

ከላይ በአጭሩ የተዘረዘሩት ኩነቶች የሚያረጋግጡት ህወሓት የተማከለ አመራር አጥተው መንገድ የጠፋቸው፤ ሆኖም ግን እጃቸው ውስጥ የገባው ስልጣንና ሀብት ላለማጣት ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ አውሬዎች ስብስብ መሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነቱን የአውሬዎች ስብስብ የሚገዛው የህግም ሆነ የሥነ-ምግባር ገደብ የለም። ህወሓት እስር በርሳችንን አባልቶ አገራችንንና ሕዝቧን ወደ ማንወጣው አዘቅት ከመክተቱ በፊት ራሱ ህወሓትን ማስወገድ እና በምትኩት ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን መገንባት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው። ይህ ካላደረግን አሁን በወህኒ ቤቶች የሚደረገው ዜጎችን ልብስን አስወልቆ የማዋረድ አስነዋሪ ተግባር ነገ በአደባባዮች የማይደረግ ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለንም። ይህ ትውልድ ኃላፊነቱ ካልተወጣ ህግን አክብረው ከአገዛዙ የተለየ ሀሳብ እናራምዳለን የሚሉ ወገኖቻችን በሙሉ አደጋ ውስጥ ናቸው። በህወሓት መሠሪ ተግባራት ሳቢያ በክርስትናና እስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው መግባባት እንዲሻክር እየተደረገ ነው። ዜጎችን በማዋረድ የሚደሰት አገዛዝና ለመዋረድ የፈቀደ ሕዝብ እስካለ ድረስ የቁልቁለቱ ጉዞ መጨረሻ የለውም። ይህንን ማስቆም ያለብን እኛ ሁላንችንም ነን። በአደባባይ መደራጀት ሲከለከል በምስጢር መደራጀትን መልመድ የኛ ኃላፊነት ነው። የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓልን ስናከብር ከቀደምቶቻችን ልንወርስ ከሚገቡን እሴቶች አንዱ ለክብራችን ዋጋ መክፈል ያለብን መሆኑን ጭምር ነው። የኢትዮጵያዊያን ክብር በወያኔ ሲዋረድ እያየን ዝምታን ከመረጥን ከዚህም የባሰ እንዲመጣ መፍቀዳችንን እንወቀው።
አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የዜጎችና የአገር ውርደት ይብቃ! በተባበረ ክንድ ህወሓት ይወገድ፤ በምትኩም ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመመሥረት መሠረት እንጣል፤ ይህንን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣት በኅብረት እንነሳ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!
