Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

ኢሕአፓ በኮሪደር ልማት ምክንያት ሜዳ ላይ ተጣሉ ላላቸው 455 አባወራዎች መንግሥት መልስ እንዲሰጥ ጠየቀ

$
0
0
  • ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሊወስደው እንደሚችል ገልጿል
  • ‹‹ሕጋዊ ከሆኑ አንድም ሰው እንዲጎዳ ስለማንፈልግ እናስተናግዳቸዋለን››

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያከናወነ ባለው የኮሪደር ፕሮጀክት ምክንያት ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ይኖሩ የነበሩና ያለ ምትክና ካሳ ተፈናቀሉ ላላቸው 455 ይሆናሉ ለተባሉ አባወራዎች ምላሽ እንዲሰጥ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ጥያቄ አቀረበ፡፡

በኮሪደር ልማቱ ተፈናቅለው ሜዳ ላይ መውደቃቸውን የሚገልጽ ባለ 15 ገጽ የተፈራረሙበት ደብዳቤ የደረሰው ኢሕአፓ፣ በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ ለ27 ዓመታት እንኖርበት ነበር ካሉት በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው ሰላም አምባ ከሚባል አካባቢ ያለ ምንም ካሳና ምትክ ቤታቸው መፍረሱን በፊርማቸው አረጋግጠው የጻፉት 455 አባዎራዎች ቢሆኑም፣ በአካባቢው ከአሥር ሺሕ በላይ አባወራዎችና እስከ መቶ ሺሕ የሚደርስ ቤተሰብ ያለበት ሰፈር መሆኑን በደብዳቤያቸው መግለጻቸውን ኢሕአፓ አስታውቋል፡፡ በኖሩባቸው ሦስት አሥርት ዓመታት የሚጠጋ ጊዜ ከቦሌ ክፍለ ከተማና ከወረዳው የመንግሥት አካላት ጋር በመተባበር ነዋሪው ገንዘብ በማዋጣት ስልክ፣ መብራት፣ ውኃና የጤና ተቋም እንደነበራቸውና እንደ ማንኛውም ዜጋ በአካባቢው ቤታቸውን ሠርተው ይኖሩ እንደነበር በደብዳቤው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ለታላቁ ህዳሴ ግድብና ለአገር መከላከያ ሠራዊት የገንዘብና የቁሳቁስ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት አካላት ቦታው ለኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እንደሚፈለግ በማስታወቅ፣ ያለበቂ ውይይትና ዝግጅት በሦስት ቀናት ውስጥ ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ፣ ምንም ዓይነት ምትክ ቦታም ሆነ ቤት ሳያገኙ በረንዳ ላይ መውደቃቸው በደብዳቤው ተጠቁሟል፡፡ ከፈረሰው መንደር ውስጥ የተወሰኑት ቤቶች የይዞታ ካርታ እንዳላቸውና የተወሰነው ይዞታ ሕጋዊ ሆኖ ካርታ የሌለው መሆኑን የጠቀሱት አንድ ቤታቸው የፈረሰባቸው አስተያየት ሰጪ፣ ቤታቸው ከመፍረሱ በላይ ካሳ አለማግኘታቸው እንቆቅልሽ ሆኖብኛል ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ቤቱ ሲፈርስ ለምንና እንዴት ብለን ለመጠየቅ የምንችለው ሰው አጣን›› የሚሉት አንድ ዕድሜያቸው ገፋ ያሉ አባት፣ ‹‹ቤቱ ከፈረሰበት ኅዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ መንገድ ላይ ወድቀናል በማለት፣ ‹‹ልማትን የምንደግፍ መሆናችንን ጠቅሰን ለፈረሰብን ቤት ምትክ ይሰጠን ብለን ብንጠይቅ፣ ከሁሉም አይመለከተንም የሚል መልስ ነው ያገኘነው፤›› ማለታቸው በደብዳቤው ተመልክቷል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ጉዳዩ ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለአሜሪካና እንግሊዝ ኤምባሲዎች፣ እንዲሁም ለሌሎችም ተቋማት ጉዳያችንን ይወቁልን ብለው ደብዳቤ እንደጻፉ ተብራርቷል፡፡ ቦታውን በግዥና በስጦታ ያገኘነው ነው የሚሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ከይዞታ ማረጋገጫ ወደ ካርታ እንዲቀየር በተደጋጋሚ ቢጠየቅም አንዱ ኃላፊ ሲመጣ ሌላው ሲሄድ፣ አንዱ ገንዘብ እየበላ፣ ያልበላው ሲመጣ ኃላፊዎች ሲቀያየሩ ጉዳዩን እንደ አዲስ ከማቅረብ ውጪ መፍትሔ ማግኘት አለመቻላቸውን አስተያየት ሰጪው መናገራቸው ተገልጿል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ቤቱን በመፍረሱ ባለንብረቶች የሚጠይቁትና የሚሰማቸው አካል ባለመገኘቱ ነዋሪዎች ተደራጅተው ስለጉዳያቸው ለመምከር ጥረት ሲያደርጉ፣ ይህን የሚያስተባብሩ አካላትን በማሳደድ ለእስር እንደተዳረጉ መናገራቸው፣ ጉዳያቸውን ለከንቲባዋ ለማቅረብ ሞክረው ወደ ግቢ ለመግባት አለመቻላቸው በደብዳቤው ተካቷል፡፡ መንግሥት ሲጠየቅ ‹‹ሕገወጥ ናችሁ›› የሚል መልስ ተሰጠን የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደር ድረስ ምላሽ ጠፍቷል ማለታቸው ተገልጿል፡፡  ማንኛውንም ዓይነት የመብት ጥያቄ ይዞ የሚንቀሳቀስ ሰው ተፈልጎ እንዲታሰር በማድረግ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቁመው ብዙዎች በፖሊስ ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው መናገራቸው በደብዳቤው ተመልክቷል፡፡ ‹‹እንደ ዜጋ እየተቆጠርን አይደለም፣ ቆሻሻ ከየመንገዱ በመኪና እየተነሳ እኛ ደግሞ በቆሻሻው ፈንታ መንገድ ዳር ተጥለናል፤›› ማለታቸውም ተገልጿል፡፡ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ለሪፖርተር በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሕጋዊነታቸው ታይቶ ከተማ አስተዳደሩ ምላሽ አልሰጣቸው ወይም ቅሬታቸውን አልተቀበለም ከተባለ ምላሽ መስጠት ይቻላል ብለዋል፡፡ የሚቀርቡት አንዳንዶቹ ክሶችና ጥያቄዎች ተገቢነትና ሕጋዊነት የሌላቸው እንደሆኑ ገልጸው፣ ለሁሉም ሰው ቤትና መሬት መስጠት እንደማይቻልና ከመልካም አስተዳደር አንፃር የተጎዱና የተቸገሩ አካላት እየተስተናገዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ተገቢነት ያላቸው ቅሬታዎች ካሉ አንድ ሰው እንዲጎዳ አንፈልግም፣ እናስተናግዳቸዋለን፤›› ያሉት አቶ ጥራቱ፣ ተገቢነትና ማስረጃ የየሌላቸው ከሆኑ አሠራሩ በዚያ መንገድ በመሆኑ ላይስተናገዱ ይችላሉ ብለዋል፡፡ ከኮሪደር ሥራ ጋር በተገናኘ ማንኛውም ሕጋዊ የሆነ ማስረጃ ያለው ሰው ከወረዳ እስከ ከተማ ድረስ የተደራጀ የቅሬታ ሰሚ አካል በመኖሩ በዚያው ልክ እንደሚስተናገድ ገልጸዋል፡፡ ሕገወጥ ግንባታ ገንብተው በኮሪደሩ ምክንያት በሚነሳበት ወይም በሚፈርስበት ጊዜ የማይገባቸውን የመብት ጥያቄ ያነሱ እንደማይስተናገዱና ምክንያቱም ከሕገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ቅሬታውን የተቀበለው ኢሕአፓ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ፓርቲያቸው ከዚህ ቀደም ከኮሪደር ልማት ጋር በተገናኘ የሚፈርሱ ቤቶችን በተመለከተ የዜጎችን ቅሬታ ተቀብሎ ያቀረበውን የመፍትሔ ጥሪና መግለጫ፣ መንግሥት ሐሰት መሆኑንና ለፖለቲካ ፍጆታ የወጣ ነው በሚል ማስተባበሉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እውነታው አሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤታቸው እየፈረሰ መሆኑን፣ ተፈራርመው ወደ ቢሯችን መምጣታቸውን፣ ሕዝብ ላይ በተጨባጭ በደል መኖሩን በማስረጃ እያሳየን ነው፤›› ብለዋል፡፡ መጋቢ ብሉይ መንግሥት ፕሮጀክቱ ማኅበረሰብ ተኮርና ዜጋ ተኮር ነው ቢልም፣ ዜጋም ማኅበረሰብም ተኮር አለመሆኑንና የበለጠ ጎዳና ተዳዳሪ እንደሚያደርግ የሚያሳይ መረጃ ነው በማለት ገልጸው፣ ‹‹መንግሥት በኮሪደር ልማት ሽፋን ዜጎችን መንገድ ላይ እየጣለ መሆኑን ተጨባጭ መረጃ እያገኘን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ማኅበራዊ ቀውስ እየፈጠረ ያለና ዜጎችን ወዳልሆነ መንገድ እያስወጣ ያለ ፕሮጀክት ነው ያሉት ተቀዳሚ ፕሬዚዳንቱ፣ የፕሮጀክቱ አካሄድ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ገበሬ ሲፈናቀል ካሳ እየተሰጠ እነዚህ ዜጎች ለዓመታት ለረዥም ጊዜ ቤት ሠርተው የኖሩበት በመሆኑ ተገቢው ካሳ ይሰጣቸው፤›› ያሉት መጋቢ ብሉይ፣ መንግሥት ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ኢሕአፓ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ማዋቀሩንና በፍርድ ቤት እንዲታይ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ‹‹ትልቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው›› ያሉት ተቀዳሚ ፕሬዚዳንቱ፣ ፓርቲያቸው ቦታው ድረስ ኮሚቴ ልኮ ተመልክቶና አጣርቶ መመለሱን አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዞ ከመሄድ በተጨማሪ ሌሎች መሰል አቤቱታዎች እየመጡለት መሆኑን ጠቅሰው፣ በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ሰላማዊ ትግል ይደረግበታል ብለዋል፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>