ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ በተካሄዱት አራት ጠቅላላ ምርጫዎች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተወዳደሩበት በአደዋ የምርጫ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በዘንድሮ ምርጫ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲወዳደሩ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ወደ ፌዴራል መንግሥት ከመምጣታቸው በፊት በደቡብ ትግራይ ክልል ምክትል ዋና አስተዳዳሪ፣ በኋላም የትግራይ ክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡
![0803fe72dc628e4a2bf444d22497ca6e_XL]()
የአደዋ ከተማ ተወላጅ የሆኑት ዶ/ር ደብረ ጽዮን ወደ ትጥቅ ትግል ከመግባታቸው በፊት፣ ከተማውን በመወከል ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች እንደነበሩ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡
አደዋን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአራት ተከታታይ ምርጫዎች የተወዳደሩት ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሕወሓትን ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ ኢሕአዴግም ከተመሠረተበት ከ1981 ዓ.ም. ጀምሮ በሊቀመንበርነት የመሩ ሲሆን፣ መጀመሪያ ለሦስት ዓመታት የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዚዳንት፣ ቀጥሎም እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገሪቱን መምራታቸው ይታወሳል፡፡
በአራተኛው ጠቅላላ ምርጫ የቀድሞዋ ሕወሓት ታጋይ ወ/ት አረጋሽ አዳነ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ አባል የሆነበትን መድረክ በመወከል፣ ከቀድሞ የትግል ጓዳቸው ከአቶ መለስ ጋር መፎካከራቸው አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ምርጫ ግን ዶ/ር ደብረ ጽዮንን የሚወዳደረውን ተፎካካሪ ዕጩ ማወቅ አልተቻለም፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕጩ ተወዳዳሪዎችን የመጨረሻ ዝርዝር የያዘውን ቅጽ አራት በመባል የሚታወቀውን ሰነድ ይፋ ባለማድረጉ፣ በተለይ የኢሕአዴግና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚወዳደሩባቸውን የምርጫ ክልሎች ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ባለፈው ሳምንት ዋነኛ የኢሕአዴግና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩዎች በአዲስ አበባ የሚወዳደሩበትን ይፋ ያልሆነ ዝርዝር ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
