የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በአንድ ቤት ውስጥ ታግተው የቆዩ እና ኢትዮጵያዊ ናቸው ተብሎ የሚታመኑ 26 ሰዎችን ጆሃንስበርግ ውስጥ ማግኘቱን አስታወቀ።
በቤቱ ውስጥ ከተገኙት ስደተኞች መካከል 15ቱ እርቃናቸውን የነበሩ ሲሆን፣ በቤቱ አቅራቢያ የተገኙት ቀሪዎቹ አስራ አንዱ ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸው ተነግሯል።
ሃያ ስድስቱ ሰዎች የተገኙት ሐሙስ አመሻሽ ላይ በጆሃንስበርግ ከተማ ሰሜን ምሥራቅ ዳርቻ ላይ ባለ ሰፈር ውስጥ ከጎረቤቶች በተገኘ ጥቆማ አማካይንት መሆኑን ፖሊስ ገልጿል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም ሦስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ኢትዮጵያውያን ናቸው የተባሉት ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዴት እንደገቡ ግልጽ ባይሆንም ባለሥልጣናት የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ መሆናቸውን ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ ነው።
ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “የሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ቡድን” መዋቅርን ማፍረሱን አመልክቷል።