
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ሐማስ ያገታቸውን አራት የእስራኤል ሴት ወታደሮችን ቅዳሜ፣ ጥር 17/ 2017 ዓ.ም ለቀቀ።እስራኤል በበኩሏ በእስር ቤቷ የያዘቻቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን እንደምትፈታ ይጠበቃል።
ሐማስ በመጀመሪያው ምዕራፍ ስምምነቱ መሰረት በጋዛ ይዟቸው የነበሩ አራት የእስራኤል ወታደሮችን በጋዛ ከተማ ፍልስጤም አደባባይ ለቀይ መስቀል ባለስልጣናት በዛሬው እለት አስረክቧል።
ታጋቾቹ ከመለቀቃቸው በፊት ጭንብል ያጠለቁ የሐማስ፣ የእስላማዊ ጂሃድስት ታጣቂዎችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ፍልስጤማውያን በአደባባዩ ላይ ተገኝተው ነበር።
በመቶዎች ከሚቆጠሩ የሐማስ አባላት በተጨማሪ ሌሎች የፍልስጤም ታጣቂዎችም በሥፍራው ተገኝተዋል።
ታጋቾቹ ከመለቀቀቃቸው በፊት የቀይ መስቀል ተወካዮች እና የሃማስ ተዋጊዎች ሰነዶች ሲፈርሙ ታይተዋል። በዛሬው ዕለት የተለቀቁት የእስራኤል ወታደሮች ካሪና አሪዬቭ፣ ዳንኤልላ ጊልቦአ፣ ናአማ ሌቪ እና ሊሪ አልባግ መሆናቸው ተገልጿል።
የእስራኤል ወታደራዊ መለዮን ያጠለቁት አራቱ ታጋቾች ሲለቀቁ ተሰብስቦ ለነበረው ሕዝብ እጃቸውን ሲያውለበልቡ ታይተዋል።
እስራኤል በእስር ቤቶቿ ከያዘቻቸው መካከል 200 ፍልስጤማውያንን በዛሬው ዕለት ትለቃለች ተብሎም ይጠበቃል።
የጋዛው የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እሁድ፣ ጥር 11/ 2017 ዓ.ም ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ በሳምንቱ መጀመሪያ እስራኤል 90 ሴቶች እና ታዳጊ ወንዶች ፍልስጤማውያንን ስትፈታ ሐማስ ሦስት ታጋቾችን መልቀቁ ይታወሳል።ለበርካታ ፍልስጤማውያን እልቂት ምክንያት የሆነው የ15 ወራቱ ጦርነት እልባት እንዲያገኝ የተደረሰውን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ተከትሎ የታጋቾች ልውውጥ ሲደረግ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ኳታር፣ አሜሪካ እና ግብጽ ያደራደሩት ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት ምዕራፍ አለው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ።
እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማውያን ትለቃለች።
የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸውም ተገልጿል።
በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡም ይፈቀዳል።
በሁለተኛው የስምምነቱ ዙር ተጨማሪ ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና “ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት” ያለመ ሲሆን ይህም የሚተገበረው የመጀመሪያው ዙር 16 ቀን ሲሞላው ነው።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ጋዛን መልሶ መገንባት ሲሆን፣ ይህም ዓመታት ይወስዳል።
በዚህ ምዕራፍ የታጋቾች አስክሬንም ይመለሳል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ46,870 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።