Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

በሰሜን ወሎ ዞን በደረሰ የመኪና አደጋ ቢያንስ የ40 ሰዎች ሕይወት አለፈ

$
0
0
በአስቸጋሪ መንገድ ላይ ያለ ተሽከርካሪ እና ተሳፋሪዎች
የምስሉ መግለጫ,በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ አገልግሎት ችግር ከመኖሩ በተጨማሪ መንገዱም ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ ቢያንስ የ40 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች፣ የህክምና ባለሙያ እና የዓይን እማኞች ተናገሩ።

ትናንት ሐሙስ ጥር 15/2017 ዓ.ም. ከወረዳው ዋና ከተማ ኩርባ ወደ ደሴ ከ60 በላይ መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ በተለምዶ “ቅጥቅጥ” የተባለ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ “መታጠፊያ ስቶ” ወደ ገደል በመግባቱ አደጋው መድረሱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አደጋው ከጠዋቱ 12፡30 ከከተማው 10 ኪ.ሜ ገደማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሰጎራ በተባለ ስፍራ መድረሱ ተገልጿል።

አንድ የኩርባ መናኸሪያ አስተባባሪ “የመጀመሪያው የመንገዱ ሁኔታ፣ ሁለተኛ ፍጥነት ነው፣ ሦስተኛ ደግሞ የመኪናው የቴክኒክ ክፍል ችግር ነው” ሲሉ ለአደጋው ምክንያት ይሆናሉ ያሏቸውን ነገሮች ለቢቢሲ ጠቅሰዋል።

ተሽከርካሪው 28 መንገደኞችን የማሳፈር አቅም ያለው ቢሆንም ከ60 በላይ መንገደኞች አሳፍሮ እንደነበር የተናገሩት አስተባባሪው “ሰው በሰው ላይ ተደራርቦ ነው የሚሄደው” ሲሉ ሁኔታው የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል።

“መኪናው ሙሉ ለሙሉ ገደል ገብቶ፤ ገደሉን ጨርሶ እርሻ ላይ ነው ያረፈው” ያሉ ከአደጋው በኋላ ወደ ቦታው የደረሱ አንድ የዓይን እማኝ፤ ተሽከርካሪው የወደቀበት ስፍራ ከመንገዱ በ10 ደቂቃ የሚርቅ ነው ብለዋል።

መንገደኞቹ ለተለያየ ጉዳይ ወደ ደሴ ሲጓዙ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን የገለፁ አንድ ነዋሪ፤ በአብዛኛው ለህክምና የሚጓዙ ሰዎች፣ ተማሪዎች እና የመንግሥት ሠራተኞች እንደነበሩ ጠቁመዋል።

“ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ናቸው” ሲሉ ስለ ሟቾቹ ማንነት የተናገሩ ሌላ አካባቢው ነዋሪ፤ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች እና ተማሪዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

“በጣም አሰቃቂ” ሲሉ አደጋውን የገለፁት የመናኽሪያ አስተባባሪው፤ ከአደጋው ስፍራ ደርሰው አስከሬን በማንሳት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

“ምነው ባላይ ነው ያልኩት። አሁን ምግብ መብላት አልችልም” ሲሉ ተሳፋሪዎቹ ላይ የደረሰው አሰቃቂ አደጋ የፈጠረባቸውን ስሜት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አደጋው የደረሰበት ተሽከርካሪ ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ “ለቆራሊዮ ይጠቅም ካልሆነ መኪናነት የለውም። መኪናው እንኩትኩት ብሏል። ሙሉ ለሙሉ ወድሟል” ሲሉ ሌላ ነዋሪ የደረሰውን ጉዳት ግዝፈት ገልፀዋል።

የሟቾች አስከሬን ወደ ኩርባ ጤና ጣቢያ ተወስዶ ቤተሰቦች አስከሬን እንዲወስዱ መደረጉንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሹፌሩን ጨምሮ የሟቾቹ ቁጥር “ከ40 በላይ ነው” ያሉ አስከሬን ያነሱ ነዋሪ፤ 30 የሚሆኑ ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ጤና ጣቢያ እና ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

አንድ የጤና ጣቢያ ባለሙያ ወደ ተቋሙ የመጡ የሟቾች ቁጥር ከ25 በላይ እንደሆነ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፤ ከመንገድ ላይ አስከሬን ወደ ቤተሰባቸው እየተወሰደ እንደነበር ተናግረው የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ እንደሚል ጠቁመዋል።

ከአደጋው በኋላ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እንደተከታተሉ የተናገሩት የመናኸሪያ አስተባባሪውም በአደጋው የ40 ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ ተናግረዋል።

28 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ጤና ተቋማት መወሰዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጤና ጣቢያው ባለሙያውም ህፃናትን እና ታዳጊዎችን ጨምሮ 25 ሰዎች ቆስለው ወደ ጤና ጣቢያው መምጣታቸውን ገልፀዋል።

“ቢያንስ ወደ 17 የሚሆኑት ከባድ ጉዳት [የደረሰባቸው ናቸው]። ቀላል ጉዳት ደግሞ ወደ ዘጠኝ አካባቢ [ናቸው]” ብለዋል።

“ከአንድ ቤት ሁለት፤ ሦስት አስከሬን ስላለ የዛሬ ውሎ በጣም አስቸጋሪ ነው። [ከተማዋ] የደም ምድር ሆና ነው የዋለችው። ዋይታ ነበር፤ ለቅሶ ነበር” ሲሉ የደረሰውን ጉዳት ግዝፈት እና የማኅበረሰቡን ሐዘን ገልፀዋል።

የሟቾች ሥርዓተ ቀብር ትናንት እና ዛሬ [አርብ] በኩርባ ከተማ እና በተለያዩ ቀበሌዎች እንደተፈፀመ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በአካባቢው አንቡላንስ ባለመኖሩ ጉዳት ደረሰባቸውን ሰዎች በአውቶብሶች እና በጭነት ተሽካርካሪዎች የህክምና ግብዓት እጥረት አለባቸው ወደተባሉ ጤና ጣቢያዎች መወሰዳቸው እንዲሁም ጉዳቱ ከባድ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም ነዋሪዎች ስጋት አላቸው።

አካባቢው ላይ ባለው ግጭት ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት በአመዛኙ መቋረጡን የተናገሩ አንድ ነዋሪ “አብዛኛው የሚሠራው ሹፌር ከሞትኩም ልሙት ብሎ ተስፋ በመቁረጥ ነው” ሲሉ ሁኔታውን ገልፀውታል።

በዚህም ሳቢያ መንገደኞች በወረፋ እንደሚጓዙ የጠቆሙት ነዋሪው፤ ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው መጠን እስከ ሦስት እጥፍ ድረስ ሰዎችን አሳፍረው ይጓዛሉ ብለዋል።

በአካባቢው ባለው የሰላም ሁኔታ ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት እንደልብ ማግኘት እንደማይቻል የጠቆሙ ሌላ ነዋሪ፤ በዚህም ምክንያት ተሽከርካሪዎች ከአቅም በላይ ጭነው እንደሚጓዙ ገልፀዋል።

በወረዳው ባለፈው ኅዳር ወር “ሲኖትራክ” በተባለ ተሽከርካሪ ሲጓዙ የነበሩ ከ50 በላይ መንገደኞች ላይ የድሮን ጥቃት እንደደረሰባቸው ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።

ለሐሙሱ አደጋ ከመንገዱ አስቸጋሪነት ባለፈ የተጎጂዎች ቁጥር ከፍተኛ ለመሆኑ የትራንስፖርት ችግሩ ትልቅ ሚና እንዳለው ሁለት ነዋሪዎች እምነታቸውን ገልፀዋል።

ዳውንት ወረዳ ከመስከረም ወር ጀምሮ በፋኖ ታታቂዎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኝም ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>