ንሃመዱ ቅርንጫፍ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ አላቸው የተባሉ አስራ ሰባት ተጠርጣሪዎች መለየታቸውን ጽህፈት ቤቱ አትቷል።

ባለስልጣናቱ የኤርትራን መንግሥት የመገልበጥ ዓላማ አንግቦ የሚንቀሳቀስ የዓለም አቀፍ ኔትወርክ መረብ አካል ነው ሲሉ በፈረጁት በዚህ ቡድን ላይ ፖሊስ ረቡዕ፣ መጋቢት 16/ 2017 ዓ.ም በስድስት ግዛቶች ወረራዎችን ማካሄዳቸውን የዜና ወኪሎች አስነብበዋል።

ከ200 በላይ የፌደራል እና የክልል ፖሊሶች በአገሪቱ በሚገኙ ስድስት ግዛቶች በ19 ንብረቶች ላይ ፍተሻ አድርገዋል። ከጀርመን በተጨማሪ በዴንማርክም እንዲሁ በተመሳሳይ ወቅት ፍተሻ መካሄዱን የጀርመን የዜና ወኪል ዲፒኤ ዘግቧል። ሆኖም እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር የዋለ እንደሌለ ተገልጿል።

በበርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ጨቋኝ ተብሎ የሚጠራው የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ መጠነ ሰፊ ጥሰት በመፈጸም ይከሰሳል።

በዚህም ምክንያት በኤርትራ ያለውን የፖለቲካ እና የእምነት ነጻነት ጭቆና እንዲሁም የጊዜ ገደብ የሌለውን አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ በርካቶች ኤርትራውያን አገር ጥለው ይሰደዳሉ።ኤርትራን እየገዙ ባሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ላይ ከዚህ ቀደም በዳያስፖራው ተቃውሞች ቢሰሙም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን መልኩን እየቀየረና የአገዛዙ ደጋፊዎች የሚያዘጋጁዋቸውን በዓላት በመቃወም በሚነሱ ግጭቶች ደም መፋሰሶች እየታዩ ነው።

በቅርቡም የእስራኤል ፓርላማ መንግሥታቸውን የሚደግፉ የኤርትራ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ያለመውን ረቂቅ ሕግ የመጀመሪያውን ዙር በሙሉ ድጋፍ አሳልፏል።

የስዊዘርላንድ የተወካዮች ምክር ቤት የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ ኤርትራውያንን በሶስተኛ አገር አድርጎ ወደ አፍሪካ የሚመለሱበትን ፕሮግራም አጽድቋል።

ለንደንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በሚነሱ የደጋፊ እና ተቃዋሚዎች ግጭት የተነሳ የዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣናት ኤርትራውያን የሚያከብሩት ፌስቲቫል ሰርዘዋል።

የጀርመን አቃብያነ ህግ ተጠርጣሪዎቹ በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ የኃላፊነትን ቦታዎችን እንደያዙ ምርመራዎች ይጠቁማሉ ብለዋል።

በጀርመን፣ ቡድኑ ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ባላቸው ፌስቲቫሎች ላይ በተቀናጁ ሁከቶች ተሳታፊ ነው በሚል ተወንጅሏል።

አቃቤ ህግ በነሐሴ 2022 በጂሰን የተካሄዱ ፌስቲቫሎች እንዲሁም በመስከረም 2023 በስቱትጋርት የነበረ የኤርትራውያን ማህበር ሴሚናርን ዋቢ አድርጓል።

በነዚህ ዝግጅቶች ላይ የከፋ ጉዳትን ጨምሮ በርካታ የፖሊስ አባላት መቁሰላቸውን እንዲሁም በርካታ ተቃዋሚዎች መታሰራቸው ተገልጿል።

በአውሮፓውያኑ 2023 በስቱትጋርት የተቀሰቀውን ረብሻ ተከትሎ 56 ሰዎች በእስር እንዲቀጡ ተደርገዋል። አንዳንድ የእንቅስቃሴው አባላት በጀርመን የመንግሥት ተቋማት እና ፖሊስ አባላት ላይ የሚደርስን ጥቃት ህጋዊ አድርገው እንደሚቆጥሩትም አቃብያነ ህግ መግለጻቸውን የዜና ወኪሎች አስነብበዋል።

በኔዘርላንድ እና በጀርመን ባሉ የብርጌድ ንሃመዱ ቅርንጫፎች ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ በመያዝ የተጠረጠረና ባለፈው የካቲት በሄግ በነበሩ ግጭቶች ግጭት ተሳትፏል የተባለ ግለሰብ የሆላንድ ፍርድ ቤት የብዙ ዓመታት እስር እንደተፈረደበት ይኸው የአቃቤ ህግ መግለጫ ጠቁሟል።በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች ዘ ሄግ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ ተቃዋሚ ኤርትራውያን ተገኝተው በተሽከርካሪዎች፣ በሌሎች ንብረቶች እና በፖሊስ ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ ነው የግጭቱ አስተባባሪ እና ዋነኛ ተሳታፊዎች ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ተይዘው ክስ የተመሰረተባቸው።

መስከረም 13/2017 ዓ.ም. ብይን የሰጠው የአገሪቱ ፍርድ ቤት ዋነኛ የግጭቱ መሪ ነው በተባለው የ48 ዓመቱ ዮሐንስ አብረሃ ላይ የአራት ዓመታት እስር ሲፈርድ በሌሎች ላይ በተለያየ መጠን የወራት የእስር ቅጣት አስተላልፏል።

በተያያዘ በስዊድን በአውሮፓውያኑ 2023 በኤርትራ የባህል ፌስቲቫል ላይ በተቀሰቀሰ ሁከትና ብጥብጥ የተጠረጠሩ ስድስት ሰዎች በፍርድ ቤት ከአምስት -ስድስር ወራት እስር እንደተፈረደባቸው የስዊድን የዜና ወኪል ቲቲ ዘግቧል።

በወቅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ተቃዋሚዎች ፌስቲቫሉን ጥሰው መግባታቸውን እና በዚህም ከ50 ሰዎች በላይ መቁሰላቸው አና ወደ 140 የሚጠጉ መታሰራቸው ተዘግቧል።

ከኤርትራ የትጥቅ ትግል ጀምሮ በውጭ አገራት ጠንካራ የማህበረሰቦች አደረጃጀትን መፍጠር የቻለው የኤርትራ መንግሥት በሰኔ መጨረሻ የሚከበረውን የሰማዕታት እና የግንቦት የነጻነት በዓሎችን በኤምባሲው እና በደጋፊዎቹ አማካኝነት ሲያከብር ቆይቷል።

ነገር ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት አገዛዙን የሚቃወሙ እና የኤርትራ መንግሥት እነዚህ ክብረ በዓላትን ለፕሮፓጋንዳ እና ገንዘብ ለማሰባሰብ ይጠቀምበታል የሚሉ ‘ብርጌድ ንሃመዱ’ የሚባል ቡድን ድንኳኖችን ማቃጠል ጨምሮ ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም እየተቃወሙ ይገኛሉ።

በአገሪቱ የተረቀቀው ሕገ መንግሥት ተግባራዊ እንዲደረግ፣ ምርጫ እንዲካሄድ፣ የፖለቲካው ምህዳር እንዲሰፋ፣ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የታሰሩ እንዲፈቱ እና ለብዙ ወጣቶች ፍልሰት ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለት ገደብ የለሽ ወታደራዊ አገልግሎት እንዲቆምና መሰል ጥሪዎች ተደጋግመው ተሰምተዋል።

በደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች በተነሱ ሁከቶች የተነሳ በተለያዩ አገራት የፓሊስ አባላት ጨምሮ በኤርትራውያን እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

ከቅርብ ግዜያት ወዲህ የኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅትን ምክንያት በማድረግ በኤርትራውያን መካከል በአውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ግጭት ሲፈጠር መመልከት የተለመደ ሆኗል።

በባለፉት ዓመታት እስራኤልን ጨምሮ በጀርመን፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ እና በካናዳ ብዙዎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭት ተከስቷል።

ዜና ምንጭ BBC NEWS https://www.bbc.com/amharic/articles/c8719qy99d0o


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>