
በርካታ የአፍሪካ ቀንድ እና የምስራቅ አፍሪካ መንግሥታት በዜጎቻቸው ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚፈጽሙ ከሰሞኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።እነዚህ መንግሥታት ተቺዎቻቸውን ዝም ለማሰኘት ጥቃትን እንደ መሳሪያ እየተጠቀሙበት እንደሆነ የባለፈውን የአውሮፓውያኑ 2024 የገመገመው የተቋሙ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ኬንያን ጨምሮ 25 የአፍሪካ አገራትን እንዲሁም በአጠቃላይ ከ100 በላይ አገራት የሰብዓዊ መብት አያያዝን ገምግሟል።”የዲሞክራሲ ተቋማት እና ዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብቶች እና የሰብዓዊ ሕግ መርሆዎች” ባለፈው ዓመት የተፈተኑበት ወቅት ነው ሲሉ የተቋሙ የአፍሪካ ዳይሬክተር ማውሲ ሴጉን ገልጸዋል። ሕዝባዊ ተቃውሞ በኬንያ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተከሰተውን የግብር ጭማሬዎችን ያካተተው የፋይናንስ ሕግን ተቃውሞ ተከትሎ በኬንያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተሸርሽሯል ብሏል ሂውማን ራይትስ ዋች። ተቃውሞው ከግብር ጭማሬ በተጨማሪ የመልካም አስተዳደር እጦት እና በአገሪቱ በሰፊው የተንሰራፋውን ሙስና እና አልቀመስ ያለውን የኑሮ ውድነትን ለመቃወም ነበር ወጣቶች ለተቃውሞ ወደ አደባባይ የወጡት። “ባለስልጣናት የተቃውሞው ሰልፉ መንስዔ የሆኑትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ተሟጋቾችን እና የተቃውሞ መሪዎችን ማስፈራራት፣ እስር እና ወከባን ፈጽመዋል” ብሏል የተቋሙ ሪፖርት። ከባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ ቢያንስ 60 ሰዎች ሲገደሉ 82 ሰዎች ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸውን የኬንያ ሰብዓዊ መብት ብሔራዊ ኮሚሽን አስታውቋል። “የስቃይ ምልክቶች የሚታይባቸው አስከሬኖች በወንዞች፣ በጫካዎች፣ በተቆፈሩ ጉድጓዶች እንዲሁም በተተው የአስከሬን ማስቀመጫ ስፍራዎች ተጥለው ተገኝተዋል” ብሏል ተቋሙ የባለፈውን የአውሮፓውያኑን ዓመት በገመገመበት ሪፖርቱ። ተቋሙ በተጨማሪም የሲቪል መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለተቃዋሚዎች የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል በሚል በወነጀላቸው የኬንያ መንግሥት ወከባ እና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነም አትቷል።
በሱዳን ተፋፍሞ የቀጠለው ጦርነት
የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል እየተደረገ ያለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ላይ ትኩረት አድርጓል። ለ21 ወራት የዘለቀው የሱዳኑ እርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እና በዓለማችን እጅግ የከፋ ቀውስን ያስከተለ ነው። ተፋላሚዎቹ በተለይም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ “የጦር ወንጀል፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን” እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰቶችን እየፈጸሙ ነው ሲል ሪፖርቱ አመልክቷል። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና አጋሮቹ ፈጽመዋቸዋል ከተባሉዋቸው ወንጀሎች መካከል የጅምላ ግድያ፣ ጾታዊ ጥቃቶች እና ሕዝብ በሚጨናነቅባቸው ሥፍራዎች ከባድ የፈንጂ መሳሪያዎችን መጠቀምን እንደሚያጠቃልልም ሪፖርቱ አክሎ አስፍሯል። በተጨማሪም በርካታ ሕዝብ በሚኖርባቸው ሥፍራዎች አካባቢዎች መሰረተ ልማቶችን ማውደም፣ መድፈር፣ የዘፈቀደ ግድያዎች፣ እስረኞችን ማሰቃየት እንዲሁም የአካል ጉዳት አድርሰዋል ተብለዋል። የሱዳን አውዳሚ ጦርነት በዓለማችን እጅግ የከፋ መፈናቀል ተብሎ በተጠራው ቀውስ ከ10.8 ሚሊዮን በላይ ሲፈናቀሉ አገሪቱ በከፋ ረሃብ ላይ ትገኛለች። ጦርነቱ በቅርቡ ወደ ማዕከላዊ እና ምስራቃዊ ግዛቶች መስፋፋቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ስደተኞችን አደጋ ላይ መጣሉ ተነግሯል። በአገር ውስጥ ተጠልለው ካሉ ስደተኞች በተጨማሪ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የሱዳን ሕዝብ እንደ ቻድ፣ ግብጽ እና ኢትዮጵያ ባሉ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸው ተገልጿል።
በኤርትራ የቀጠለው ጭቆና
የኤርትራ መንግሥት የእምነት ነጻነትን ጨምሮ የዜጎቹን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች በመግፈፍ እንደቀጠለበት የሂውማን ራይትስ ዋች የዓመቱ ሪፖርት አመልክቷል። ኤርትራ ነጻነት ካገኘችበት ከአውሮፓውያኑ 1993 ጀምሮ ምርጫ አላካሄደችም። ያልተመረጡት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሦስት አስርት ዓመታት በዘለቀ ሥልጣንን ተቆናጠው ይገኛሉ። አገሪቱን ከሚመራት ሕዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲና ለፍትህ (ህግደፍ) ፓርቲ ውጭ ሌላ የፖለቲካ ድርጅት አይፈቀድም። ሕገወጥ እስር፣ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የመንግሥት ተቺዎችን ጨምሮ በግዳጅ መሰወር በኤርትራ የተለመደ ተግባር እንደሆነ ተቋሙ በሪፖርቱ አካቷል። ሪፖርቱ አክሎም ኤርትራ በግዳጅ የምታደርገው የውትድርና ምልመላ በርካቶች እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል ብሏል። በዚህ ምልመላ የተወሰኑ ህጻናት እንዳሉበት ተመልክቷል።

በሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ የተፈጸሙ ጥቃቶች
የሶማሊያ መንግሥት በታጣቂው አልሻባብ ላይ እየወሰደው ያለው ወታደራዊ ዘመቻ ባለፈው ዓመት የበርካቶችን ሕይወት የነጠቁ ጥቃቶች የተፈጸመባቸው ናቸው። በነዚህ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን እንዲሰደዱ ምክንያት መሆኑን ሪፖርቱ አጉልቷል። የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት አልሻባብ፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና የታጠቁ ሚሊሻዎች በሴቶች እና በታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃትን እንደፈጸሙ እና በህጻናትም ላይ በስፋት እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ቀጥለውበታል ብሏል። በሶማሊያ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ ላይ መጠነኛ መሻሻሎች ቢኖሩም በአገሪቱ 4.4 ሚሊዮን የሚገመቱ ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተቋሙ ገልጿል። በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን፣ አልሻባብ እንዲዳከም እና ንጹሃን ዜጎችን እንዲጠበቁ ያለመው አዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ስምሪት በቅርቡ ይጀምራል። ነገር ግን ሂውማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ ይህንን ፕሮግራም የገንዘብ እና የሎጂስቲክ ድጋፍ በተመለከተ ጥያቄዎች አሉ ብሏል።
በብሩንዲ የጨመረው መንግሥታዊ ጫና
በብሩንዲ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ ተሟጋቾች እና በተቃዋሚዎች ላይ የሚደርሱ ዛቻዎች እና እስራቶች እንደቀጠሉ ነው ይላል ሂውማን ራይትስ ዋች።ሪፖርቱ የብሩንዲ ገዥ ፓርቲ የወጣቶች ሊግ አባላት (ኢምቦኔራኩሬ) በመላው አገሪቱ በሚፈጸሙ ተከታታይ ግድያዎች፣ ጥቃቶች እና ስቅይቶች በሰፊው እየተሳተፉ እንደሆነ አትቷል።በተጨማሪም የአገሪቱ ባለስልጣናት በሚዲያ ነጻነት ላይ ተጨማሪ ገደቦችን እየጣሉ ነው። በብሩንዲ ከሚገኙት የመጨረሻዎቹ ነጻ ጋዜጦች አንዱ የሆነው ኢዋኩ ፕሬስ፣ በአውሮፓውያኑ 2024 ዓመቱን ሙሉ እንዳይታተም ማስጠንቀቂያ ደርሶታል።
የምዕራብ አፍሪካ መፈንቅለ መንግሥታት
ሂውማን ራይትስ ዋች ባወጣው በዚህ ሪፖርቱ በምዕራብ አፍሪካ በወታደራዊ ኃይሎች የሚገዙትን እንደ ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ፣ ኒጀር ያሉ አገሮችን ተመልክቷል። እነዚህ ወታደራዊ አገዛዞች ተቃዋሚዎችን እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማፈን ቀጥለዋል ያለው ይህ ሪፖርት፣ በእነዚህ አገራት ሙስናን ለማዋጋት እየተደረጉ ያሉ በርካታ ጥረቶች ወደ ኋላ ተመልሰዋል ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ቀናት በፊት የወጣው የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት በደቡብ አፍሪካዋ አገር ሞዛምቢክ ከምርጫው በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተገደሉበትን ሁከትና ብጥብጥ አጉልቶ አሳይቷል።