የዩናይትድ ኪንግደም የግምጃ ቤት ሚኒስትር ቱሊፕ ሲዲቅ በባንግላዴሽ እየተካሄደባቸው ካለው የሙስና ምርመራ ጋር በተያያዘ በደረሰባቸው ጫና ከሥልጣናቸው ለቀቁ። ሚኒስትሯ ባለፈው ዓመት ከሥልጣናቸው ከተወገዱት አክስታቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ ጥያቄ ከተነሳባቸው በኋላ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሲር ላውሪ ማንጉሰ ጋር ወስደውት ነበር። ሰር ላውሪም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ትክክለኛ ማስረጃ እንዳላገኙ፤ ነገርግን ሚኒስትሯ ከአክስታቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ሳቢያ የስም ማጥፋት አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችል በማሰብ ጥንቃቄ አለማድረጋቸው የሚያፀፅት ነው ብለዋል። ሲዲቅ በበኩላቸው በኃላፊነታቸው ላይ መቆየት ለመንግሥታቸው ጥሩ ሊሆን እንደማይችል ገልጸው፤ ነገር ግን ምንም የሰሩት ወንጀል እንደሌለ ተናግረዋል። የሲዲቅ ከሥራ መልቀቅ ከመገለጹ አስቀድሞ በባንግላዴሽ የሙስና ምርመራ ከሚካሄድባቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ተካቷል። የወግ አጥባቂው መሪ ኬሚ ባደኖች በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚኒስትሯን ለመከላከል እና ለመጠበቅ ዘግይተዋል ሲሉ ወቅሰዋል። መሪው ጨምረውም አሁንም ባንግላዲሽ በቱሊፕ ላይ የወንጀል ክስ ሲመሰርት ሚኒስትሯ ከሥራ በመልቀቃቸው ሃዘናቸውን ከመግለጽ ባሻገር ያደረጉት ነገር የለም ሲሉ ኮንነዋል። ” ከደካማ ጠቅላይ ሚኒስትር ደካማ አስተዳዳር ” ሲሉም ተችተዋል። ሰር ኬር የሲዲቅን የሥራ መልቀቂያ መቀበላቸውን በገለጹበት ደብዳቤ ለሳዲቅ በራቸው ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ገልጸዋል። በዩኬ የፋይናንስ ገበያ ያለውን ሙስና መከላከልን ጨምሮ ለግምጃ ቤቱ የኢኮኖሚ ኃላፊነት ሚና የነበራቸው ሲዲቅ፣ ባለፈው ወር ቤተሰባቸው በባንግላዴሽ በተሰራ የመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ 3.9 ቢሊየን ፓውንድ ገንዘብ ዘርፈዋል በሚል ስማቸው ተጠቅሶ ነበር።የቀድሞው የባንግላዴሽ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አክስታቸው ሼይክህ ሃሲና የአዋሚ ሊግ ኃላፊ የነበሩ ሲሆን ባለፈው ዓመት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በስደት ነው ያሉት።

ቢቢሲ የተመለከተው የፍርድ ቤት ሰነድ ሃጃጂ ፣ እአአ በ2013 በባንግላዴሽ አዲስ የኒውክሌር ኃይል ጋር በተያያዘ አክስቷ ከሩሲያ ጋር ለማስማማት ሲዲቅ ረድተዋል ሲሉ ከሰዋል። የኃይል ማበልጸጊያውን የስምምነት ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ ሲሆን ከሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ፎቶ ተነስተዋል። ሆኖም ሰር ላውሬ እና ሲዲቅ በወቅቱ የነበረውን አውድ ማህበራዊ ግንኙነትና ጉብኝት እንደነበር አስረድተዋል። ሰር ላውሪ እንዳሉት ሲዲቅ በባንግላዴሽ እና በሩሲያ መንግሥታት መካከል በተካሄደው ውይይት ምንም ዓይነት ግንኙነት የላትም። የባንግላዴሽ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲዲቅ እናቷን ሬሂና ሲዲቅ ሃሲናን ሥልጣኗን በመጠቀም በጣም ወሳኝ በሆነ እና ዲፕሎማቲክ ቦታ መሬት ለማግኘት ተፅዕኖ ለማሳደር እናቷን ስትደግፍ ነበር ሲል ከሷል። ከዚህም በተጨማሪ የባንግላዴሽ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን አክስታቸውን ለመርዳት ሥልጣናቸውን ተጠቅመዋል ብሏል። የሲዲቅ ቃል አቀባይ በበኩላቸው በሚኒስትሯ ላይ ለቀረቡት ክሶች ምንም አይነት ማስረጃ አልቀረበም ብለዋል። የሲዲቅን ከሥልጣን መልቀቅ ተከትሎም የሌበር የፓርላማ አባል ኢማ ሪይኖልድስ ለግምጃ ቤቱ አዲስ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ሪይኖልድስ ለመጀመሪያ ጊዜ የፓርላማ አባል የሆኑት በ2010 ሲሆን በድጋሜ ወደ ፓርላማ የተመለሱት ባለፈው ዓመት በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ወቅት ነው።