Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 937

አይኤምኤፍ ብሔራዊ ባንክ ገለልተኛ ሆኖ እንዲሠራ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ አደረገ

$
0
0


የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከመንግሥት ተፅዕኖ ውጪ ሆኖ በራሱ ለመወሰን የሚያስችለው ተቋማዊ ነፃነት መረጋገጥ እንደሚገባው፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ አደረገ።

ይህ የተገለጸው የአይኤምኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስታሊና ጆርጂዬቫ ከየካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ ይዘት አስመልክቶ፣ ከገንዘብ ሚኒስትሩ ከአቶ አህመድ ሺዴ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ነው።

ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ የብድር ምጣኔዎችን የሚያረጋጋ፣ የብድር ክፍያዎችን ዝቅ ማድረግ የሚያስችልና የዋጋ ግሽበትን የሚያወርድ የሞኒተሪ (ገንዘብ) ፖሊሲ መኖር፣ የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ የተነቃቃ እንዲሆን ለማስቻል ወሳኝ በመሆኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ከገዥው ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ ከመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ መሆንና ውሳኔዎቹ ገለልተኛ የመሆናቸው አስፈላጊነት ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ትግበራ አፈጻጸምን በመገምገም፣ በአጠቃላይ ለማሻሻያ ፕሮግራሙ ከፈቀደው አጠቃላይ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ሁለተኛውን ዙር ብድር ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ማፅደቁ የሚታወስ ሲሆን፣ የፕሮግራሙ አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት ትኩረት የተደረገባቸውን ጉዳዮች ዝርዝር ያካተተ ሪፖርት ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

በዚህ ሪፖርት በትኩረት ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል፣ ከመፅደቁ በፊት አይኤምኤፍ የተመለከተውና በኋላም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ይገኝበታል።

የገንዘብ ተቋሙ ሪፖርት አዋጁ የብሔራዊ ባንክን አሠራር እንደሚያዘምን ቢገልጽም፣ ከመንግሥት ተፅዕኖ ውጪ ሆኖ በራሱ ለመወሰን የሚያስችለውን ተቋማዊ ነፃነት ከመስጠትና ባንኩን ከሚመለከቱ ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች አኳያ ጉድለቶች እንዳሉበት አብራርቷል።

ከእነዚህም በአዋጁ ምላሽ ያላገኙ ወሳኝ ክፍተቶች በሚል ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል፣ በሥራ ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት (ሚኒስትሮችን ጨምሮ)፣ በብሔራዊ ባንክ ቦርድ ውስጥ እንዳይካተቱ የሚከለክል አንቀጽ አለመኖሩ አንዱና ዋናው ነጥብ ሆኖ መጠቀሱን መዘገባችን ይታወሳል።

በተጨማሪም የሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ባለሥልጣናት ያልሆኑ ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎችም በብሔራዊ ባንክ ቦርድ ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ መያዝ እንደሌለባቸው የሚከለክል ድንጋጌ በአዋጁ ውስጥ አለመካተቱ፣ እንዲሁም የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ ምክትል ገዥዎችና የቦርድ አባላት የሚሾሙበት ባለሁለት ድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት (Double Veto Procedure) በአዋጁ መካተት ነበረበት ሲል የገንዘብ ተቋሙ ሪፖርት ጠቁሟል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መነጋገሩን ያመለከተው አይኤምኤፍ፣ የገንዘብ አዋጁ ለብሔራዊ ባንክ የሚሰጠው የነፃነት ደረጃ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ምርጥ ተብለው ከሚታወቁ ነባር አሠራሮች አንፃር ውሱንነት ያለበት መሆኑን ባለሥልጣናቱ እንደሚረዱ፣ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ሁኔታና ቀድሞ ከነበረው ሕግ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሻሻል የተደረገበት መሆኑን እንደገለጹለት ከ15 ቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጎ እንደነበር አይዘነጋም።

በተጨማሪም ባለሥልጣናቱ፣ ‹‹አይኤምኤፍ ለብሔራዊ ባንክ መሰጠት አለበት ብሎ የሚመክረው የነፃነት ደረጃ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመንግሥት ተቋማት አግኝተውት የማያውቁትና ከአገሪቱ የሕግ ልማዶች (Legal Traditions) የራቀ ነው፤›› የሚል ምላሽ እንደሰጡት፣ ይሁን እንጂ አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ መንግሥትን አመክንዮ እንዳልተቀበለውና የተጠቀሱትን ክፍተቶች በዋናነትም የብሔራዊ ባንክ ነፃነትን የተመለከቱ ጉዳዮችን የመፍታት አስፈላጊነትን በድጋሚ አስረግጦ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና የምጣኔ ሀብት አማካሪ ግርማ ብሩ (አምባሳደር) ሰብሳቢነት፣ የባንኩን ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱን ጨምሮ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯን ፍጹም አሰፋን (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታውን እዮብ ተካልኝን (ዶ/ር)፣ ምክትል የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥውን አቶ ፈቃዱ ድጋፌን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታዋን ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢን በአባልነት፣ እንዲሁም የባንኩን ከፍተኛ አማካሪ አቶ ገብረየሱስ ጎንጤን በጸሐፊነት ያካተተ ነው።

ከብሔራዊ ባንክ ጋር በተያያዘ አይኤምኤፍ ያነሳቸውን ነጥቦች በተመለከተ ባለፈው ሳምንት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ምላሽ የሰጡት የተቋሙ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስታሊና ጆርጂዬቫ፣ ‹‹የብሔራዊ ባንክ ተቋማዊ ነፃነትን ለማረጋገጥ ሁሉም በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ አካላት በአጠቃላይ ዝግጁ መሆናቸውን በማረጋገጤ ደስ ብሎኛል። የባንኩ ተቋማዊ ነፃነት ወሳኝ የሆነው ለምንድነው? ለሚለው ምክንያትም፣ የሞኒተሪ ፖሊሲ ውሳኔዎች በአጠቃላይ ያሉ ማስረጃዎች ምን ዓይነት ምሥል ያሳያሉ በሚለው ጉዳይ ላይ በመመሥረት እንጂ፣ በፖለቲካዊ ድርድሮች መሠረትነት መሰጠት የለባቸውም፤›› ብለዋል።

በተጨማሪም ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮቪድ ወረርሽኝ፣  በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ በተፈጠሩ ችግሮች፣ እንዲሁም በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በምግብና በኃይል አቅርቦት ላይ የዋጋ ንረት ታይቷል፤›› ብለው፣ እነዚህን ክፍተቶች ለማለፍ የማዕከላዊ ባንኮች የወለድ ምጣኔን ከፍ በማድረግ የዋጋ ንረቱን እንዲወርድ የሚያስችሏቸው ጠንካራ የትግበራ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የመቻል አቅም መኖር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ፣ ‹‹የዋጋ ንረት በደሃው ላይ ግብር ማለት ነው፡፡ ማዕከላዊ ባንክ ውሳኔዎቹን በመረጃ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ካላሳለፈ፣ አገሪቱንም ሆነ ኢኮኖሚውን አያገለግልም። እናም በድጋሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን አስተዳደራዊ ነፃነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ዝግጁነት እንዳለ ነው እኔ የሰማሁት። እኛም ክህሎትና አቅም በማሳደግ የባንኩን ዘመናዊ የሞኒተሪ ፖሊሲ አቅም እንዲጠናከር ለማስቻል ድጋፍ እናደርጋለን፤›› ብለዋል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 937

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>