
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትራምፕ አስተዳደር ከተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር መጋቢት 18/ 2017 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ በሆነ መልኩ መወያየታቸው ተገለጸ።
ማርኮ ሩቢዮ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከር አክሎ በጋራ ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ በስልክ መነጋገራቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያስረዳል።
አገራቱ በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትን ማምጣት አንድ የውይይታቸው ርዕስ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስን ዋቢ ያደረገው መግለጫ አትቷል።
በሪፐብሊካኑ የትራምፕ አስተዳደር የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አገራቸው ለሰላማዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠውላቸዋል ተብሏል።
ትራምፕ በመጀመሪያ አስተዳደራቸው ወቅት ግብጽ የህዳሴ ግድብን ታፈነዳለች ማለታቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን ያሳዘነ ነበር።
በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ ተቀማጭ የሆኑትን የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይኖርን ጠርተው ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሰጡት አስተያየት ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀው ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቅምት 13፣ 2013 ዓ.ም ሱዳን እና እስራኤል ግንኙነታቸውን ለማደስ የደረሱበትን ስምምነት አስመልክቶ ከሱዳን ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ እና ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅትም ነው የህዳሴ ግድብን ጉዳይን ያነሱት።
“ግብፅ በዚህ መንገድ መቀጠል ስለማትችል ሁኔታው አደገኛ ነው። ግብፅ የህዳሴ ግድብን ታፈነዳለች፤ አሁንም በግልፅ እናገረዋለሁ ግብፅ በድጋሚ ታፈነዳዋለች” በማለት በተደጋጋሚ የተናገሩት ትራምፕ
“ስምምነት ለአገራቱ ባቀርብም ኢትዮጵያ ስምምነቱን ሳትቀበል ቀርታለች። አንደዚያ ማድረግ አልነበረባቸውም ይህ ትልቅ ስህተት ነው። በዚህም ምክንያት የምንሰጣቸውን ብድር አቁመናል። ስምምነቱን ካልተቀበለች በስተቀር ኢትዮጵያ ያንን ገንዘብ አታየውም ” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
አቶ ገዱ አክለውም በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል እንዲህ ጦርነት የሚያጭር ነገር ከተቀማጭ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሰማቱ የሁለቱን አገራት የቆየ ግንኙነትና ጥምረት አያሳይም እንዲሁም አገራቱን በሚገዛው የአለም አቀፍ ህግም ተቀባይነት የለውም ማለታቸውንም በወቅቱ የወጣው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አመላክቷል።
ከአራት ዓመታት በፊት በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የአፍሪካ አገራትን በማንቋሸሽ እና በጸያፍ ዘለፋዎች በመንቀፍ ይታወቃሉ ትራምፕ።
“የአሜሪካን ታላቅነት በድጋሚ ለማምጣት” በተደጋጋሚ የሚምሉት ትራምፕ ፀረ-ስደተኝነት፣ፀረ- ሙስሊም የሆኑ ንግግራቸው እና አቋማቸውን ደጋግመው አንጸባርቀዋል።
ከሥልጣን ወርደው ለሁለተኛ ጊዜ በመመረጥ ታሪክ የሠሩት ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐቢይ ለሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአሜሪካ የምርጫ ውጤት በይፋ ሳይገለጽ ነበር”በምርጫ ድልዎት እና ወደ ሥልጣን በመለለስዎ እንኳን ደስ አለዎት ማለት እፈልጋለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኤክስ ገጻቸው ላይ መልዕክታቸውን አስፍረው ነበር።
አክለውም “በእርስዎ የሥልጣን ዘመን የሁለቱን አገራት ግንኙነት በበለጠ ለማጠናከር በጋራ የምንሠራበትን ጊዜ እጠብቃለሁ” ሲሉም በዚሁ መልዕክታቸው ላይ አትተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሥልጣን የቆዩባቸው የባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ አራቱ በዲሞክራቶች የሥልጣን ዘመን ነው።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት ምክንያት በተፈጸሙ ጥሰቶች በርካታ ማዕቀቦች በአሜሪካ መጣላቸው ከዴሞክራቶች ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻክር አድርጎታል።
ከእነዚህም ውስጥ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በትግራይ ጦርነት ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መፈረማቸው ይታወሳል።
ማዕቀቡ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ክልል አስተዳደር እና የህወሓት አመራሮችን ተጠያቂ የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጿል።
ዕቀባው ግጭቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ ተኩስ አቁሙን የተከላከሉ በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ወይም ተባባሪዎቻቸው ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ባይደን በጊዜው አስታውቀው ነበር።
የምጣኔ ሀብት እና የደኅንነት እገዛ እንዲቋረጥ፣ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ የመከላከያ ወታደራዊ ንግዶች ላይ ገደብን አሜሪካ የጣለች ሲሆን፣ በተጨማሪም በባለሥልጣናት ላይ የጉዞ እቀባ ተጥሎ ነበር።
ባለፈው ዓመት ጳጉሜ ወርም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችለውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም መወሰናቸው አስታውቀዋል።
ሌላኛው የአሜሪካ መንግሥት ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት የዘረጋው ከቀረጥ ነጻ ዕድል (አጎዋ) ተጠቃሚ የነበረችው ኢትዮጵያ እየተካሄደ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ከተጠቃሚነት ውጪ እንድትሆን መደረጓ ይታወሳል።
በጦርነቱ ወቅት የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሻክሮ የነበረ ሲሆን፣ አሜሪካም በጦርነቱ የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን በመንቀስ ስታወግዝ ቆይታለች።
በዚህም ምክንያት የዲሞክራቶች ከዋይት ሐውስ መውጣት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት አዲስ መስመር ወይም አዲስ ዕድል የሚያመጣ ሊሆን ይችላል ብለው ሊያስቡ እንደሚችሉ ተንታኞች ይናገራሉ።
የትግራይ ጦርነት ቢቋጭም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ውስጥ ያሉ ግጭቶች የቀጠሉ ሲሆን፣ የትራምፕ ፖሊሲ ይህንን አስመልክቶ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው የሚታይ ይሆናል።