ታፈሰ ወርቁ –
ህወሃት ትግራይን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ፣ ገና “የጎንደርን ጦር ደረመሰ፣ ሃሙሲት ደረሰ፣ ጎጃምን አዳረሰ … ይባል በነበረበት ጊዜ፣ አ.አ ከመግባቱ በፊት በጎጃም ትንሿ የዳንግላ ከተማ ውስጥ ስራ ላይ ነበርኩ። በአንድ ሱቅ ውስጥ እቃ ልገዛ ቆሜአለሁ። ወዲያው አንድ የህወሃት ታጣቂ ሱቁ ውስጥ ገባ። አማርኛ አይችልም። ግን እንደ ምንም እየሰባበረም፣ በጥቅሻም ቢሆን ሲጋራ ለመግዛት መፈለጉን ለባለሱቁ ገልጾ የጠየቀውን አገኘ። ጥቂት ቆይቶ አሁን የማላስታውሰውን ነገር በተሰባበረ አማርኛ ተናገረ። ሁለቱ አልተግባቡም። ግራ መጋባታቸውን አይቼ ጣልቃ ገባሁ፣ እና ለሁለቱም ማስተርጎም ጀመርኩ። ሁለቱም ደስ አላቸው። እናም ወሬያችን ደራ። ያ የህወሃት ታጣቂ፣ በጫወታችን መሃል፣ እግራቸው በረገጠበት በአብዛኛው የጎንደር እና ጎጃም ገጠር እና ከተማ ውስጥ ሁሉ ያለው ህዝብ ቤቱ እያስገባ ያበላ ያጠጣቸው እንደነበር የነገረኝን እና በመጨረሻም “ቧ! አታ… እዚአቶም ከማና ጥኡያት ኢዮም” (አንተ! ለካስ እነዚህ [አማራዎች] እንደኛ ጥሩ ሰዎች ናቸው) ያለኝን ሳስበው… ከዚያም ጋር ህወሃት ጫካ ውስጥ ሆኖ፣ አዲስ አበባም ገብቶ አገረ-ገዢ ሆኖ በቆየበት ጊዜ ውስጥ በአማራ ህዝብ ላይ የዘራው የጥላቻ ዘር በቅሎ፣ ተባዝቶ፣ ጎምርቶ እና ለምርት ደረሶ… ህዝቡን በጅምላ እየገደለ እና እያስገደለ፣ በበሽታ እና ድህነት በማፈናቀል እና በጅምላ ግድያ አማራውን እየፈጀ እስካሁን አለ። የዚህን “አማራዎች እንደኛ ጥሩ ናቸው እንዴ” አስተያየት የሰጠኝ ታጣቂ ገጽታ ውስጥ የነበረው ጸጸት አሁን ድረስ ይታየኛል። ገጽታው ላይ ቅንነት እና ሰብዓዊነት ታያለህ፣ ምክንያቱም ስለ አማራ የተነገረውን እና በአይምሮው ያለውን ነው የተናገረው፣ መሬት ላይ እያየ ያለው ግን ሌላ ሆኖበታል። እንዲህ አይነቶቹ “ቅን” የህወሃት አባላት፣ ያኔ ገና መለስ ዜናዊ ክራባት አስሮ እና ተሽቀርቅሮ በቲቪ መስኮት ያዩት ዕለት፣ በርካታዎቹ አብደዋል፣ አንዳንዶቹ በግልጽ በመቃወማቸው ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ በርካቶቹ ደግሞ ብጅምላ ተባረዋል፤ በድል አጥቢያ አርበኞቹ፣ ያለ ሆዳቸው አገርም ሆነ ወገን በሌላቸው፣ በትግራይ እና የሌላም ክ/ሃገራት አድርባዮች ተተክተዋል። የመለስን ጋንግ ተቀብለው እና አምነው የቆዩት እና እስካሁንም የዘለቁት ደግሞ ዛሬ ዛሬ ባለሃብቶች እና ኢንቬስተሮች ሆነዋል። ይህ ማለት ግን ህወሃት መጀመሪያ ላይ አላማው ትክክል ነበር ማለት አይደለም። ሲጀመር ጎደሎ አላማ ይዞ የተነሳ ድርጅት ነው። በስሩ ያሰባሰባቸው ቁጥራቸው በርካታ የሆኑት የህወሃት አባላት ግን እውነትም ለትግራይም ይሁን ለኢትዮጵያ ህዝብ ትንሳኤ ሲሉ እየተዋጉ ያሉ የመሰላቸው፣ እየተሽቀዳደሙ ሞተው፣ ግን ደግሞ ኢትዮጵያን ይዘው የሞቱ ናቸው። ማሌሊት/ህወሃቶች በአማራ ህዝብ ላይ የጠነሰሱት ሴራ እና እስካሁን ያደረሱት ጥፋት፣ በሰነድ ደረጃ ያሰፈሩት እና እየተገበሩት ያለ በመሆኑ፣ ህወሃት መንግስት ከመሆኑ በፊት ጀምሮ በወልቃይት ጠገዴ እና አካባቢው የአማራ ነገድ ህዝብ ላይ የደረሰው እልቂት ግፍ (እጅን የኋሊት አስሮ በተከዜ ዉሃ ሙላት ውስጥ አስገድዶ ማስገባት…ወዘተ) አይነት በደል ሊቆነጥጠን ይገባል። ወደፊት ስንቱን የህወሃቶች ወንጀል እንሰማ ይሆን? እድሜ ለኢሳት። ይህ አንድ ታጣቂ፣ እንዳለ አይምሮው ውስጥ ያለውን ነገር እንደወረደ (ሳይፈትሽ/sensor ሳያደርግ) የተናገረው መሆኑ ደግሞ እጅግ ሊያስደነግጠን፣ ሊያመን እና ግፍ እና በደሉን፣ በትግራይ ጎሳ ተውላጆች አይምሮ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኦሮሞውም አይምሮ ላይ ያሳደሩትን ጥላቻ በሚመጥን መልኩ፣ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ነጻነት ወደሚያጎናጽፍ እና ወደ ድል ሊያመራን በሚችል በማንኛውም አይነት ትግል መሳተፍ፣ በእልህ፤ በቀጣይነት፣ ግን ደግሞ በቁርጠኝነት፣ እያንዳንዳችን ምን ማድረግ እችላለሁ? ብለን ራስን በመጠየቅ እና በዚያው ልክ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዳሉት እያንዳንዱ ሰው፣ በተለይም በየውጭ አገሩ ተሰዶ የሚገኘው ህዝብ፣ ለሚደግፈው ድርጅት፣ በጉልበት፣ ገንዘብ እና እውቀት አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባዋል። እኔ ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነጻነት እና አንድነት ለሚታገለው የግንቦት ሰባት አርበኞች እና አብሮ ህብረት የፈጠረው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ቋሚ ደጋፊ ነኝ። አንተስ? አንቺስ? ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
